>
5:28 pm - Saturday October 10, 2916

ሲውጥ ይመርቅ መሆን ነውር ነው!!! (ደረጄ ደስታ)

ሲውጥ ይመርቅ መሆን ነውር ነው!!!
ደረጄ ደስታ
ሀገር አቀፍ ጀግንነትን አንዴ እንኳን ለመፈፀም መታደልን ይጠይቃል፡፡ ሁለቴ፣ ሶስቴ ለመደጋገም ደግሞ እንዲሁ ተደጋጋሚ ልዩ ተሰጥኦንና ልዩ መታደልን ያስፈልጋል፡፡ ቴዲ በተደጋጋሚ በወጥነትና ለአመታት ጀግንነትን ፈፅሟል፡፡ ቴዲ ግፈኛውን ሥርዓት በግንባር ቀደምትነት በጥበብ ተፋልሟል፣ በፍቅር ስብከቱ ጠማሞችን ተገዳድሯል፡፡ የኢትዮጵያዊነት ፍም ስሜት ተዳፍኖ እንዳይቀር በየደረሰበት በተሰጥኦው እስትንፋስ አቀጣጥሎታል፡፡ 
 
ከማንም በፊትና በላይ የኤርትራና የኢትዮጵያ ጉዳይ ተበጥሶ ወይም ተረስቶ እንዳይቀር በኪነጥበባዊ ድሩ አያይዞ ኖሯል፡፡ ቀልድ ቢመስልም፣ የኢትዮጽያና የኤርትራ ጉዳይ በፍቅር ብቻ ይፈታል ብሎ ያለመታከት ከማንም በፊት የሰበከው፣ ያለመው፣ ያስተጋባው ቴዲያችን ነው፡፡
 
ከሀገር ውጭ በከወነባቸው መድረኮች ሁሉ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያንን እጅ ለእጅ አያይዞ በፍቅር አስተቃቅፏል፡፡ ፍቅር ያሸንፋል በሚለው መርኁ ተነሳስቶ እንደ አውሬ ይቆጠር ወደነበረው የሻዕቢያ አስተዳደር ዘልቆ በመግባት፤ ለኤርትራዊያን የሙዚቃ ሥራውንና የፍቅር ቅስቀሳውን ለማቅረብ በተለያዩ ጊዜያት ሲሞክር መኖሩን ስንሰማ ኖረናል፡፡ 
 
ቴዲ በሳንቲም የማይደለል፣ በዝና የማይንቦጣረር፣ በወንበዴዎች ጉልበት የማይበገር፣ መቼም የትም ሀገሩንና ሕዝቧን ብቻ የሚያስቀድም በልዕለ-ህሊና የሚመራ የትውልዳችን ጀግና ነው፡፡ በተንኮለኞች ጠማማ ታሪክ በመወናበድ፣ ቀጥ ያለ መስመሩን አወላውሎ በጎሰኝነት ወጥመድ ውስጥ ወድቆ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ሰው ነው፡፡
 
የጠ/ሚ አብይ የሠላምና የፍቅር የመደመር መርኅ ዕድልና መድረክ አግኝቶ እንዲህ በሀገራችን ላይ መናኘት ከመጀመሩ በፊት፤ እንደ ቴዲ ፍቅር ያሸንፋልን እየዘመረ የክፉዎች አስተሳሰብ ላይ ውኃ ሲቸልስና የጠማሞችን ሀሳብ ቅስም ሲሰብር የኖረ ብቁ ሰው መኖሩን ማስታወስ ይከብዳል፡፡ ቴዲ በሚሊኒየም አዳራሹ መድረክ የተገኘው ለመታደም እንጂ ለመዝፈን አልነበረም፡፡ ስለሆነም በሕዝብ ጥያቄ መድረክ ላይ ወጣ በተጓጓው መጠን ሥራውን ሳያቀርብ ቀረ፡፡ አለቀ፡፡ 
 
ስህተት ቢፈፅም እንኳን ቴዲን ለመታገስ ከበቂ በላይ እጅግ አይረሴ እና አይነኬ ገድሎችን የታደለ የምን ጊዜም የትውልዳችንና የኢትዮጵያ ጀግና ነው፡፡ እንከን ፈልጎ ሰውን ያውም ጀግናን ሰው ለመዘርጠጥ መሞከር፣ ሀገር አያፀናም፡፡ የጋራ ጀግና የሌላት ሀገር የጋራ ዕሴት፣ የጋራ አስተሳሳሪ ራዕይ እንዳይኖራት ያደርጋልና፡፡ ይኼ ድርጊት ካልታረመ፣ ዛሬ ላይ በነገረ ሥራቸው እየደገፍናቸው የምንገኘውን ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ላይ ነገ አንዲት እንከን የተገኘች ጊዜ ይኼንኑ የዝርጠጣ ጦራችንን ላለመስበቃችን ምንም ምክንያት አይኖረንም፡፡ 
 
ትላንትን ከትላንት ወዲያን በመርሳት በዕለት እና በቅፅበት ድርጊቶች ላይ ብቻ በመወሰን፣ የሰዎችን ገድልና ተግባር ማወደስም ሆነ መዘርጠጥ፤ ማመዛዘን ያለመቻል ቀሽምነት ነው፡፡ በዕለታዊ ተግባር ብቻ ነገሮችን የሚያወድስም ሆነ የሚኮንን ሰው፣ ሲውጥ ይመርቅ ይባላል፡፡ ሲርበው ደግመው ካላጎረሱት፣ የቅድሙን የትላንቱን ውለታ የሚረሳና የሚሳደብ የማስታወስ ልምሻ ተጠቂ መሆን ደግሞ ሀገራዊ መግባባትን ያፈርሳል፡፡ ይታሰብበት፡
Filed in: Amharic