አሰፋ ሀይሉ
ከኛዎቹ በጥላቻ እሣት ከሚግለበለቡት በርበርታዎችና ሂጎዎች፣
ከኛዎቹ በንዴት እሣት ከሚንቀለቀሉት ቄሮዎች፣ ከኛዎቹ በንዴት እሣት ከሚንተከተኩት ኤጀታዎች፣ ከኛዎቹ በንዴት ቋያ ከሚግለበለቡት ፋኖዎች፣
ከኛዎቹ በንዴት እሣት ከሚቅለበለቡት ዘርማዎች እና ከመሣሠሉት እሣት ለብሰው እሣት ጎርሠው… የንዴት፣ የቁጭት፣ የበቀልና የጥላቻ እሣት አንድደው ከሚነዱት ቁርጡ የታወቀው የፋሽስት ጦር በምን ጣእሙ ያሰኛል!!!
– ‹‹አሁን እኔ ፈልጌ ነው ደብረሲና ላይ የተወለድኩት??! ፈልጌ ነው ወይ…???!!!!››
ይሄ ባለሣይክሉ የፋሺስት ኢጣልያ የጦር መኮንን ነው፡፡ በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ወረራ ዘመን በአዲሳባ ፒያሳ፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ (በቼንትሮ እያለፈ) የተነሣው ታሪካዊ ፎቶ ነው፡፡ በወቅቱ ፒያሣ ለነጮች ብቻ የተከለለች ናት ሲባል ብንሰማም – ይኸው በዚህ ምስል እንደምናየው – ብዙ ዘናጭ ኢትዮጵያውያንም ከባለሣይክሉ ጀርባ ይታያሉ፡፡ ያውም – አፍሮቴክሶቹ ኢትዮጵያውያን – በሣይክል ላይ ተፈናጥጠው ጭምር ነዋ – ከባሻገር የሚታዩት፡፡
እና … ሚን ላማለት አካባቢ ኖ?!
ለማለት የተፈለገው አካካባቢማ… እነዚህን ከሠፈራችን ውጡልን፣ ከከተማችን ውጡልን፣ ካገራችን ውጡልን፣ ከምናምናችን ውጡልን….! የሚሉትን የኛን ዘመነኞች ነገር ስመለከት ነዋ – ወደ ዋናው የፋሺስቶች መናኸሪያ – ወደ ፒያሣ አካባቢ – በቢሽኪሊሊት የመጣሁት፡፡ ምነው ሸዋ!!! . . . እንዴ?! ያሁኖቹ የራሳችኑ ‹‹አንያችሁ!›› ባዮች እኮ… ከነዚያ ቁርጡን ከለየላቸው ፋሺስቶች አንፃር እኮ ከታዩ…. አልባሱ ይሆን ያሁነኞቹ የራሳችን ፋሺስቶች ግን?
እሣት እሣትን ሲወልድ አየን እኮ!!! ያ ያለፈው ክፉ እሣት የፈጠረው የበለጠ፣ ከልካይ የሌለው፣ ሃይ ባይ የሌላቸውን እሣቶች ነው!!!! እሣት እሣትን ወልዶብን ቁጭ አለኮ!!! እንዲያው ምን ይሉት ኩነኔ ይሆን ግን… እንዲህ ካንዱ እሣት ወደ ሌላው እሣት… ከእሣት መልሶ ወደ እሣት እያሸጋገረ የሚደረግመን…?? መጥኔ ነው እንጂ! የወገን የራስ መጥኔ!!
