>

አምስት ቀናትን በጅጅጋ ካየሁ ከሰማሁት!!! (ኦስማን ዩሱፍ)

አምስት ቀናትን በጅጅጋ ካየሁ ከሰማሁት!!!

ኦስማን ዩሱፍ

እዚያ መቼ እና እንዴት ተገኘሁ?

እኔ እና ሁለት ባልደረ ቼን ወደ ጂግጂጋ ሄደን አንድ የመስሪያ ቤት ጉዳይ ፈፅመን እንድንመለስ አርብ ዕለት አለቃችን ትዕዘዝ ይሰጡናል፡፡

በዚህም መሰረት ስራው ብዙ ቀናት የማይጠይቅ በመሆኑ ቅዳሜ በጧት ሄደን ቀኑን ሙሉ እና

እሁድ ደግሞ ግማሽ ቀን ስርተን ለመመለስ ወስነን የደርሶ መልስ ትኬት ይቆረጥልናል፡፡

በተለምዶ የጂግጂግ በረራ 2፡40 አካባቢ ከአዲስ አበባ የሚነሳ በመሆኑ እኛ ግን ጉዳያችንን

ቶሎ ፈፅመን ለመመለስ በነበረን ፍላጎት መሰረት የቆረጥነው ትኬት ከአዲስ አበባ በጂግጂጋ አድርጎ ወደ ቀብሪደሃር የሚጓዘውን አውሮፕላን ነበር፡፡

በዚህም መሰረት ምንም እንኳን የበረራ መነሻ ሰዓቱ 2፡05 የነበረ ቢሆንም ቦሌ በነበረው የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ከቦሌ የተነሳነው 2፡36 ሲል ሲሆን ጂግጂጋ የደረስነው 3፡30 ላይ ነው፡፡

ልክ ከኤርፖርት ስንወጣ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ባለ ቀይ ኮፍያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት

በኮድ 4 መኪናዎች ላይ ሆነው ስናይ ምንድን ነው እያልን ባለበት ሁኔታ አንድ ሱፍ የለበሰ

(ጀነራል ይመስለኛል) ባለስልጣንን አጅበው እነርሱ ከፊት እኛ ደግሞ ከዃላ ሆነን ወደ ከተማ መውጣት ጀመርን፤

ከኤርፖርት ወጥተን ዋናውን መንገድ እንደያዝን ሌሎች ወደ 30 አካባቢ የሚሆኑ የሰራዊት አባላት

በእግራቸው ወደ ካምፕ አቅጣጫ ሲጓዙ ብንመለከትም ከልምምድ እየተመለሱ ነው የሚል ግምት ወስደን

ነገሩን ችላ አልነው፤ ከኤርፖርት የወጣው ሰውየም እንደታጀበ ከፊታችን ሲጓዝ ቆይቶ

የአብዲ ኢሌን ቤተመንግስት እንዳለፈ ከተማ መግባቱን ትቶ በስተግራ በኩል ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ሲገባ እኛ ግን ጉዞ ወደ ከተማ ቀጠልን፡፡

ቅዳሜ ምን ሆነ?

ወደ ከተማው መግቢያ ስንቃረብ (ውጫሌ መገንጠያ ላይ) አንድ የመከላከያ ኦራል ላዩ ላይ ከባድ መሳሪያ ገጥሞ ቆሟል፡፡

ነገሩን ለማወቅ ሹፌራችንን ብንጠይቀውም ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ነግሮን

