(አሰፋ ጫቦ- የትዝታ ፈለግ )
….ወደ እኛ ቤት የሚወስደውን የመንገድ ካርታ ልስጣችሁ።…. አባቴ ዳና ሳዴ፣ ሀማ፣ ያሬና፤ እናቴ ማቱኮ አጆ ሙሉ ጋሞ ናቸው። ታላቅ ወንድሜ 12 ልጆች ወልዷል። የስምንቱ እናት ታየች በዛብህ የጋሞ ነፍጠኛ አማራ ናት። የአራቱ እናት ትግሬ ነች።
የእኔ ልጆች 3ቱ እናት ጎንደሬ መስላኝ ነበር። እናቷም እሷም ጎንደር ስለተወለዱ ጎንደር ስላገባኋት። ጠጋ ብዬ ሳይ የእናቷ እናት ካፈቾ ናቸው። በሚኒሊክ ወረራ ተማርከው ከወጡት ከከፋ ልዕልቶች ውስጥ ነበሩ። የጋኪ ሻረቾ ዘመድ ነበሩ። በ1956 እኔ ሳናግራቸው ዕድሜያቸው ከ100 አመት በላይ መሰለኝ። አማርኛ አይችሉም። ድንገት ካፊቾ ቢችሉ ከማን ጋር ሊነጋገሩ? የባለቤቴም አባት አዘዞ ተመድቦ የነበረ ወታደር የሸዋ ኦሮሞ ነው ተባለ። አንዱ ልጄ ¼ኛ ጉራጌ ነው።
የእህቴ ባል ኦሮሞ ነው። ባሏ ደግሞ የሄደው ከሰላሌ ነው። አምስት ወልደዋል። አንዱ ወንድሜ ሶስት ልጆች አሉት። ትልቋ ግማሽ ኩኩዩ ነች። የሁለቱ እናት እንግሊዛዊት ነች።
የሻቱ በዛብህ ሚስት ንግስቲ መረፅ ስመ ጥር ሀማሴን የሻሸመኔ ልጅ ነች። ሻሸመኔ ከወንድሟ ከኢትዮስ መረፅ ጋር አጼ ናዖድ ትመህርት ቤት አብረን ነበርን። ሻቱ የታየች ወንድም ነው። አማራ የጋሞ ነፍጠኛ ነው። ወልደው ከብደዋል።
የእኔ ልጆች ሁለቱ አግብተው ወልደዋል። ትልቁ ባህርዳር የተወለደው ልጄ ሚስቱ ኤርትራዊት ነች። የሀረር ኤርትራዊት። ትንሿ ልጅ ያገባችው ግማሽ አማራ የሆነ ልጅ ነው።
ኧረ ተውን! እንዲህ ተወሳስቦ እያለ አትከልክሉን! ማሩን! ኢትዮጵያዊ በሉን! የእኛ ቤት መቀላቀል ገና አንድ ሁለት ትውልድ ነው። ለአስር ትውልድ ያህል የኢትዮጵያ ውብ ጥበብ (ሞዛይክ) ገጽታ የፈጠሩ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን አሉ።
ካሳ አንበሳ – ምንጭ፡ የትዝታ ፈለግ መጽሐፍ፣ ገፅ 148