>

ዘመቻ ምሁርን ፍለጋ (ዳንኤል መኮንን)

ዘመቻ ምሁርን ፍለጋ 

ዳንኤል መኮንን

ቀጣይ ሳምንት ሰኞ ማለትም በሐምሌ 16 ወደ 4000 የሚጠጉ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተወጣጡ ምሁራን ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ያደርጋሉ፡፡ ይህ የምሁራኑና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት ለሀገሪቱ ምን ፋይዳ ይኖሯል የሚለውን ቆይተን የምናየው ቢሆንም  በዚህ ውይይት ላይ ምሁሩ ሀገሪቱ የተከናነበችውን ዲሪቶ ችግሮች የሚፈቱ የመፍትሄ አሳቦች ያቅርባል ብዬ አስባለው፡፡ ከአራቱ የአካዳሚክ ነጻነት ከሚባሉት መካከል አንዱ በሆነው “Extra Mural right‘’ አሳብ መሠረትም ምሁሩ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች አሳቡን የሚያቀርብብት መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡

ምሁር ማን ነው?

ምሁር ማን ነው በሚለው አሳብ ላይ ጸሐፊያኑ የተለያዩ አሳቦች ይነሳሉ፡፡ በግሪክ-ላቲን ስልጣኔ ዘመን የአንድ ግለሰብ ምሁርነት የሚለካው ግለሰቡ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ባለው ንቁ ተሳትፎ ነበር፡፡ ስለዚህ ማኛውም ምሁር የተባለ ግለሰብ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ (በተለይ በፖለቲካ) መሳተፍ እንደ ግዴታ ይታይ ነበር፡፡ የማህበረሰብ ሳይንቲስቱ ፍራንክ ፍሩድ “Where have all the intellectuals gone’’ በሚለው ጽሁፉ ምሁርነት አንድ ግለሰብ በተሰማራበት የስራ መስክ የሚገለጽ ሳይሆን ግለሰቡ በማህበረሰቡ ውስጥ ባለው ተሳትፎና እንቅስቃሴ፣ ለራሱ ባለው ግምትና አመለካከት እንዲሁም ባለው ማህበራዊና ፖለቲካዊ እሳቤ የሚገለጽ ነው ይላል፡፡ ጣሊያናዊው ኮሚዩኒስት አንቶኒዮ ግራምሼ ደግሞ “The prison notebook’’ በተሰኘው ስራው እንደሚጠቅሰው በማንኛውም ስራ የተሰማራና እውቀትን በማመንጨትና በማሰራጨት ስራ ውስጥ የተሰማራ ሁሉ ምሁር ነው በማለት ያብራራል፡፡ ለእነዚህ ጸሀፊያን የአንድ ሰው ምሁርነት የሚለካው በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ባለው ንቁ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ፈረንሳዊው ፈላስፋ ጄን ፓውል “Intellectuals is someone who meddles in what does not concern him’’ በማለት ምሁርነትን በማያገባውም (ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ) በመግባት ጉዳዩን የሚያይና መፍትሔ የሚያመጣ ግለሰብ ጋር ያያይዘዋል፡፡ለጆን ፓውል ምሁር ማለት የህብረተሰቡን ችግር (ምንም እንኳን እሱን ባያገባውም) ችግሩን ግን እንደ ራሱ ጉዳይ አይቶ የሚጋፈጥና ለመፍትሔም የሚሰራ ነው፡፡ ‘’Sociological Imagination‘’ በሚል ስራቸው ሚልስ ራይት እንደሚጠቅሱት ደግሞ በሚዲያ ምሁር የሚለው አሳብ የሚወክለው “የዩኒቨርስቲ ምሁራንን” ነው ይላሉ፡፡ የእነዚህ ምሁራን ዋና ስራም የህዝቡን ችግር መተንተንና መፍትሔ በማመንጨት ለፖሊሲ አውጪዎችና ለአስፈጻሚዎች በማቅረብ የህብረተሰቡን ችግር መፍታት ነው ይላሉ፡፡

በ19ኛው እና 20ኛው ክፍለ ዘመን ገናና በነበረው የካርል ማርክስ ፍልስፍና ውስጥ ምሁራን ትልቅ ቦታ ይዘው እናገኛለን፡፡ በማርክስ አሳብ ምሁራን ተራማጅ አሳቦችን የማመንጨት፣ ለፖለቲከኞች ምክረ አሳብን የማቅረብ፣ ለማህበረሰቡ የሀገሪቱን አጠቃላይ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በሳይንሳዊ መንገድ የመተንተን ፣ በተቻለ አቅምም ፖለቲካዊ አመራሩን የመጨበት ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ለካርል ማርክስ ምሁር ማለት በጥልቅ እሳቤ፣ በምርምርና ጥናት ተደግፎ የማህበረሰቡን ችግር የሚያይና መፍትሔውንም የሚፈልግ ነው፡፡ 20ኛው ክፍለ ዘመን “ምሁርነት” አውንታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በመያያዝ ከእውቀትና ልእቀት ጋር በመቆራኘቱ በማህበረሰቡም ክብርን ማግኛ መንገድ ሆኗል፡፡