እኛም ነገሩን መልሰን ረሳነው፤ ከተማ ደርሰን አንድ ሁለት ሆቴሎችን ብናጠያይቅም

ሩም ማግኘት ባለመቻላችን በተለምዶ 06 በሚባለው ሰፈር በኩል አድርገን ወደ ታይዋን መንገድ ገብተን

መጓዝ እንደጀመርን የክልሉ ም/ቤት አካባቢ ያልተለመደ ግርግር በማስተዋላችን እና

ባለታክሲውም ወደ ኤርፖርት መመለስ በመፈለጉ ወደ ቢሮ እንዲወስደን ተስማምተን

በቅርብ ርቀት (ሴንትራል) ወደሚገኘው ቢሯችን አመራን፡፡

ቢሮ ደረስን …

የተቀበለን የስራ ባልደረባችን (የሶማሌ ተወላጅ ነው) በከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ ሆኖ

ጉዞውን እንድንሰርዝ ለመንገር በተደጋጋሚ ስልካችንን ቢሞክርም

እኛ በረራ ላይ ስለነበርን ሊያገኘን እንዳልቻለ በመንገር ከተማ ውስጥ ውጥረት መንገሱን እና

እኛም በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንድንመለስ ይነግረናል፤

በዚህ መካከል ግን ከህንፃው ውጪ ግርግር እና ጩኸት በመስማታችን ሁኔታውን ለማጣራት ስንወጣ

ከመቶ የማይበልጡ ሰዎች የተቃውሞ ድምፅ ያሰማሉ፤

ነገሩን ለመረዳት የጅግጂጋውን ባልደረባችንን ስንጠይቀው

“አብዲ ኢሌ ይውረድ!” እያሉ መሆኑን ነገሮን ወደ ቢሮ እንድንመለስ ጠየቀን፤

ነገር ግን ሁኔታው እየባሰ በመሄዱ እና የሰዎቹም ቁጥር ቁጥር እየጨመረ መጥቶ እርስ በራስ ድንጋይ መወራወር ተጀመረ፡፡

ነገሮች ባልተጠበቀ ፍጥነት ተለዋውጠው አብዲ ኢሌ ይውረድ የሚሉ ሰዎች የት እንደገቡ ሳይታወቅ

አቢይ ይውረድ!፤ ረጅም እድሜ ለአብዲ ኢሌ! CMC! ወዘተ. የሚሉ ድምፆች መሰማት ጀመሩ፤

ሴንትራል አካባቢ የሚገኘው የትራፊክ መብራት ይዞት ቆሞ የነበረ ቅጥቅጥ አይሱዙ መኪናን መደብደብ፤

እዛው አካባቢ በእጅ የሚገፋ ጋሪ ላይ ቢራ ጭኖ ይሄድ የነበረ ወጣትን ቢራ መስበር

ቀጥሎ የሆነው ነገር ሁሉ መነሻ ሆነ፤ ቀጥሎ ከትራፊክ መብራት ፊት ለፊት አዲስ በመገንባት ላይ ካለ ህንፃ ስር

የነበረው የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ላይ የድንጋይ ናዳ ማውረድ፣ በጅምላ መዝረፍ እና የባንኩ ሰነዶች መንገድ ላይ እንዲበተን ተደረገ፡፡

ከዚያ በኋላ …

የሆነው ነገር በሙሉ በቃላት ለመግልፅ የሚቻል አይደለም።

የሀበሻ ናቸው የተባሉ ሱቆች፤ ሆቴሎችና ካፌዎች፣ ቡቲኮች፣ ክሊኒኮች እንዲሁም ባንኮች ወደሙ፤

አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ፤ መጤ የተባሉ ሰዎች በመንጋ እየተከበቡ ተቀጠቀጡ፤

መኪናዎች እና ባጃጆች ከቆሙበት መስታዎታቸው እየተሰበረ እና ያለ ቁልፍ ኤልክትሪክ እየቆረጡ በማስነሳት መስበር፤

በአደባባይ መንዳት እና ወዳልታወቀ ስፍራ መውሰድ እንደ ጀብዱ በአደባባይ ተፈፀመ፡፡

ከቀኑ 10፡00 አካባቢ ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አሻጋሪ የሚገኘው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሁ

