>

ኤርትራን (ባሕረምድርን) ወደ እናት ሀገሯ የመመለሱ ጥረት በሚያሳዝን ሁኔታ ከሸፈ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

ኤርትራን (ባሕረምድርን) ወደ እናት ሀገሯ የመመለሱ ጥረት በሚያሳዝን ሁኔታ ከሸፈ!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
“አጠፋሁ ብላ አጋጋመችው!” 
 
* የዚህች ሀገር ነገር ጭራሽ ተወሳስቦ ቁጭ አለ፡፡ 
እነ አቶ ኢሳይያስ በዚህ ጉብኝታቸው የዐቢይን ግብዣ በመቀበል መዋሐዳችንን አንድ መሆናችንን ያውጃሉ የሚል እምነት ወይም ግምት ነበረኝ፡፡ ዝም ብየ ስቃዥ አልነበረም ይሄንን ያሰብኩት፡፡ ነገር ግን ስድስት ፈጠው የሚታዩ ምክንያቶች ስላሉ ነበረ፦
1ኛ. ደርግ ከወደቀና ሸአቢያና ወያኔ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሸአቢያ የመገንጠል ዓላማውን የተወ መሆኑን ሲያስታውቅ እነ አቶ መለስ ማባበያ አሰብን በመስጠት ያለ ፍላጎቱ ገፋፍተው እንዲገነጠል ያደረጉት በመሆኑ፡፡
2ኛ. መገንጠሉን ተከትሎ ላለፉት 27 ዓመታት ከደረሰው ሁለንተናዊ ኪሳራ እንደሰው ላይማሩ የሚችሉበት ምክንያት ሊኖር ስለማይችል ወደ እርምት እርምጃ ይገባሉ ከሚል ምክንያታዊና አመክንዮአዊ ግምት የተነሣ፡፡
3ኛ. ሕዝባዊ ግንባር ወይም ሸአቢያ የመገንጠሉን ሐሳብ የተው ሆኖ እያለ በወያኔ ወይም በነአቶ መለስ ገፋፊነትና በአሰብ የማባበያ ስጦታ ተገፍተው የተገነጠሉ ከሆነ የዐቢይን የማግደርደሪያ ግብዣ ተቀብለው እንደገና ለመዋሐድ ለሸአቢያ ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ አልነበረምና፡፡
4ኛ. ኢትዮጵያንና ባሕረምድርን (ኤርትራን) ሁለቱንም በማያግባቡ ነገሮች አግባብቶ አስማምቶ በጥሩ ጉርብትና እንዲቀጥሉ ከማድረግ ይልቅ ሁለቱን መቀላቀሉና እንደቀድሞው አንድ ሀገር አድርጎ መቀጠሉ የሚቀል ከመሆኑ የተሣ፡፡
5ኛ. እነ አቶ ኢሳይያስ በተደጋጋሚ እንደገለጹት ወደፊት አንድ መሆናችን የማይቀር በመሆኑ “በሌላ ዘመን በሌሎች ሰዎች መልሰን መዋሐዳችን የማይቀር ከሆነና የሕዝቡም ፍላጎት ከሆነ እኛን በሚተኩን በሌሎች ሰዎችና በሌላ ዘመን አንድ ከምንሆን ወይም መልሰን ከምንዋሐድና እኛ ስሕተታችንን ሳናርም ከነስሕተታችን አልፈን የታሪክ ተወቃሾች ተከሳሾች ከምንሆን በእኛውና በዚሁ ዘመን እናድርገው!” ብለው ማሰባቸው አይቀርም ከሚል፡፡
6ኛ. አቶ ኢሳይያስ አዲስ አበባ ላይ “ከእንግዲህ አንድ ነን ሁለት ሀገር የሚለን ካለ እሱ ሞኝ ነው!” ብሎ በመናገሩ፣ አዋሳ ላይ ደግሞ “አደራውን ለዶ/ር ዐቢይ ሰጥቻለሁ እሱ ይምራን!” ብሎ መናገሩ በእነኝህ ምክንያቶች ነበር እንደዛ ላስብ ችየ የነበረው፡፡