አንዳንዴ እኮ…. በቃ አንዳንድ እየተፈፀሙ ያሉ ነገሮችን ስናይ እኮ… የምር… ወይ አንድያቸውን እነዚያ ቁርጣቸው የታወቀው… እነዚያ በዱር በገደል ብለው አያቶቻችን ያስወጧቸው… በየረገጡበት ሃገር ‹‹ፒያሳ›› ብለው በየሚሰይሙት አደባባይ… ወዲያ ወዲህ በሣይክላቸው እንዲህ ሽው ሽው ሲሉ የሚውሉት፣ ‹‹ዝቅ በሉልን፣ ስገዱልን፣ አሜን አሜን በሉልን›› የሚሉት… እና አሜን ብለህ ከተገዛህ ምንተዳዬ ብለው የሚተዉህ…. እነዚያ ደህና ደህናዎቹ ሻል ሻል ያሉት በዚህ ፎቶ እንደሚታየው ያሉትን ‹‹ሸበላ የሙሶሊኒ ወጣት ፋሺስቶችን!›› አፈላልገን እናምጣ ይሆን እንዴ ግን ወዳገራችን?? የምር… እንዲህ አንድያውን ቁርጡ የታወቀውን ‹‹ግባ በለው!›› ብለን ብናስገባው አይሻልም ግን? አንድያውን ባዕዱ ፋሺስት አይሻልም – ከራሳችኑ የወገን ፋሺስት??
ከኛዎቹ በጥላቻ እሣት ከሚግለበለቡት በርበርታዎችና ሂጎዎች፣ ከኛዎቹ በንዴት እሣት ከሚንቀለቀሉት ቄሮዎች፣ ከኛዎቹ በንዴት እሣት ከሚንተከተኩት ኤጀታዎች፣ ከኛዎቹ በንዴት ቋያ ከሚግለበለቡት ፋኖዎች፣ ከኛዎቹ በንዴት እሣት ከሚቅለበለቡት ዘርማዎች፣ እና ከመሣሠሉት እሣት ለብሰው እሣት ጎርሠው… የንዴት፣ የቁጭት፣ የበቀልና የጥላቻ እሣት ባገኙት ሁሉ ላይ ለመለኮስ ሲንቀዠቀዡ ከምናያቸው ከራሳችኑ ዱቼያኖች…. የምር.. seriously… አንድያውኑ – ወገን ናቸው ብለን ቆጥረናቸው የማናውቃቸው – እነዚያ የድሮዎቹ እንዲህ እንደምናየውን የመሠሉት ባለሣይክል ሸበላ ሶላቶዎች አይሻሉ ይሆን ግን… ?
ኧረ በስንት ጣዕማቸው!!!? እኒያን ዘናጭ ጥልያኖች አስወጥተው… ይኸው ለገዛ ራሳችኑ እቶን እሣቶች መለመላችንን የጣሉን አያት ቅድመ አያቶቻችን…. ምን በድለናቸው ይሆን?? ምን ይሉት እርግማን ይሆን ግን በራሳችኑ ፋሺስቶች መንጋጋ ያስጣለን??!! እናንት የኢትዮጵያ አርበኞች… ምን በድለናችሁ ይሆን… ባዕዳኑን ፋሺስቶች አስወጥታችሁ እንዲህ በራሳችን ፋሺስቶች እንቃጠል ዘንድ ልባችሁ እሺ ያላችሁ??!!
አስባሉኛ!!!? እኒህኞቹ አቃጣዮች፣ ሠቃዮች፣ ገዳዮች፣ በስሜት እሣት የተንቀዠቀዡት የራሳችኑ የዛሬ ዘረኝነትን እንደጠብመንጃ ያነገቡ ከገዛ ራሳችን ማህፀን የወጡ… የገዛ ራሳችኑ ዘመነኛ ፋሺስቶች… አሰኙኛ! አስመኙን እኮ እነዚያን ቁርጣቸው የታወቀላቸውን የፒያሣ ፋሺስቶች!!! ኧረ ማሩኝ ጀግኖች አርበኞች!! ይህማ ይመጣል መች አላችሁ እናንተ!!?? እንኳን በእውን – በህልም እንኳ – እንዲህ በገዛ ሀገሩ ኢትዮጵያዊ ተሸማቅቆ.. እንዲህ የዚህች ምድር ያበቀለችው ኢትዮጵያዊ… እንዲህ በሄደበት መሬት ብትውጠው እንደሚመኝ – መች ታያችሁ እናንተ??!!