በተመሳሳይ ሰልፈኞች ተወሮ ተሰብሮ ተዘርፏል፤ ኤዶም ሆቴልም በተመሳሳይ ሰዓት በእሳት ተልኩሷል፡፡

ይሄ ሁሉ የሆነው ሴንትራል የሚባለው አካባቢ ሲሆን ተመሳሳይ ተግባራት በከተማ በሙሉ ሲፈፀም ውሏል፡፡

ከጠዋቱ 4፡30 አካባቢ የጀመረው ሁከት እና በጥብጥ እንዲሁም ዝርፊያ መረጋጋት ያሳየው

ከምሽቱ 2፡00 አካባቢ ጀምሮ ሲሆን ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ፀጥ ያለችው ግን ከምሽቱ 5:00 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡

ይሄ ሁሉ ሲሆን የከተማው ህዝባዊ ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ሀይል ዘራፊዎቹን ሲያጀቡ እና ሲያበረታቱ፣ በክፍት መኪናዎች ተጭነው ለዝርፊያው ሽፋን ይሰጡ ነበር፡፡

እኛም ከቢሮ መውጣት ባለመቻላችን በስጋት ተወጥረን የመጀመሪያውን ምሽት በቢሮ ውስጥ ለማሳለፍ ተገደድን፤

ለእራት ይሆነን ዘንድ ህንፃው ላይ የሚገኝ አንድ ሱማሌ ግለሰብ ካርቶን ሙሉ ብስኩት ገዝቶ

ህንፃው ውስጥ ላለን ሰዎች ሲያድለን የእኛ የስራ ባልደረባ ደግሞ የተቀቀለ በቆሎ እና የሚጠጣ ነገር አመጣልን፤ እርሱን በልተን ሌሊቱን አሳለፍን፡፡

እሁድ

በስጋት ስንናጥ አድረን እኔ እና አንደኛው ባልደረባየ የሱብሂ ሰላት ሰግደን ንጋት 12፤00 ሰዓት ሲል በሱማሌው ወዳጃችን ታጅበን በእግር ወደ ኤርፖርት መጓዝ ጀመርን፤ በጉዟችንም ቅዳሜ ዕለት በከተማው የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመታዘብ የበለጠ እድል አገኘን፤ በመንገዳችን የተዘረፉ ሱቆችን፤ የተቃጠለ ባጃጅ እና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በአናይችን ለመመልከት ቻልን።

እስከ የመከላከያ ካምፕ ድረስ በእግራችን ጉዞ ካደረግን በኋላ አንዲት ባጃጅ የቆሰለ ልጅ መከላከያ ካምፕ ውስጥ ወዳለው ክሊኒክ ይዛ ስትመጣ አገኝንና ከካምፕ ጀምረን እስከ ኤርፖርት ድረስ (ምናልባት 7 ኪ.ሜ.) በባጃጅ ተጉዙን ኤርፖርት ብንደርስም በረራ በመሰረዙ እና ወደ ከተማ ለመመለስ የምንችልበት እድል ዜሮ በመሆኑ እንዲሁም ኤርፖርቱ ለደህንነታችን ምቹ ቦታ ሆኖ ስላገኘነው ከእሁድ እለት ጀምረን እስከ ረቡዕ ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ ለአራት ቀናት በኤርፖርት ለማሳላፍ ተገደናል፡፡

በአጠቃላይ በኤርፖርት የነበሩ እውነታዎች ሲጠቃለሉ የሚከተሉት ናቸው፡፡

• የፌደራል ፖሊስ የኤርፖርት ጥበቃ አባላት ወደ ካምፓቸው ከወሰዱን በዃላ እንደነገሩን ቅዳሜ ጧት ላይ የክልሉ ልዩ ሀይል አባላት በፓትሮል መጥተው ለፌደራል ፖሊስ አባላት ኤርፖርቱ በእነርሱ ቁጥጥር ስር መዋሉን በመንገር የፌደራል ፖሊስ አባላት ለቀው እንዲወጡ ይነግሯቸዋል፤