እነ አቶ ኢሳይያስ ግን ምክንያታዊነት ፈጽሞ በራቀው ግትርነት ታንቀው የተያዙና በዚህም ምክንያት ባልተለመደ መልኩ የተለዩ ፍጥረቶች በመሆናቸው የፈለገ ነገር ቢፈጠር ስሕተት መሆኑን እያወቁም “የኢትዮጵያን ለጋራ የእኛን ለብቻ መጠቀም!” በሚለውና ለግጭት የዳረገንን የቀድሞ ምኞታቸውን፣ ፍላጎታቸውን ሊተው ሊጥሉ ፈጽሞ ባለመፈለጋቸው፣ በኢትዮጵያ ሀብት ባሕረምድርን (ኤርትራን) የአፍሪካ ሲንጋፖር ከማድረጉ ሕልማቸው ጋር የቆረቡ በመሆናቸው በሰውኛ ስሌት አስልቸ ከላይ ከጠቀስኳቸው እውነታዎች የተነሣ አንድ ለመሆን ለመዋሐድ ወይም መልሶ ለመቀላቀል ወስነው የመጡና ይሄንንም በሚሊኒየም (በአምዓት) አዳራሽ በአልታሰብ (በሰርፕራይዝ) ዜና አውጀው የሁለቱንም ሕዝብ ያስጨፍሩታል የሚለው እምነቴ ወይም ግምቴ ሳይሰምር ቀርቷል ወይም ከሽፏል፡፡ እጅግ እጅግ እጅግ ያሳዝናል!!!
ዐቢይ አስመራ ሔዶ እንዲሁም ኢሳይያስ እዚህ ከመጣ በኋላም እዚህ ሲናገራቸው የነበሩ ነገሮችን ልብ ብላቹሃቸው ከሆነ ይናገራቸው የነበሩ ነገሮች በሙሉ እነ ኢሳይያስ አንድነትን መዋሐድን እንዲያስቡ የሚጫኑ ወይም “ይሄንን ዕድል ተጠቀሙበት!” የሚል ልምምጥ ያለባቸው የማግደርደሪያ ንግግሮች ናቸው የነበሩት፡፡ እነ አቶ ኢሳይያስ ይሄ ጠፋቷቸው አልነበረም፡፡ ስላልፈለጉ ነው አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጡት ያልቻሉት፡፡
በጉጉት የምትጠበቀዋ ሰዓት ደርሳ በአምዓቱ አዳራሽ አቶ ኢሳይያስ አጭርና ባዶ ንግግር አድርጎ ከተቀመጠ በኋላ ዐቢይን ልብ ብላቹህ ተመልክታቹህት ከሆነ ከኢሳይያስ መስማት የፈለገው የጠበቀው ነገር እንደነበረና ከአቶ ኢሳይያስ ባለመስማቱ ከፍተኛ ቅሬታ እንደተሰማው ፊቱ ላይ ይነበብበት ነበረ፡፡
ከዚህ ቅጽበት በኋላ ዐቢይ እንዲታወቅበት ባይፈልግም ከኢሳይያስ ንግግር በኋላ እፍር ኩምሽሽ እንዲል፣ ፊቱ ጥቁር እንዲል ያደረገው የዚያ ያልበሰለ የሃጫኑ ጠባብና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ወራሪነትን የሚያበረታታ ቅስቀሳው ሳይሆን ይሄው ከኢሳይያስ መስማት ፈልጎት የነበረውን ባለመስማቱ ነው ሌላ አይደለም፡፡ ዐቢይ የሠዓሊ ለማ ጉያን የካባ ስጦታ ለአቶ ኢሳይያስ ሲያስረክብ እንኳ ፊቱ አልተፈታም ነበረ፡፡
እነ ኢሳይያስን ውሕደቱን እሽ ለማሰኘት ወያኔ ጥሩ ስልት ነድፎ ለዐቢይ ተልእኮውን ሰጥቶት ነበረ፡፡ ዐቢይም ከሚችለው በላይ ተንቀሳቅሶ እነ ኢሳይያስን ተጭኗል ግፊት አድርጓል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ሊሳካለት አልቻለም፡፡ ተልእኮውን ግን በሚገባ ነው የተወጣው፡፡
እነ ዐቢይ ከድርድሩ በፊት የሱንና የኢሳይያስን ጉብኝት ያስቀደሙት የመዋሐዱን ነገር “ቀንቶኝ አሳምናቸው እንደሆን ልሞክራቸው!” በሚል ተስፋ ነበረ፡፡ እነሱ አያ ወይ ፍንክች!!! ኧረ! ኧረ! ኧረ! እነዚህ ሥጋ የለበሱ አጋንንት ይሆኑ እንደሆነ ነው እንጅ በፍጹም የሰው ፍጥረት አይመስሉኝም፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር ምንም ፍንክች የማያደርጋቸው!!!
