(የአ.ግ. ሰ ልዩ ርዕሰ አንቀጽ)
በርካታ ኢትዮጵያዊያን “በአገራችን የለውጥ ጭላንጭል መታየት ጀምሯል” የሚል ተስፋ በሰነቁበት በአሁኑ ወቅት ይህን ተስፋ ለማጨለም ታጥቀው የተነሱ ኃይሎች መኖራቸው ገሀድ ሆኗል። ለ27 ዓመታት በጉልበት ከያዙት ስልጣን ትንሽንም እንኳን መገፋት የማይፈልጉ ፀረ – ለውጥ ኃይሎች የተለያዩ እንቅፋቶችን እየፈጠሩ ነው። በዚህም ምክንያት በአንድ በኩል ተስፋ ሰጪ ዜናዎችን ስንሰማ በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎች ለዘመናት ኖረው፣ ሠርተው ሀብት ካፈሩበት፣ ወልደው ካሳደጉበት ቀዬ “አገራችሁ አይደለም ውጡ” እየተባሉ ነው። አማራ አርሶ አደሮች ከቤንሻንጉል፣ ከኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጽያ ክልሎች መፈናቀላቸው ቀጥሏል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦሮሞ ወገኖቻችን ከሶማሊ ክልል ተፈናቅለው እስካሁን የረባ መጠለያ አላገኙም፤ እንዲያውም መፈናቀሉ አሁንም እንደቀጠለ ነው። በጉጂ ዞን በሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ዘርን ማዕከል ያደረገ ግጭት አላባራም። በጋምቤላ ያለው ውጥረትም አልበረደም። በመላዉ ኢትዮጵያ ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በማርገብ ፋንታ እየተራገቡ እንዲባባሱ እየተደረገ ነው።
በወልቂጤ ከተማ በእግር ኳስ ጨዋታ ሰበብ በጉራጌና በቀቤና ማኅበረሰቦች መካከል በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ብዙዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ግጭቱ አሁን እንደቀጠለ ነው። በሀዋሳ ከተማ በባህላዊ በዓል ሰበብ የተነሳው ግጭት ሥርዓት አልባ ወደሆነ ዘረፋ ተሸጋግሮ በዜጎች ንብረት ላይ አደጋ ደርሷል። በሀዋሳም ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል። በባህርዳር ተማሪዎች በአገዛዙ ታጣቂዎች እየተደበደቡ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ብ/ብ/ ሕዝቦች፣ የሀረሪ፣ የጋምቤላ፣ የሶማሊ እና የቤንሻንጉልና ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥታት እንዲሁም በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ያሉ የኢህአዴግ አባል ወይም አጋር ድርጅቶች በየአካባቢያቸው ለሚፈጠሩ ማኅበራዊ ግጭቶች መፍትሄ በመስጠት ፋንታ የችግሩ ቆስቋሽ መሆናቸው ገሀድ እየሆነ መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። እነዚህን ደካማ ክልላዊ መንግሥታትን እና ደካማ ድርጅቶችን ለእኩይ ዓላማ የሚጠቀም ኃይል ማን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ምርምር የሚፈልግ ጉዳይ አይደለም።
ትላንት ይፋ የሆነው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ማን ከእነዚህ ግጭቶች ጀርባ እንዳለ አመላካች ነው። በለውጡ ሂደት የተከፋው የኢህአዴግ ኋላ ቀር ስብስብ በየቦታው ተባባሪ ፀረ-ለውጥ ኃይሎችን እየመለመለና እያደራጀ እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው። ይህ የኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ ስብስብ ዋነኛ ምሽጉን የተከለው ህወሓት ውስጥ መሆኑ መግለጫው በግልጽ ያሳያል። የኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ ቡድን በህወሓት ውስጥ ጎልቶ ይታይ እንጂ በሌሎችም የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ተሰግስጎ የሚገኝ ነው። ይህ ስብስብ የለውጡን ሂደት እየመራ ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አስተዳደርን በችግር ላይ ጥሎ ቀድሞ ወደ ነበረው ሁሉንም ጠቅላይ አምባገነናዊ አገዛዝ ለመመለስ እንዲያመቸው ኢትዮጵያን በዘር አቧድኖ ለማፋጀት ቆርጦ ተነስቷል።
የዚህ ፀረ-ለውጥ ኃይል አገር አፍራሽ ተግባራትን ለማስቆም ምን መደረግ ይኖርበታል?
በአርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ እምነት በአገራችን ለሚከሰቱ ማኅበራዊ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት ለ27 ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የፓለቲካና የአስተዳደር ሥርዓት ነው። ስለሆነም ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚገኘው ስር ነቀል የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ በማድረግ ነው።
ስለሆነም አርበኞች ግንቦት 7 በኢትዮጵያ ውስጥ መሠረታዊ የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ ማስጀመር፤ ማለትም ዲሞክራሲያዊ የሕዝብ አስተዳደር ማስፈን ለችግሮቻችን ሁሉ ቁልፍ መፍትሄ ነው ብሎ ያምናል። በዚህም መሠረት የለውጥ ኃይሎች በሙሉ በለውጡ በቁርጠኝነት እንዲገፉበት ያበረታታል፣ ለትግል ያደራጃል፣ እየታገለ ያታግላል። በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ኃይሎች ኅብረታቸውን እንዲያጠነክሩ፤ በተለይም በህወሓት ውስጥ ያሉ የለውጥ ኃይሎችን አቅም እንዲያጎለብቱ ይመክራል፤ የፀረ-ሽብር ህጉንና እሱን ተከትሎ የመጡት ፍረጃዎችን በማንሳት የለውጡን ኃይል ደጋፊዎችን የማብዛት ሥራ እንዲሠሩ ያሳስባል።
አርበኞች ግንቦት 7፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የለውጡ ባለቤት መሆኑ ማረጋገጥ አለበት ብሎ ያምናል። በተለይ ወጣቶች በዚህ የለውጥ ወቅት በትልቅ ጥንቃቄና ብልሃት እንዲንቀሳቀሱ፤ ተደራጅተው ለመሠረታዊ የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ እንዲታገሉ አርበኞች ግንቦት 7 እገዛ ያደርጋል።
የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች በየአካቢያቸው ያሉ የለውጡ ተፃፃሪ የኢህአዴግ ወይም የአጋር ድርጅቶች ካድሬዎች ከያዟቸው ስልጣን እንዲወገዱ፤ የፓለቲካው ምህዳር እንዲሰፋ፤ ሁሉን ዓቀፍ ማኅበራዊ መግባባት እንዲጀመር እየታገሉ ማታገል ይኖርባቸዋል።
የአርበኞች ግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች በማኅበረሰቦች መካከል ያሉ አለግባባቶችን በማስታረቅ የኢትዮጵያ ሕዝብን ለጋራ ትግል ማነሳሳት፤ በማንኛውም ሰበብ ይምጣ የሕዝብ ለሕዝብ መቃቃር የሚጠቅመው የለውጡ ተፃፃሪ ኃይሎችን መሆኑ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ትኩረት በዚህ ላይ እንዲሆን ንቅናቄዓችን ያሳስባል።
የኢህአዴግ ፀረ-ለውጥ ኃይል የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ በሚያደርገው ጥረት የረዥም ጊዜ ተጎጂ ራሱ እንደሆነ መገንዘብ ይጠቅመዋል። ከእንግዲህ እንደቀድሞው ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ መግዛት አይቻልም፤ ከእግዲህ የሕዝብ ሀብት በግላጭ መዝረፍ አይቻልም። ይህን በጊዜ አለመገንዘብ ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፍላል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን የዜጎች ነፃነት የተረጋገጠባት፤ ፍትና እኩልነት የሰፈኑባት፤ የበለፀገች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትኖረን እንፈልጋለን። ይህንን ህልማችንን የሚያጨልምብን የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቾችን የሚቆሰቁሱ ኃይሎችን አንታገስም። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ በነፃነት መኖር ማየት ከምንፈልጋቸው መልካም ነገሮች ቀዳሚው ነው። ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሩ ባዕድ መደረግ የለበትም። እርስ በርሳችን የሚያጣሉንን ፀረ-ለውጥ ኃይሎችን አምርረን እንታገላለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓም