>

የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሰራዊትን ማዛዝ በኦሮሚያና ሶማሊ አዋሳኝ አከባቢዎች ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም!

by Mengistu D. Assefa

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች የሚታዩ ግጭቶችን አስመልክተው የሰጡት መግለጫ እና እሱን ተከትለው ያስተላለፉት ትዕዛዝ የጸጥታ ችግሮቹን ሁሉ በአንድ ዓይን የማየት፣ ተራ የብሄር ግጭት ወይም ደግሞ ትንሽ ቡድን የሚመራው ችግር አድርጎ የማየት ነገር አለበት።

በተለይ የኢትዮ ሶማሌና የኦሮሚያ አዋሳኝ ቦታዎች የሚታየው ችግር ሲጀምር ፌዴራል ፖሊስም ሆነ መከላከያ የሚያስቆመው ጉዳይ አይደለም። ይህ ሊሰመርበት ይገባል። ከዚህ በፊት የተሞከረ እና ያልሠራ ነገር ነው፤ አዲስ ነገር የለምና። ችግሩ የሶማሊ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ግጭት አይደለም።

ይባሱኑ መከላከያው ጣጣ ውስጥ እንዳይገባ። ምክንያቱም ከሁለት ቀናት በፊት ይህ የሶማሌ ልዩ ኃይል መከላከያው ላይ ተኩሶ ሲገድል ነበር። ቢያንስ አንድ የመከላከያ ሠራዉት አባል እና ሦስት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትን እንደገደለ መንግሥት ራሱ ያመነው ነገር ነው። አሁንም ከዚህ ኃይል ጀርባ ያሉ እጆች ንጹሃንን እና መከላከያው ላይ ተኩስ እንደማያስከፍቱ ምንም ማረጋገጫ የለም። ያ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ኪሳራ ነው። ዜሮ ድምር ፖለቲካ ነው ሚኾነው ትርፉ። ይልቁንም ችግሩ ላይ ትኩረት ተድርጎ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል።

ችግሩ ምንደን ነው?

እዚህ ሀገር ውስጥ ሥውር የመንግሥት (deep state) አለ። ይህ deep state ደግሞ መከላከያውን እና የደኅንነቱን መዋቅር ተጠቅሞ ነው ሕዝብ ላይ ጦርነት የከፈተው። ችርሩ የሶማሌ ልዩ ኃይል ነው …የሱ አዛዥ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አዲስ አበባ ላይ ይንሸራሸራል…ሲያሻው ጸሎት ይመራል። በቃ ይሄ ነው ችግሩ።

ሌላው በጣም የሚያሳዝነው ነገር ጠቅላይ ሚኑስትሩ ችግሩን externalize ለማድረግ መሞከራቸው ነው። አርቲስቶች፣ አክቲቪስቶች እና የሚዲያ ሰዎች ችግሩን እንዳራገቡት አድርጎ ማቅረብ። ይህ በራሱ ችግር ነው። ማንም ከዚህ ግጭት ለመጠቀም ያረገበው አካል አለ ብየ አላስብም። ካለ ደግሞ እሱን በሕግ መጠየቅ ነው እንጅ ጅምላ ፍረጃ የትም አያደርስም።
እኔ አሁንም ደግሜ እላለሁ፦

አይደለም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ችግሩ የመንግሥትህ ችግር ነው። መንግሥትህ ውስጥ የመረቀዙ፣ ጥቅም ፈላጊ ነፍሰ ነላዎች አሉ። እርስዎ ወደ ሥልጣን ከወጡ እንኳን ከ350 በላይ ሰዎች ሙተዋል። አካል ያጡ ብዙ ናቸው። ይህንን መንግሥት ያስቁም ማለት ግዴታ ነው። የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደኅንነት እና ሰላም መጠበቅ ነው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን አቅልለው ከማየት፣ መንሥኤውን ሳይነኩት መከላከያና ፌዴራል ፖሊስን ማዘዛቸው መፍትሔ እንደማያመጣ አሳምረው ይረዱታል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ። የታሪክ ተወቃሽ የሚኾነው የዚህን ችግር ክብደት ተረድቶ መፍትሄ የሚሻ አካል ሳይሆን ነቀርሳውን ከመንቀል ማስታገሻ የሚሰጠው የኢፌዴሪ መንግሥት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር …በገለሰብ ደግሞ ጠቅላይ ሚኑስትሩ ናቸው። በቃ ይኻው ነው።
ከ 4 ቀናት በፊት የመፍትሄ ሃሣብ ይሆናል ብዬ ያስቀመጥኳቸውን 3 ነጥቦች ደግሜ እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ።

  • ፩. አብዲ ሙሐመድ ዑመርን ጨምሮ ሌሎች ከሱ ጋር ጥፋት ሲፈጽሙ የኖሩት ግለሰቦች እና የልዩ ኃይሉ አመራሮች በሕግ መጠየቅ አለባቸው። ይቅርታ ብሎ ነገር የለም። Fallacy of Appeal to emotion እየተጠቀሙ deliberately ለረጅም ዓመታት ከፈጸሙት ጥፋት ማምለጥ ሌላን ጅል ማድረግ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ላጠፉት የሰው ሕይወት ክብር ማጣት ነው።
  • ፪. የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ቶሎ ትጥቅ ፈትቶ መበተን እና በሕዝባዊ ፖሊስ መተካት አለበት። የሶማሎን clan dynamics ማኒፑሌት በማድረግ የክልሉን ፖለቲካል ኢኮኖሚ አዘቅት ከመክተት ባለፈ ከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸመ ነውና።
  • ፫. ሶማሌ ክልል ፖለቲካው ለመሃል ሃገር ሰው አይገባም። ባሕሉም ሆነ የጎሳ ሥርዓቱ (clan dynamics) ሶማሌ ብቻ ነው የሚረዳው። እስካሁን ኢሕአዴግ ኢሶዴፓ’ን አጋር ድርጅት አድርጎ ሲያስቀምጥ ይህንን complex clan dynamics and unique cultural values ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም።

አሁን በድኅረ-አብዲ ኢሌ ከክልሉ ምሁራን እና ፓርቲዎች (በቅርቡ ከአሸባሪነት ዝርዝር የተፋቀውን ኦብነግን ጨምሮ መለት ነው) ጋር ይህንን ግንዛቤ በመውሰድ (descriptively) እንዲሁም ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ፖለቲካል ፖሊሲ መቅረጽ (normatively accommodative policy) ያስፈልጋል። ለዚህም ድርድርና ምክክር ያስፈልጋል። አለዚያ ሕዝቡም ዴሞክራሲያዊ አመራርም አያገኝም፤ በሁለተኛ ደረጅ ደግሞ በኢኮኖሚም ሆነ በጽጥታ እስትራቴጂክ ክልል መኾኑም (ነዳጁን እና አልሸባብን ልብ ይሏል) መገንዘብ ያስፈልጋል።

ተጨማሪ ነገሮች ስልጉዳዩ ለማንበብ ይህን ማስፈንጠሪያ የጠቀሙ…..ይጫኑ

Filed in: Amharic