ይሁን እንጂ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሀይላቸውን በማጠናከር ከበባ ሲፈፅሙባቸው ነገሩ እንደማያዛልቅ በመገንዘብ ኤርፖርት ውስጥ ያሉ የእኛን ሰዎች ስጡን ይሉ እና በዚህ ተስማምተው የሱማሌ ተወላጆችን ይዘው ኤርፖርቱን ለቅቀው ወጥተዋል፤

• የኢፌዴሪ የመከላከያ ሀይል ወደ ጅግጅጋ ከተማ የደረሰው እሁድ ንጋት ላይ ነው፤

የመጀመሪያው ዙር የመከላከያ አባላት ቅዳሜ ማታ 2፡00 ሰዓት ላይ በቦይንግ ተጭነው ቢመጡም የጂግጂጋ ኤርፖርት መንደርደሪያ (Runway) የማታ መብራት ስለሌለው አውሮፕላኑ ለማረፍ ባለመቻሉ

ተመልሶ ድሬዳዋ አድሮ ጧት 12፡00 አካባቢ ወደ ጅግጅጋ ተመልሶ የመጀመሪያ ዙር አባላትን አውርዷል፡፡ከአንደኛው ሻለቃ ጠይቀን እንደተረዳነው እነሱ የሀገሪቱ ልዩ ሀይል (ስፔሻል ፎርስ) መሆናቸቸውን ገልፆልናል፤

• ሁለተኛው ዙር የስራዊት አባላት ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ በጦር አውሮፕላን (አንቶኖቭ) ተጭነው ጂግጂጋ ላይ አርፈዋል፤

ይሁን እንጂ እስከ ሰኞ ከሰዓት ድረስ የትኛውም የመከላከያ ሀይል ወደ ከተማ ገብቶ የማረጋጋት ስራ አልሰራም፡፡ በእኔ እምነት ይህ የሆነው ፖለቲከኞች እካሄዱት በነበረው ድርድር ምክንያት ይመስለኛል፤ በተረፈ ቀሪው የመከላከያ አባላት የገቡት በሀረር በኩል በመኪና ነው።

ሰኞ

• ሰኞ እለት ወደ አስር ሰዓት አካባቢ ከአዲስ አበባ በቻርተርድ አውሮፕላን (Bombardier Q400)

አምስት ሰዎች አብዲ ኢሌን ይዘው ለመመለስ ወደ ጅግጂጋ ይመጣሉ፤

በዚህም መሰረት በሶስት መኪናዎች ም/ፕሬዘዳንቷ እና አፈ ጉባዔውን ጨምሮ 20 (VIP) ሰዎች ያሉት

የአብዲ ቡድን በኤርፖርት ከተገኘ በሁዋላ ምክትል ፕሬዘዳንቷ እና ሌሎቹም አንፈተሸም በማለታቸው

የኤርፖርቱ ሰራተኞች ሁኔታውን ከአዲስ አበባ ለመጡት ሰዎች ያሳውቃሉ፤

የአዲስ አበባዎቹ ሰዎች በደንብ ፈትሿቸው የሚል ትዕዛዝ በመስጠታቸው እና

እነርሱ አንፈተሸም በማለታቸው አፈ ጉባዔው እና ም/ፕሬዘዳንቷ በስልክ ከሌላ ሰው ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ኤርፖርቱን ለቀው ወጥተዋል፤

