>

የሁለት ቤተ መንግስቶች ወግ! (ጌታቸው ሽፈራው)

የሁለት ቤተ መንግስቶች ወግ!
ጌታቸው ሽፈራው
አጤ ፋሲለደስ በጎንደር በርካታ ውብ ሕንፃዎች አስገንብተዋል። ዋናው የፋሲለደስ ህንፃ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት እንክብካቤ ስለማይደረግለት አብዛኛዎቹ የቤተ መንግስቱ ክፍሎች የመፍረስ አደጋ  ተጋርጦባቸዋል። አንድ ቀርስ የሚያስፈልገውን ጥበቃና እንክብካቤ አይደረግላቸውም።
ከዋናው ፋሲለደስ ቤተ መንግስት ትንሽ ራቅ ብሎ በተመሳሳይ የኪነ ህንፃ ጥበብ የተሰራ አንድ ግቢ ይገኛል። ራስ ግንብ ይባላል። አጤ ፋሲለደስ ያሰሩት ሌላኛው ግቢ ሲሆን ልጃቸው እስክንድራዊት  እና አማቻቸው ራስ  ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ የኖሩበት ግቢ ነው።
ይህ ግቢ ከመግቢያው ጀምሮ የዋናው የአጤ ፋሲል ቤተ መንግስት የሌለውን ጉዳዮች አካትቷል። አንድ ጎብኝ ምን ማድረግ እንዳለበትና እንደሌለበትም የሚገልፁ መልዕክቶች በየቦታው ይገኛሉ። ከዋናው ቤተ መንግስት የተሻለ ግቢው የታደሰና ንፁህ ነው። በሮቹና ግድግዳዎቹ ላይ ማሳሰቢያ መልዕክቶች ተፅፈዋል።
ወለሎቹ ስጋጃ ተነጥፎባቸዋል። ፎቶና ቪዲዮ ማንሳት፣ ማጨስ እንደማይቻል ማሳሰቢያዎች ተፅፈዋል። የየክፍሎቹን ታሪኮች የሚያስረዱ መልዕክቶች  ሰሌዳዎች ላይ በአማርኛ፣ እንግሊኛና ፈረንሳይኛ ተፅፈዋል። በየ ክፍሉ የሚገኙ ቁሶች ላይ በወረቀት አጠር ያለ መግለጫ ተፅፎላቸዋል። ግድግዳዎቹ፣ ለዝናብ ተጋላጭ የሆኑት ወለሎች ወደውስጥ ዝናብ የማያስገባ ምንጣት ተነጥፎባቸዋል።
የእምነት መፅሐፍቶችና መሰል ቅርሶች መስታውት ውስጥ ተቀምጠው ይጎበኛሉ። ወንበሮች፣ የንጉሱና የንግስቷ ክፍሎች ያሉት እቃዎች ጥሩ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል። ግድግዳዎቹ፣ ጣውላዎቹ ከነባሩ ጋር የሚመስል ቀለም ተቀብተዋል።
ከዋናው የፋሲለደስ ቤተ መንግስት በተለየ ክፍሎቹ ታድሰዋል። እንደዋናው ፋሲለደስ ቤተ መንግስት ጎብኝዎች በዘፈቀደ የሚፅፉባቸው፣ የሚወጡ የሚገቡባቸው አይደሉም። በጥሩ ሁኔታ የተያዙና ጉዳታቸውን በማሰብ በስጋት የሚጎበኙ ሳይሆኑ  በተመስጦ ታሪኩን ለመረዳት በሚያስችል ሁኔታ የተያዙ ናቸው።
በክፍሉ ካሉት መግለጫዎች መካከል አንዱ ላይ በዝርዝር እንደተገለፀው ግቢው ይህን ውበት ያገኘው በፈረንሳይ መንግስት እገዛ ሲሆን ጥቅምት ወር 2010 ዓም ጀምሮ ለእይታ ክፍት ሆኗል። በዘፈቀደ ከተያዘውና በርካታ ታሪኮች ከታጨቁበት የአጤ ፋሲለደስ ዋናው ቤተ  መንግስት ይልቅ፣ ጠባቧ የራስ ግንብ ውስጥ የሚገኘው ሙዝየም ለመጎብኘት የሚስብ፣ ከስነ ህንፃዎቹ ባሻገር ሌሎች ቅርሶችም የሚጎበኙበት ነው።
በሌላ በኩል በዘፈቀደ የተያዘውና እንዲፈርስ የተፈረደበት የሚመስለው፣ ዋናው የፋሲለደስ ቤተ መንግስት በርካታ ቅርሶች ያሉት ቢሆንም ክፍሎቹ ለመጎብኘት በሚያስችል መልኩ ባለመዘጋጀታቸው በርካታ ውድ ቅርሶች በአንድ አዳራሽ ተዘግቶባቸዋል።
ከስር  የሚታዩት ፎቶዎች የጎንደር መለያ መስዕብ ተደርጎ ከሚቆጠረው የፋሲለደስ ቤተ መንግስት የተሻለ ጥበቃ የተደረገለት የራስ ግንብ ግቢ ውስጥ የተነሱ ናቸው። ዋናው የፋሲለደስ ቤተ መንግስት የተሻለ ጥበቃ ቢደረግለት  ከውድመት ከመጠበቁ በተጨማሪ ምን ያህል ሳቢ ሊሆን ይችል እንደነበር በዚህ ጠባብ ግቢ የተሰራውን ማየት ይቻላል።
Filed in: Amharic