>

ለዶ/ር አብይ የምንሰጠው ወደ አምልኮ የተጠጋ ፍቅር ባለውለታዎችን በማንኳሰስ አይገለጽ!!! (መሳይ መኮንን)

ለዶ/ር አብይ የምንሰጠው ወደ አምልኮ የተጠጋ ፍቅር ባለውለታዎችን በማንኳሰስ አይገለጽ!!!
መሳይ መኮንን 
አልገባኝም:: ቴዲ ምን አደረገ? ይፋዊ ግብዣ ያልተደረገለት: ከ15ሰዓታት በላይ በረራ አድርጎ ትላንት ምሽት የገባ ሰው: ከባንድ ጋር ለሰከንድ እንኳን ያልተናበበ ድምፃዊ ከዚህ በላይ ምን ያደርግ ዘንድ ጠብቀን ኖሯል?!
ለዶ/ር አብይ ከአምልኮ የተጠጋ ፍቅር ውስጥ የወደቅን አንዳንዶች እየሰጠን ያለው አስተያየት ለትዝብት የሚያጋልጥ ነው::
ሳይጋበዝ እንደተገኘ ሰምቼአለሁ:: ለዶ/ር አብይ አክብሮት ሲል ያደረገው ይመስለኛል:: አልተዘጋጀም:: አልተለማመደም:: ለህዝብና ለመሪው ክብር ሲል ያን ያህል ሞክሯል:: በቂ ላይሆን ይችላል:: እንዲህ የውግዘት መዓት ማውረድ ግን መርህ የሌለው ነገር ነው:: አዲስ ከመጣ ባለውለታ ጋር ጭልጥ ብሎ የመክነፍና ሌላውን የማኮሰስ አባዜ ለሀገር አይበጅም::
አንዳንዶቻችን ለዶ/ር አብይ የሰጠነው የተትረፈረፈ ፍቅር የሌሎች ባለውለታዎቻችን ዋጋ በማርከስ ጭምር እየገለፅን ነው :: ዶ/ር አብይ ከአያሌ ኢትዮጵያውያን በዱላ ቅብብሎሽ የመጣውን ትግል ወደ ውጤት በመቀየራቸው ባለውለታ ሆነዋል::
– ታማኝ በየመድረኩ የጮሀለትን:
 – ቴዲ አፍሮ በሙዚቃዎቹ ያስተጋባውን:
– ብዙዎች በየተሰለፉበት ዘርፍ ዋጋ የከፈሉበትን ኢትዮጵያዊነትን የፖለቲካ ስልጣኑን በያዙት ዶ/ር አብይ አማካኝነት ለፍሬ በቅቷል::
ዛሬ ድንገት ተነስተን የትላንቱን አጣፍተን: ባለውለታዎቻችንን አርክሰን በአንዲት የመድረክ ትዕይንት ያውም ጥፋት በሌለበት ሁኔታ የስድብና እርግማን ናዳ ማውረድ በእውነት ያሳፍራል::
ነገ ዶ/ር አብይ ትንሽ ሸርተት ቢሉ ተመሳሳይ ውርጅብኝ ከማዝነብ የማንመለስ ለመሆኑ አመላካች ነው::
የምንሰጠው ፍቅር ልክ ይኑረው:: ወደ አምልኮ እንዳይቀየር እንጠንቀቅ:: ሳያመልኩ መደመር ይቻላል:: ዶ/ር አብይ ፍፁም አይደሉም:: ስጋ ለባሽ ናቸውና ስህተት ሊሰሩ ይችላሉ:: ቴዲም እንደዚያው:: መደመር ማለት በዶ/ር አብይ ቁመትና ልክ የተሰፋውን ዝም ብሎ ማጥለቅ ማለት አይደለም:: ዓይነቱ ከታወቀ በልካችን አድርገን ከለውጡ ጋር አብሮ መሄድ ይመስለኛል:: የእሳቸውም የመደመር ስሌት የእኔን እንዳለ ሳታላምጡ ዋጡ አይደለም::ያለንን: ልካችንን ጠብቀን ለለውጡ አስተዋፅኦ እናድርግ ነው::
ፍቅራችን ማስተዋልን እንዳይጋርድብን መጠንቀቅ ይገባል:: የእስከዛሬዎቹን ባለውለታዎች በማራከስ ለዶ/ር አብይ የሚጨምር ፍቅር ጤናማ አይሆንም:: ሁለቱም አንድ ናቸው:: ዶ/ር አብይና ቴዲ አፍሮ ግባቸው አንድ ነው:: ህልማቸው ተመሳሳይ ነው:: ኢትዮጵያዊነት:: ሁለቱን ማወዳደሩ የደካሞች ቁማር ናት:: በየተሰለፉበት መድረክ ለኢትዮጵያ እያገለገሏት ናቸው:: አዲስ ለመጣ ባለውለታ ብለን የነበሩንን ማጣጣል ለኢትዮጵያ አይበጅም::
Filed in: Amharic