ኤርፖርት ዙሪያ ለጥበቃ ተሰማርተው ከነበሩ ፖሊሶች ለመረዳት እንደቻልኩት

ፕሬዘዳንቱ ከዋናው መንገድ ወደ ኤርፖርት መገንጠያው ላይ በልዩ ፖሊሶቹ ታጅቦ ቆሞ የነበረ ሲሆ

ን የም/ፕሬዘዳንቷን እና አፈ ጉባዔው መኪናዎች ከኤርፖርት መውጣታቸውን ተከትሎ

እርሱም ወደ ቤተ መንግስቱ ተመልሷል፡፡

በእኔ ግምት ምናልባት ሁለቱ ሰዎች ስልክ ሲያወሩ የነበሩት ከአብዲ ጋር ሊሆን ይችላል ብየ አስባለሁ።

• የአብዲ ሰዎች የኤርፖርቱን ህንፃ ለቀው እንደወጡ አቶ አህመድ ሽዴ (እኔ ያየሁት በዋልታ ቴሌቪዥን ነው) መግለጫ መስጠት ጀመረ፤

ይሄ ሲሆን ከአዲስ አበባ የመጡ አራቱ ሰዎች ከእኛ ጋር መግለጫውን በመከታታል ላይ እያሉ

አምስተኛው ወደ ውስጥ ገብቶ ተመለሰ እና አራቱን ባልደረቦቹን እንሂድ ሲላቸው

ወደ አውሮፕላናቸው ገብተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡

እውነት ይሁን አየሁን ማወቅ ባልችልም በአውሮፕላኑ ውስጥ ከአምስቱ ሰዎች በተጨማሪ

አህመድ ሺዴ እና ደመቀ መኮንን ነበሩ ሲባል ሰምቻለሁ፤ የአብዲ ሰዎች የወጡበት፣

መግለጫው የተለቀቀበት እና የአዲስ አበባዎቹ ሰዎች ወደ ፕሌን የገበቡትን ቅፅበት ካስተዋልነው የእነ አህመድ ፕሌን ውስጥ የመኖር እድል ከግምት በላይ ነው።

• የመከላከያውን ወደ ከተማ መሰማራት ተከትሎ ሰኞ ማምሻውን የድጋፍ እና የተቃውሞ ሰልፎች የነበሩ ሲሆን

በተለምዶ ሀበሻ የሚባለው የማህበረሰብ ክፍል በሶማሌዎቹ ላይ የአፀፋ ርምጃ መውሰድ ጀመረ፤

ሀረር ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ (ከኖክ ማደያ ጀርባ አካባቢ) የሚገኝ መስጂዲን ለማቃጠል ሙከራ የነበረ ሲሆን

በመከላከያ ጣልቃ ገብነት መስጂዱ ከመቃጠል መትረፉን ከሶማሌው ባልደረባየ ተነግሮኛል፡፡

ማክሰኞ

• ማክሰኞ እኩለ ቀን አካባቢ አብዲ ኢሌ በመከላከያ እጅ ገባ፤

እንደ ተያዘም እርሱ ከሚኖርበት ቤተ መንግስት አቅራቢያ ወደሚገኘው የኤፌዴሪ የመከላከያ ካምፕ ተወስዷል፤

ይሄን የሰማሁት ከጎናችን የነበረ ባለማዕረግ ወታደር ከባልደረቦቹ ጋር ሲነጋገር ነው።

• ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ሀይል በመኪና ወደ ጅግጂጋ ጉዞ ያደርጋል፤

በጉዞ ላይ እያለም የተዘጋ መንገድ ለማስከፈት (ቦምባስ ወይም ፋፈን ላይ) በሚሞክሩበት ጊዜ

በተከፈተ ጥቃት አንድ የመከላከያ ሻለቃ ይቆስላል፤

• ወደ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የኢፌዴሪ አየር ሀይል ንብረት የሆነች ሄሊኮፍተር