እኔ ማመን ነው ያቃተኝ! እንዳልኳቹህ ካለፈው ሁሉ አሳዛኝ ኪሳራዎቻችን በተጨማሪ ይህ የዐቢይ ጫናና ግፊት ተጨምሮበት ነገሩን ሰዋዊ በሆነ ስሌት አስልቸው ተስፈኛ አድርጎኝ ነበረ፡፡ ይሄ ሁኔታ ግን ሰዋዊ ባለመሆኑ ግምቴ ከሸፈና ዐቢይ አስመራ ሔዶ በእራት ግብዣ ላይ ከተናገረው በመነሣት በጻፍኩት ጽሑፍ ላይና ከዚያም ቀደም በጻፍኳቸው ጽሑፎች የጠቀስኩላቹህ አደጋዎች የሚደርሱ ለመሆኑ ቁልጭ ብሎ ሊታይ ችሏል፡፡
ከነ ኢሳይያስ ጋር በግጭት ላይ መክረማችን ያከሰረው ኤርትራን ብቻ አይደለም፡፡ እነ አቶ ኢሳይያስ በኦጋዴን ነጻ አውጭና በኦነግም በኩል እጃቸውን በማስገባታቸውና በሀገሪቱ መረጋጋት በመጥፋቱ የውጭ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን አርቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ግጭቱ ከነሱ በባሰ መልኩ በኢኮኖሚውም በፖለቲካውም (በምጣኔ ሀብቱም በእምነተ አሥተዳደሩም) እኛንም ከባድ ኪሳራ ላይ ጥሎን ቆይቷል፡፡
የሚያሳዝነው ነገር ከነ ኢሳይያስ ጋር ስምምነት መፈጠሩም እንደዚያው ሀገሪቱን በኢኮኖሚው እና በፖለቲካውም አሁንም ለከባድ ኪሳራ የሚዳርግ  መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢኮኖሚውን ተጠቃሚነት በሚፈልጉት መልኩ ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ በሀገራችን ፖለቲካ ላይም ስውር እጃቸውን ማስገባታቸው አይቀርምና ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይም ለአማራ ሕዝብ አደገኛ ሁኔታን ነው ይዞ የሚመጣው፡፡ ኢሳይያስ በተጠበቀው ንግግሩ ላይ “በማወቅም ባለማወቅም ለጠፋው ጥፋት ሁሉ ይቅርታ!” አለማለቱ ወይም ለማለት አለመፈለጉ ጨርሶ አለመለወጡን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ሸአቢያ በማወቅም ባለማወቅም ስሕተት መፈጸሙን እያወቀ “በማወቅም ባለማወቅም ለፈጸምነው ስሕተት ይቅርታ!” ቢል ሠማዕታት በሚላቸው በትግሉ ወቅት በተሠው ወገኖቹ ላይ ክህደት የፈጸመ ነው የሚመስለው፡፡ በመሆኑም ስሕተት እንደፈጸሙና የትግላቸው ውጤት እንዳልጠቀማቸው ቢያውቁም መለወጥ አይፈልጉም፡፡ የሰው ልጆች የመግባቢያ ደንቦች (code of conducts) የሆኑት የሞራል (የቅስም) ድንጋጌዎች፣ ፍትሕና አመክንዮ ሸአቢያ ላይ ጨርሶ አይሠሩም፡፡ ከሸአቢያ ጋር መግባባት የሚቻለው ምንም ይሁን ምን እሱ የሚፈልገውን በማድረግ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ሸአቢያ ማለት ቀላል ባለጋራ እንዳይመስላቹህ!!! የኛ ነገር “ከእሾህ ጋር የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል!” እንደተባለው ነው፡፡ ይሄንን ውስብስብ ችግር መፍታት ለእግዚአብሔር ካልሆነ ለሰው የሚቻል አይመስለኝም፡፡
እውነቴን ነው የምላቹህ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ እነ ዐቢይ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው ሊሰጡ ካልሆነ በስተቀር እንዴትም ብለው በምንም ተአምር ቢሆን በንግድ ላይ እንደሚጠበቀው ፍትሐዊና ዕኩል ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ከእነ ኢሳይያስ ጋር ፈጽሞ ሊስማሙ እንደማይችሉ በእርግጠኝነት ልነግራቹህ እችላለሁ፡፡ በመሆኑም ጣጣችን ገና ገና ገና ብዙ ነው፡፡
