ይልማ ኪዳኔ
ሜ/ጄ ክንፈ ዳኜ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተብሎ የሚጥራውና በወታደሮች በሚመራው ትልቁ የመንግስት ኢንዱስትሪ ውስጥ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ራሳቸውን “በፈቃደኝነት” እስከ አገለሉበት ጊዜ ድረስ ይሰሩ ነበር። ይህ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሃገር ሓብትና ንብረት የሚዘረፍበት ቦታ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው። እዚህ ፎቶግራፍ ላይ የሚታየው ትንሽ ቤተ መንግስት የመሰለ ነገር የእሳቸው ቤት ነው። የኤርትራውን ፕሬዚዳንት የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂን አኗኗር ከተመለከት በኃላ ለእሳቸው ያለኝ ከበሬታና አድናቆት ሲጨምር የእኛዎቹ ሌቦች አኗኗር ግን ይበልጥ የሚዘገንን ከመሆንም አልፎ ምን ያህል ጨካኞች እንደሆኑ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
………………
ሜ/ጄ ክንፈ ዳኜ ወታደር እንጂ ነጋዴ እንዳልሆኑ እሳቸውም የሚክዱት ነገር አይመስለኝም። ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ በደሞዛቸው ቤተሰብ አስተዳድረውና ለኑሮ የሚያሰፈልገውን ወጪ ሸፋፍነው የምትቀራቸውን ትርፍ ገንዘብ ወደ ጎን በማድረግ በቁጠባ እንኳን ይሄን ቤት መስራት አይደለም የቤቱን መስኮቶችንም መግዢያ የሚሆን ገንዘብ መቆጠብ አይችሉም። በእርግጥ ሜ/ጄ ክንፈ ዳኜ ቢጠየቁ ቤቱን የሰራሁት በቀጠባ ካስቀመጥኩት ገንዘብና መንግስት በትግል ጊዜ ላደረኩት “አስተዋጾ የሰጠኝ ገንዘብ” የሚሉት ቋንቋ አላቸው ጋር በማጣመር ነው ይህን ቤት የሰራሁት እንደሚሉ ምንም ጥርጣሬ የለኝም። የሟቹ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ለመቀለ የእግር ኳስ ክለብ 30 ሚሊዮን ብር ስጦታ ስትሰጥ የተናገረችው የሚረሳ አይደለም። ወ/ሮ አዜብ ስትናገር በወር ከማገኛት ስድስት ሺህ ብር ላይ በመቆጠብ ነው ይህን የገንዘብ ስጦታ ለክለቡ የሰጠሁት ብላ ስትናገር ወይ የሚታዘበኝ የለም ብላ አሊያም ህዝቡን እንደ ደንቆሮ ቆጥራው ሊሆን ይችላል። ምንም አፍረት የሚባል ነገር የፈጠረባቸው ሰዎች አይደሉም።
………