ኢትዮጲያና ምሁራን

ምንም እንኳን  ዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን የአንድ ምዕተ አመት እድሜ ብቻ ያስቆጠረ ቢሆንም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ልሂቃን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ነበሩ፡፡ የአውሮፓ አይነት ትምህርት ወደ ኢትዮጲያ ከመግባቱ በፊት ሀገራችን የብዙ ምሁራንና ሊቃውንት ባለቤት ነበረች፡፡

ዘመናዊ ትምህርት በተዋወቀበት 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ወደ ስልጣን የመጡት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስልጣናቸውን ለማደላደልና የሸዋ መሳፍንትን ለማዳከም የተጠቀሙት በዘመኑ እያበቡ የነበሩትን ምሁራንን ነበር ፡፡ እነዚህ ምሁራን ንጉሱ ላለሙት ሀገሪቱንና ማህበረሰቡን የማዘመን ውጥን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በምሁራን እርዳታ ወደ ስልጣን የመጡት ንጉስ በተማሪዎችና ምሁራን ጥረት ስልጣናቸውን ሲነጠቁ መንበረ ስልጣኑን የተቆናጠጠው ወታደራዊው ደርግ በአብዮቱ መጀመሪያ አካባቢ ይበል የሚያሰኝ ኅብረት ከምሁራን ጋር ፈጥሮ ነበር፡፡  ቀን ቀንን ሲተካ ግን የደርግና ምሁራኑ ግንኙነት በመሻከሩ በስመ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር እስከ ዛሬ ለመተካት ያቃተንን ወጣትና ጎበዝ ምሁራኖችን አተናል፡፡

ዘመነ ኢህአዴግና ምሁራን

ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ ‘’Reflection on changing role of intellectuals in Ethiopian politics’’ በተሰኘው መጣጥፋቸው በደርግ ዘመን ከነበረው የምሁራን ነጻነት አሁን በዘመነ ኢህአዴግ ያለው የምሁራን ነጻነት የተሻለ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ የምትከተለው የብሔር ፖለቲካ፣ የሀገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎች መዳከምና ኢህአዴግ ከምሁራን ጋር ያለው ቅራኔ ምሁሩ በሀገሪቱ ፖለቲካ የጎላ ሚና እንዳይጫወት አድርጎታል በማለት በሀገሪቱ የምሁራን ተሳትፎ ደካማነትን ይገልጻሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ ያለው ወቅት ስንመለከተው ከሞላ ጎደል የምሁራን ተሳትፎ (ምንም እንኳን በማህበራዊ ሚዲያዎች የታጠረ ቢሆንም) መነቃቃት እያሳየ መስላል፡፡

በእኔ አሳብ ዛሬ ላይ በሀገሪቱ ያሉትን ምሁራን በአምስት ክፍል መመደብ ይቻላል፡፡

  1. የመጀመሪያው ምድብ “የፈራ ምድብ” ነው፡፡ እዚህ ምድብ ወስጥ የሚጠቃለሉት ምሁራን በህብረተሰቡ እና በአገሪቱ ችግሮች እንዳሉ ያውቃሉ ነገር ግን ስለሚፈሩ በእነዚህ ችግሮች ዙሪያ ምንም ማድረግ አይፈልጉም፡፡ እነዚህ ምሁራን ዋነኛ መደበቂያ ዋሻቸው “ምን አገባኝ” የምትለዋ ዐረፍተ ነገር ነች፡፡ እነዚህ ምሁራን ዳንኤል ክብረት በአንድ ጽሁፉ “ምን አገባኝ የምትል ብሒል ነች ሀገር ያጠፋች” እንዳለ በፍርሀት ተጀብነው በምን አገባኝ ስሜት ትክክለኛ ምሁራዊ ጥሪያቸውን ትተዋል፡፡ የፈላስፋ ጄን ፓውል “Intellectuals is someone who meddles in what does not concern him’’ የሚለው አሳብ እነሱ ጋ አይሰራም።
  2. ሁለተኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ምሁራን “በጭፍን ጥላቻ የታወሩ” ናቸው፡፡ እነዚህ ምሁራን በሀገሪቱ ውስጥ ለሚታዩት ችግሮች በጥልቅ እሳቤ፣ በጥናትና ምርምር ተደግፈው ምክንያታዊ መፍትሔን ከመስጠት ይልቅ በጭፍኑ ነገሮችን በመረዳት ይበልጡኑ የሀገሪቱን ችግሮች እያባባሱት ይገኛሉ፡፡ እዚህ ምድብ ውስጥ ያሉ ምሁራን በትክክል የሀገሪቱን ችግሮች አልተረዱም ወይም ለመረዳት ዝግጁ አይደሉም፡፡
  3. ሶስተኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ደግሞ “ተቺዎች” ናቸው፡፡ እዚህ ምድብ ውስጥ ያሉ ምሁራን የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ችግሮችን ከመተቸት በዘለለ እዚህ ግባ የሚባል የመፍትሔ ሀሳብ አያመነጩም፡፡ እነዚህ ምሁራን የሀገሪቱን ችግር በሁለተኛው ምድብ ካሉት ምሁራን በተሻለ ይረዱታል ያውቁታል ትልቁ ክፍተታቸው ግን መተቸት እንጂ መፍትሔ አለማመንጨታቸው ነው፡፡
  4. በአራተኛው ምድብ የሚጠቃለሉትን ምሁራን ጋናዊው ጸሀፊ ጆርጅ አይቲይ “hordes of intellectual prostitute’’ የሚሏቸው አይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ምሁራን ለራሳቸው ጥቅም እንጂ የሌላው ጉዳይ ግድ የማይሰጣቸው፣ በምሁርነት ስም ለግል ጥቅም የሚሮጡ፣ ለአእምሯቸውን ክደው ለሆዳቸው ያደሩ፣ መንግስት የማይሳሳት የሚመስላቸው፣ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አሰራርን የሚደግፉ፣ ችግሮችን እያዩ የማይነቅፉ፣ የብልሹ አሰራር ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች በአጠቃላይ በምሁር ስም ከእነሱ የማይጠበቁ ተግባራትን የሚፈጽሙ ናቸው፡፡
  5. በአምስተኛው ምድብ ውስጥ የምናገኛቸው “Socratic intellectual” የምንላቸው አይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ምሁራን ከላይኞቹ በተለየ  እንደ ታዋቂው ፈላስፋ ሶቅራጠስ “እኔ ሞቼ እውነት ትኑር” የሚሉና ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለህብረተሰብ የቆሙ ናቸው፡፡ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ማርክሲስት አንቶንዮ ግራምሼ እውቀትን የሚፈጥሩና የሚጠብቁት ምሁራን ለህዝቡ የሚናገሩ “የሕዝብ አፈ-ጉባሔዎች (spokesman of the people)” እና ለህዝቡ መብት የቆሙ መሆን አለባቸው እንደሚለው እዚህ ምድብ ያሉ ምሁራን ለራሳቸው ጥቅም ሳይሆን ለማህበረሰብ ጥቅም በመቆም  ምሁራዊ አላፍነታቸውን እየተወጡ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ምሁራን ምንም እንኳን በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም ለመንግስትም የሚሆኑ ብዙ ምክረ አሳቦችን ሲያፈልቁ እናያቸዋለን፡፡

እርቅ በእንተ-ኢትዮጲያ

“የአንዲት ሀገር ሃብት ምሁራኖቿ ናቸው” ይላል አንድ ጥንታዊ የእስራኤሎች አባባል፡፡ ማንም ሀገር ያለ ምሁራን ድጋፍ ልታድግ ልትመነደግ አትችልም፡፡ ጃፓንና ጀርመን በሁለተኛው የአለም ጦርነት እንደዚያ ተንኮታኩተው ከእንደገና በመነሳት የአለምን ሃያልነት የተቆናጠጡት በምሁራኖቻቸው እርዳታ እንጂ ሌላ በምንም አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራው መንግሥት “የአዲሲቷን ኢትዮጲያ ህዳሴ” ላለማብሰር ህልሙ ካለው ከምንግዜውም በላይ ከምሁራን ጋር መቀራረብና በጋራ መስራት አለበት፡፡መንግስት ሆደ ሰፊ ሆኖ ምሁራኑ የሚሉትን መስማት አለበት፡፡ ምሁራኖች እንዲናገሩ፣ አማራጮችን እንዲያቀርቡ፣ እንዲተቹና እንዲወያዩ መንገድን መክፈት አለበት፡፡ ምሁር ዝም ሲል ሀገር ስጋት ውስጥ ትሆናለች፡፡ ምሁሩ እንዲናገርና ሀገርንም ከስጋት ለማዳን መንግስት ምሁሩን ማናገርና እንዲናገርም መኮርኮር አለበት፡፡ በተጨማሪም ለምሁራን ተገቢውን ክብር በመስጠት ተተኪ ምሁራንን ለማፍራት  መሰራት አለበት፡፡

ምሁሩም ፍራቻውን ትቶ፣ በጭፍን ጥላቻ መንቀፉንና ከንቱ ትችቱን ለቆ በጥልቅ እሳቤ ተመስርቶ ማህበረሰቡንም ሆነ መንግስትንና ፖሊሲውን መተቸት፣ አማራጭ ማቅረብ፣ መናገር፣ መጻፍ፣ መወያየት አለበት፡፡ በመንግስትና በምሁራን መካከል አዲስ የግንኙነት መንገድ በመደማመጥና በመከባበር መመስረት ያስፈጋል፡፡ ስላለችን አንዲት ታላቅ ሀገር ብለን ምሁሩና መንግስት እርቅ ያውርዱ፡፡

Daniel Mekonen

ዳንኤል መኮንን ይልማ በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር

Filed in: Amharic