>

በትውልዶች ሁሉ ሥራው ሲዘከር የሚኖር እጅግ  ድንቅና፣ ልባም ኢትዮጵያዊ አጣን!!! (አሰፋ ሀይሉ)

በትውልዶች ሁሉ ሥራው ሲዘከር የሚኖር እጅግ  ድንቅና፣ ልባም ኢትዮጵያዊ አጣን!!!
አሰፋ ሀይሉ
 
* ለሀገሩ በሙያው ዘብ የቆመላትን መግደል ትሪሊየን ጊዜ እኩይ ቢባል የማይገፀው — የእኩይ እኩይ፣ የአሳፋሪ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
ዛሬ ስለዚህ ሰው በኢትዮጵያን መረጃ ድረገጾች እየተሰማ ያለው ወሬ ደስ አይልም፡፡ እጅግ ያስደነግጣል፡፡ የሚባለው እውነት ከሆነ ደግሞ ከዚህ በሚሊዮን እጥፍ እጅግ አድርጎ ያስደነግጣል፣ ኳድሪሊዮን እጥፍ ደግሞ እጅግ ያሳዝናል፡፡
ይህ ሰው በሙያው — ለዚህች ሀገር — ለአንዲትም ቀን ይሁን፣ ለአንዲት ሰዓትም ይሁን፣ ወይም ለአንዲት ቅፅበት — የትውልድን ራዕይ አንግቦ — ታላቅን ፕሮጀክቷን ሊገነባ — ዘብ ቆሞላታል!! ያም ራሱ ብቻውን — ሌላው ቀርቶ — የተሠራው ሥራ ጥፋት ኖሮበት ቢገኝ እንኳ ራሱ — ጥቂቶች ብቻ ሊከውኑት የሚታደሉትን — ታላቅ የወገን ሥራ እየተሠራ የተደረገ ጥፋት ነው — እንጂ — ትናንት ለሀገር የቆመልንን ታላቅ ወገናችንን ሁሉ — ዛሬ ባልተጣራ ወሬ እያሸማቀቅን — በድንዙዝ አዕምሯችንና በደነዝ እጃችን ተኩሰን እየገደልን — ለዚህች ሀገር እና ለዚህ ምስኪን ህዝብ በጎ ለውጥን እናመጣለን ብሎ ማሰብ — ከንቱ ብቻ ሣይሆን — የከንቱ ከንቱ ከንቱ — ጅልነት ብቻ ሆኖ ነው ሊያሰኘን የሚችለው!! ኢትዮጵያ በሙያው የሚገድልላት ሰው አላጣችም፡፡ ከበቂ በላይ ሞልቷታል፡፡ ያጣችው ከበቂ በላይ በሙያው ተግቶ የሚሠራላትን ወገን ነው፡፡
ድሮ የሀገራችንን ሕዝብ የጨፈጨፈች የሀገረ ኢጣልያ ተቋራጮች — እነ ሣሊኒ እንኳን — ግድባችሁን እንሥራላችሁ ብለው — በሙያቸው ለሀገራችን በሙያቸው በተሠለፉበት በዚህ ጊዜ ላይ — ለሀገሩ ለአንዲትም ቅፅበት ይሁን ለአንድ ዓመት — በሙያው ዘብ የቆመላትን አርአያ ዜጋ — ለህልፈት መዳረግ — ከቶውን ከቶውን ይቅር የማይባል — የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ብቻ ሊፈጽሙት የሚችሉት — ትሪሊየን ጊዜ እኩይ ቢባል የማይገፀው — የእኩይ እኩይ፣ የአሳፋሪ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡
ኢንጅነር ስመኘው ትውልድ በሥራው በፅናቱ በመልካም አስተሳሰቡ ሲያከብረው የሚኖር፣ በሙያው ሊመጡ ላሉት ኢትዮጵያውያን ትውልዶች ዘብ የቆመ – ተራራን በሙያው ያንቀጠቀጠ – ተራራን የናደ – ሀይቅን የፈጠረ – ኃይልን ሊያመነጭ ደፋ ቀና ያለ – በኢትዮጵያውያን ትውልዶች ሁሉ ሥራው ሲዘከር የሚኖርለት – ድንቅ ፣ እጅግ ድንቅ ፣ ልባም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እርሱን ሊያጠፉ የተነሱት አዕምሮዎች ደግሞ — ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጨለማን የሚመኙ — አዕምሯቸው በጥላቻና በጥላሸት የጨለመባቸው — የኢትዮጵያ ሕዝብ የምንጊዜም ጠላቶች ናቸው፡፡
ፍቅር ያሸንፋል፡፡ ጥላቻ ግን ሌላውን አጥፍቶ – በመጨረሻ ጠፊ ነው፡፡ ጥላቻን እናርቅ፡፡ ለፍቅር እንበርታ፡፡ ለበጎ ነገር እንበርታ፡፡ የሰው ህይወት ለመቅጠፍ ጭንቅላት አይጠይቅም፡፡ ጅብም፣ ተኩላም፣ ተዋጊ በሬም የሰውን ህይወት መቅጠፍ ይችላሉ፡፡ ታላቅን ግድብ ለመሥራት ግን ታላቅ ጭንቅላት ይጠይቃል፡፡ ታላቅ ጭንቅላት ያለውን ወገናችንን ያጠፉ እና የሚያጠፉ ተዋጊ በሬዎች ሁሉ — የምንጊዜም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው፡፡
አምላክ ከክፉ አድራጊዎች ይጠብቀን፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍቅር፣ በልጆቿ ድንቅ አዕምሮ ተበራትታ ለዘለዓለም ትኑር!!
ለኢንጅነር ስመኘው — ቢኖርም፣ ቢያልፍም — በሚመላለስበት የሀገሩ ምድር ላይም ሆነ — በሚያርፍበት ሠማያዊ ሥፍራው — መልካሙን ሁሉ ከልብ እንመኝለታለን፡፡ ለልጆቹ ገና ከፍለን የማንጨርሰው የአባታችሁ ውለታ አለብን ማለት እንፈልጋለን፡፡
አምላክ ኢትዮጵያውያንን ትውልዶች ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡
አበቃሁ፡፡
ፎቶግራፉ (ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
‹‹ኢንጂነር ስመኘው በቀለ – GERD filling process harms no other interests – ethpress››
Filed in: Amharic