የህክምና ቡድን አባላትን ይዛ ጂግጂጋ ኤርፖርት ከደረሰች በኋላ

የህክምና ቡድን አባላቱን አውርዳ ቁስለኛው ሻለቃ፤ ሌሎች ወታደሮች እና ከእኛ ጋር የነበሩ

ሶስት ሲቪሎች (እኔ ራሴ ከተሳፈርኩ በኋላ ነው ፓይለቱ ያስወረደኝ) ከጫነች በኋላ ወደ መከላከያ ካምፕ አመራች፡፡

• መከላከያ ካምፕ ድጋሚ በማረፍ አብዲ ኢሌን እና ሌሎች ሰዎችን ጭና ከጂግጂጋ ድሬዳዋ አዲስ አበባ አቅንታለች፡፡

ወደ አስር ሰዓት ከጂግጂጋ ተነስታ 12፡00 አካባቢ አዲስ አበባ መድረሷን የኤርፖርት ሰራተኞች ነግረውኛል፤

• ማክሰኞ ማምሻውን አብዲ ኢሌ ተደራድሮ ወደ ስልጣኑ ተመለሰ የሚል ወሬ በመናፈሱ እና

ደጋፊዎቹ ወደ ጎዳና በመውጣታቸው ውጥረት ነግሶ የነበረ ቢሆን

በመጨረሻ መከላከያው የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ነገሮችን በመቆጣጠሩ ነገሩ በአጭሩ ተቋጭቷል፡፡

ረቡዕ

• ረቡዕ ዕለት ከተማው አንፃራዊ ወደሆነው መረጋጋት የተመለሰ ሲሆን በኤርፖርቱ ውስጥ ከእኛ ጋር የነበሩ

ሰዎች ከተማ ደርሰው ተመልሰው ይሄንኑ አረጋግጠውልኛል፤

• ረቡ ከሰዓት ጀምሮ ወደ ሀረር የሚወስደው መንገድ በመከፈቱ እና ሰዎች በጭነት መኪናዎች ተጭነው መውጣት የጀመሩ ሲሆን

እኔ እና ጓደኞቼም ምሽት 12፡00 ላይ ከኤርፖርት በመውጣት በአይሱዙ መኪና ተሳፍረን  ምሽት 2፡00 ሀረር ደረስን።

በነጋታው (ዛሬ ሀሙስ) ከቀኑ 6፡00 ድሬዳዋ መግባት የቻልን ሲሆን እድለኞች ሆነንም ፕሌን በማግኘታችን ከድሬዳዋ አዲስ አበባ 7:40 አካባቢ በሰላም ገብተናል፡፡

ሲጠቃለል

• መከላከያ አብዲን ለመያዝ ሞክሮ አልተቸገረም፤ ሲወራ እንደነበረው ሳይሆን የአቶ አህመድ ሺዴ መግለጫ እስኪወጣ ድረስ መከላከያው አብዲን ለመያዝ እንቅስቃሴ አላደረገም፤

• በሩቅ እሰማው ከነበረው ፍፁም ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አባላት

ሲበዛ ሩህሩህ እና ቅን ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፤ ለእነርሱ ያለኝ እሳቤ እስከ ዘላለሙ እንዲቀየር የሚያደርግ እንክብካቤ አድርገውልኛል፡፡

• በጅግጂጋ እንዳየሁት መከላከያው ሲበዛ ጥንቁቅ መሆኑን አስተውያለሁ፤

ነገሮች እንዳይጋጋሉ እና ፈር እንዳይስቱ የሚያደርጉት ጥንቃቄ ተስፋ የሚሰጥ ነው፤

• ከስራ ባልደረቦቼ እና ሌሎችም ሰዎች ጠይቄ ያገኘሁት መረጃ እሚያሳየው የችግሩ መነሻ

አርብ ምሽት ላይ አብዲ ኢሌ ክልሉን ከኢትዮጵያ ገንጥያለሁ ማለቱ እና

ይሄንንም በክልል ምክር ቤት ቅዳሜ ለማስፀደቅ መንቀሳቀሱ አንዱ ሲሆን

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በክልሉ ከተገኘው ነዳጅ የክልሉ ደርሻ 5% ነው ብሎ ዶ/ር አቢይ ተናግሯል ተብሎ ወሬ መናፈሱ ነው፤

Filed in: Amharic