እነ ዐቢይ “የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም!” ካሉ ደግሞ ወደነበርንበት ግጭት መግባታችን አይቀሬ መሆኑን ልነግራቹህ እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን ወያኔ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ተነሥቶብኛልና ሸአቢያን ከጎኔ ላሰልፍ!” ብሎ ካሰበ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ይስማማ ይሆናል፡፡ እነ ኢሳይያስም ወይ ፍንክች!!! ያሉበት ምክንያት “ወያኔ እኔን ከጎን ማሰለፍ ስለሚፈልግ የሀገሪቱን ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት ውጭ አማራጭ የለውም!” ከሚል ሒሳብ ይመስለኛል፡፡ የልዑካን ቡድን ወደ ሀገራችን ሊመጣ ሲል በጃፓን ሀገር የኤርትራ አንባሳደር (እንደራሴ) ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የሚደረገው ለውጥ ሕወሓትን ያገለለ መሆን የለበትም!” ሲሉ ፈርጠም ብለው ማሳሰባቸው ከምንም ነገር በላይ የሕወሓት መኖርን ሸአቢያ ምን ያህል እንደሚፈልገው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ እና የባሕረ ምድር (ኤርትራ) ሕዝብ በታላቅ የመነፋፈቅ ስሜት አንድነትን እየፈለገ በእነኝህ ደንቀራዎች ምክንያት አንድ ሊሆን አለመቻሉ በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡ ሥልጣን የሕዝብ በልሆነበት ሀገር የፖለቲከኞች እንጅ የሕዝብ ፍላጎት ተፈጻሚ አይሆንም አይጠበቅም፡፡
የቆየው የወያኔና የሸአቢያ ግጭት ለኢትዮጵያ አንድ ዕድል ፈጥሮላት ነበረ፡፡ ወያኔ ያለአግባብ ለሸአቢያ የሰጠውን አሰብን ያለአግባብ መሰጠት አንሥተን ምንም ዓይነት ጦርነት መቀስቀስ ሳያስፈልገን መረጃዎችን ብቻ ለገላጋይ ፍርድ ቤቱ በማቅረብ ንብረታችንን ማስመለስ የምንችልበትን ዕድል ነበር፡፡ አሁንም በግጭት እስካለን ጊዜ ድረስ ክሱን የመቀስቀስና አሰብን የማስመለስ ዕድሉ ነበረ፡፡ ነገርግን ሥልጣን ላይ ያለው ክሕደቱን በመፈጸም ንብረታችንን የሰጠብን ወያኔ በመሆኑ ይሄንን ሊያደርግ አልቻለም፡፡
ነገር ግን ወያኔዎች “እኛ ሳናውቅና ሳንመክርበት ነው መለስ በግሉ ወስኖ አሰብን ለሸአቢያ የሰጠው!” ይላሉና ይሄ የሚሉት ነገር እውነት ከሆነና ውሳኔው የመለስ የብቻው ከነበረ ከመለስ ሞት በኋላ ጥያቄውን አንሥተው አሰብን የማስመለስ ሒደት ለመቀስቀስ ከሸአቢያ ጋር ግጭት ላይ መሆናችን ምቹ አጋጣሚ ነበረ ሊያደርጉት ግን አልቻሉም፡፡ አሁን ደግሞ ስምምነት ላይ ከደረሱ የመለስን የክህደት ውሳኔ በዚያው እንዲጸና ማድረግ ነውና የሚሆነው ስምምነት ከደረሱ ዕድሉ መክኖ መቅረቱ ነው፡፡ አሰብ የኢትዮጵያ ስለመሆኑ በሚቀጥለው ጊዜ እጽፋለሁ፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! እባክህን በደል መተላለፋችንን ይቅር በልልንና በምሕረት ተመለስልን??? ይቅር በቃ በቃቹህ በለን??? አሜን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic