>

የትናንት ምሽቱ ኮንሰርትና የቴዲ አፍሮ እውነታዎች - ”ወደ መድረክ ጋብዞ የጀርባ በር ቆልፎ” (ያሬድ ሹመቴ)

የትናንት ምሽቱ ኮንሰርትና የቴዲ አፍሮ እውነታዎች
– ”ወደ መድረክ ጋብዞ የጀርባ በር ቆልፎ”
ያሬድ ሹመቴ

በትናንትናው ምሽት በኢትዮጵያና ኤርትራ የሰለም ኮንሰርት ላይ በእንግድነት ዝግጅቱን እንዲታደም ተጋብዞ የነበረው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን በርከት ያሉ የተዛቡ መረጃዎች እየቀረቡበት ነው።

ከነዚህም መካከል ሙዚቃዎቹን በብዛት አለማቅረቡና ወደ መድረክ እንዲወጣ ከተጋበዘ በኋላ ‘ታዳሚውን ለብዙ ደቂቃዎች አስጠብቋል’ የሚሉት ዋናዎቹ ሲሆን በእለቱ በስፍራው አብሬ በመኖሬ ትክክለኛውን መረጃ በአጭሩ እነሆ።

• ቴዲ አፍሮ የዝግጅቱን መግቢያው ካርድ ያገኘው ዝግጅቱ መካሄድ ከጀመረ በኋላ ነው።

• የመግቢያ የይለፍ ወረቀቱን አትላስ አካባቢ ያስቀመጡልን የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ሀላፊው አቶ ፍፁም አረጋ ፍፁም ተባባሪ ሆነው አምሽተዋል።

• መግቢያ ካርዱ ከተገኘ በኋላ ሚሊንየም አዳራሽ ስንደርስ ለረዥም ደቂቃዎች እንዳንገባ ተከልክለናል።

• ተፈቅዶልን ግቢ ውስጥ ከገባን በኋላ ወደ አዳራሹ ለመግባት ቢያንስ ከ15 ደቂቃ በላይ መግቢያው ላይ እንድንቆም ተደርጓል።

• ወደ ክብር እንግዶች ማረፍያ ከገባን በኋላም ወንበር እስኪዘጋጅ ጠብቁ ተብለን በድጋሚ ለመጠበቅ ተገደናል።

• ወ/ሮ ዝናሽ (ቀዳማዊት እመቤት) እንደገባን በፈገግታ ለቴዲ እጃቸውን እያውለበለቡ ሰላምታ በመስጠታቸው እሱም በአክብሮት አፀፋውን መልሷል።

• የተዘጋጀልን የመቀመቻ ስፍራ ወደ ታዳሚው የተጠጋ በመሆኑና በስክሪን ቴዲ በመታየቱ ቴዲ ተነስቶ ለህዝቡ ሰላምታ ሰጥቶ ተቀምጧል።

•ህዝቡ በተደጋጋሚ እንዲዘፍን ስለጠየቀ ቴዲ ፍቃደኛ መሆኑን ተናግሮ ወደ መድረኩ ለመሔድ ተነሳን።

• መድረክ መሪው የቴዲን ፍቃደኝነት ከሰማ በኋላ እንደ አዲስ ልምምጥ በሚመስል መንገድ ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉ አስገራሚ ነበር።

• ቴዲ ዶ/ር አብይን ሰላም ብዬው ልሂድ ብሎ ሁለት ግዜ ጠይቆ የፌደራል ፖሊስ ዋና አዛዡ አቶ ዘይኑ ቢፈቅዱም የፕሮቶኮሉ ሹም ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ለሰላምታ ሳይፈቀድ ቀርቷል።

• አዳራሹን ዙረን ባክ ስቴጅ ላይ ስንደርስ የጀርባው በር ተቆልፎ ጠበቀን።

• በቦታው የነበሩ ሰዎች ለማስከፈት ቢሞክሩም በሩን የዘጋው ሰው አልከፍትም ብሎ ብዙ ቆመናል። ለጀርባው መግቢያ አማርጭ ናቸው የተባሉ ሌሎች ሶስት በሮችንም እየተዘዋወርን ለመግባት ብንሞክር የሚቻል አልሆነም።

• የብሄራዊ ትያትር ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ባዬ “ላስቸግራችሁ በህዝቡ መሀል ይዛችሁት ኑ?” ብለው ሀሳብ በማቅረባቸው፤ ከመድረኩ በስተቀኝ በኩል በህዝብ መሀል ይዘነው ለመግባት ተገደናል።

• በቂ ጥበቃ ባለመኖሩ የከበበውን ህዝብ አልፎ ወደ መድረኩ ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ ፈተና ሆኖብን ነበር።

• በመከራ በህዝብ መሀል አልፈን ከመድረክ ጀርባ ብንደርስም እዚያም የነበሩ የቴዲ አድናቂዎች አላሳልፍ ብለው ግርግር ተፈጥሮ ነበር።

• የመድረክ መሪው ግሩም ጫላ በተደጋጋሚ ቴዲን የሚያሳጣ ጥሪ ሲያደርግ እኛ ግን ቴዲን ይዘን ለመድረስ ከባድ ፈተና ላይ ነበርን። ቴዲ የለበሰው ልብስ እስኪጨማደድ ድረስ ግፊያውንን ተቋቁሞ ወደ መድረኩ ደርሷል።

• ሙዚቀኞቹ በመድረክ መሪው ጋባዥነት “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን የቴዲን ዜማ ያለ እሱ ፍቃድ መጫወት ሲጀምሩ በቦታው ደርሰናል።

• ባንዱ እየተጫወተ የነበረውን ሙዚቃ አቋረጠ። መድረክ መሪው የቴዲን ስም ጠርቶ ወደ መድረኩ ሲጠራው ቴዲ መድረክ ላይ ወጣ።

• መድረክ ላይ ከህዝቡ የተወረወረለት ኮከብ አልባ ሰንደቅ አላማ በሴኪዩሪቲ በፍጥነት እንዲነሳ ተደርጓል።

• አንዲት እናት ያዘጋጁለትን ስጦታ መድረክ ላይ ሊሰጡት እያለቀሱ መጡ ስጦታውን እንደተቀበለ ለህዝቡ የስንብት ሰላምታ ሰጥቶ ወደ ጀርባ ገባ።

• ቀደም ብሎ የተቆልፈብንን በር ለመውጣት ሲሆን ከፈቱልንና በጀርባ በኩል ወጣን።

ይህ ሁሉ ሲሆን ቴዲ አፍሮ ግን ባልተዘጋጀበት መድረክ ከዚህ በፊት ገጥሞት የማያውቅ ውክቢያ ደርሶበት፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማክበር ሲል ራሱን በማረጋጋት መልዕክቱን አስተላልፎ፤ ፊዮሪናን ዜማ ተጫውቶ ዛሬም የህዝብ ልጅነቱን አስመስክሯል።

Filed in: Amharic