‹‹ነፃነትን አወረስን›› ብላችሁ እፎይ ብላችሁ ያለፋችሁ እናንት አያት ቅድመአያት አርበኞች… ለከንቱ ሲላችሁ ነበር ለካ.. ያን ለሀገር ሲባል ወደኋላ ያላለ አንገታችሁን ለፋሺስት ጎራዴ አሣልፋችሁ የሰጣችሁት? ለካንስ እንዲህ ለከንቱ ነበር ያን ተሰፍሮ፣ ለተክቶ ሀገር የማይበቃውን ያን የማያልቅ ውድ ኢትዮጵያዊ ደማችሁን.. እንዲያ ከፋሺስት ጋር በዱር በገደል እየተሞሸላለቃችሁ… በዚህች እንዲህ ከንቱዎች ሊወርሷት እንዳሉ ባልጠረጠራችኋት ምድር ላይ – እንዲያ በከንቱ ደማችሁን ያዘራችሁት??!!!! መጥኔ! መጥኔ! መጥኔ! መጥኔውን ይስጣችሁ!!!
ገና 30ና 40 ዓመት ሙሉ እግዜር በእርግማኑ በራሳችኑ ጉግማንጉጎች በትውልዳችን ላይ የዘራብን የዘረኝነት ዘር፣ በትውልዳችን ላይ የተበተነብን ያ ሁሉ የብሔርተኝነት ዘር፣ ያ ሁሉ የሰቆቃ፣ የግፍ፣ የጭቆና፣ የጥላቻ፣ የመጠፋፋትና የመጠራጠር መርዝ….. ገና የቱን ያክል ጥፋት፣ የቱን ያክል የበረታ እሣት፣ የቱን ያህል የራቀ ጥልቅ ገደል ውስጥ ስንቶቻችንን እንደሚጨምረን…. ገና መች አወቅነው?? አዬዬዬ….!! ኡፍፍፍ…!!! በማይሆነውም፣ በሚሆነውም ሁሉ እንዲህ ጨሰን አርረን አለቅን እኮ!!!! ሣይቸግር ጤፍ ብድር! እስቲ ይሁና… እንግዲህ!! እንዲህ የመፍትሄ መካን ስንሆን… ምን ይደረጋል??!!
ለማንኛውም – እኔም እራሴ – በየቦታው ለዓመታት እንደፍም እዚህም እዚያም በአመድ ተለባብሶ ሲቀበርብን የኖረው የዘር እሣት ቋያ – እንዲህ አፍ አውጥቶ፣ እያደር ሲቀጣጠል፣ እያደር ሲበላን፣ እያደር ሁላችንን ወደ እሣቱ ሲጨምረን በማየው – በዚሁ ሀገራዊ የጥፋት እሣት – እኔም በበኩሌ – የቃላት እሣት ለብሼ – የንዴት ቃላት ጎርሼ – በሚግለበለብ ጥቅል ቋንቋ – በሚፋጁ ትኩስ ቃሎቼ – በጅምላ የተኮስኳችሁን ወገኖቼን – እስቲ ከልብ ‹‹አፎ!›› በሉኝ – ብዬ ልለይ!!! ምን እናርግ… ?!! አሁን በኛ ይፈረዳል?? አሁን በኔ ይፈረዳል.. እንዲህ በንዴት የቃላት እሩምታዬን ባንበለብለው??!! ይፈረዳል ወይ?? ‹‹አሁን እኔ ፈልጌ ነው ደብረሲና ላይ የተወለድኩት??! ፈልጌ ነው ወይ???!!!!››
አቤቱ ማረን ፤ አታመራምረን ! ! እስቲ ለሁላችን ልቦናውን ይስጠን!! ሃገራችንን ትውልዳችንን ይባርክ አንድዬ ቸር አባታችን፡፡ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያ ሀገራችንን አብዝቶ ይባርክልን አምላካችን፡፡ ልቦናችንን ይመልስ!! ፍቅርና ሕሊናችንን ይመልስ!!! በምህረቱ ልባችንን ያብስ!!! አሜን ይሁን!!!