>
10:51 am - Sunday May 22, 2022

ዶ/ር አብይ እንዳያስጨርሱን!!! (ይድረስ ለዶ/ር አብይ) - [ያሬድ ደምሴ መኮንን]

ዶ/ር አብይ እንዳያስጨርሱን!!!

(ይድረስ ለዶ/ር አብይ)

ያሬድ ደምሴ መኮንን

ዶ/ር አብይ ሆይ!! እንደ እርግብ የዋህ ብቻ ሳይሆኑ እንደእባብ ብልህ የሚሆኑበት ጊዜ አሁን ነዉ፡፡

እርስዎ የሚያምኑበት ታላቁ መጽሃፍ የሚለዉም ይሄንኑ ነዉ!!

“እንደ እርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ ሁን!!”

የእርስዎን እንደርግብ የዋህ መሆን ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ እስኪበቃን ድረስ አይተናል፡፡ደግ ነዎት፡፡አዛኝ ነዎት፡፡መሃሪ ነዎት፡፡እርስዎ ምንም የማይወጣልዎት መሪ መሆንዎን በዉጭም ሆነ ሃገር ዉስጥ ያሉ ኢትዮጵያዉያን በሙሉ መስክሮልዎታል፡፡ለ27 ዓመታት ሳይታክት ኢህአዴግን ሲቃወምና ስለነጻነት ፍትህ ሲጮህ የነበረዉን ታማኝ በየነ በፍቅርዎና በትህትናዎ እግርዎ ስር አንበርክከዉ ዲያስፖራዉን ከጎንዎ አሰልፈዋል፡፡ለሁለት አስርት አመታት ያህል የተኮሳተረ ህይዎት ሲመሩ የነበሩትን የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሳቅ አንከትክተዉ ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል፡፡የእናት ሃገር እትዮጵያዉያን ስም ለመጥራት የሚያንቀዉና ስለ ሃገር አንድነት ሲወራ የሚያንገሸግሸዉን ሁሉ ዛሬ ከእርስዎ ጋር ኢትዮጵያ እያለ እንዲዘምር በፍቅርዎ አስገድደዉታል፡፡

አዎ እርስዎ እንደ እርግብ የዋህ ስለሆኑ ይህ ተችሎዎታል!!!

ትናንት ቀና ብሎ በነጻነት መሄድ አቅቶት “ቃና” ቴሌቪዝን ዉስጥ ተደብቆ የነበረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በእርስዎ ሱስ ተጠምዶ ሴቱም ወንዱም ትንሹም ትልቁም የቲቪዉን ሪሞት ኮንተሮል ከእጁ ሳይነጥል ከአንዱ አገር በቀል የዜና ቻናል ወደሌላዉ ቻናል እየዘለለ ሰበር ዜናና የእርስዎን ንግግር በማሰስ ዉሎ እያደረ ነዉ፡፡የእርስዎን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ እያነከሰ ሲኖር የነበረዉ ህዝብ አንጻራዊ ነጻነትን ተቀዳጅቶ እርስዎን እድሜ እንዲሰጥዎት እየጸለየ ይገኛል፡፡

አዎ እርስዎ እንደ እርግብ የዋህ ስለሆኑ ብቻ ይህ ሁሉ ተችሎዎታል!!!

ይሁን እንጂ ይቺ የበራችለትን የነጻነት ሻማ ለማጥፋት ከያቅጣጫዉ የሚነፍሰዉ ነፋስ አይሏል፡፡እርስዎን አምኖና ተመክቶ በየአደባባዩ የልቡን እየተናገር የቀን ጅቦቹን በመቃወም ላይ ያለዉ ህዝብዎ ላይ ከባድ አደጋ አንዣቦበታል፡፡ኢንጂነር ስመኘዉን በአደባይ ለመግደል ያልፈሩ ሰዎች የኔ ቢጤዉን ተራ ዜጋማ ምን ሊያደርጉት እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነዉ፡፡በሰላም ከቤታችን ወተን በሰላም ወደ ቤታችን ለመመለሳችን ምንም ዋስትና የለንም!!

ዶ/ር አብይ ሆይ ዛሬ ደግሞ እኛን ላለማስጨረስ ሲሉ እንደ እባብ ብልህ መሆንዎን ያሳዩን!!

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የጥፋት እሳት እየተንበለበለ ብዙዎቹን እየፈጀ ነዉ፡፡አሁን ጅግጅጋ ላይ የምንሰማዉ ነገር የሚያስለቅስና የሚያሳዝን ነዉ፡፡ዛሬ እሳቱ የሚንቀለቀለዉ ጅግጅጋ ላይ ይሁን እንጂ ወናፉ ያለዉ የትና እነማን እጅ እንደሆነ አሳምረዉ ያዉቃሉ፡፡ይሁን እንጂ ዛሬም ዝምታን መርጠዋል፡፡ወናፉን ይዘዉ እሳቱን የሚያቀጣጥሉትን ግለሰቦች አስረዉ እስካላስቆሟቸዉ ድረስ ጅግጅጋ ላይ የሚቀጣጠለዉን እሳት ዛሬ ተረባርበዉ ቢያጠፉትም ነገ ደግሞ አፋር ላይ ወይም ሌላ ቦታ የከፋ እሳት መነሳቱ አይቀርም፡፡

አንዳንዴ የዋህነትዎና ዝምታዎ ሲበዛብኝ እኒህ ሰዉዬ ህዉሃትን በጾም በጾለት አስረዉ ጸጥ ለማሰኜት አስበዉ ይሆን እንዴ ስል የጅል ሃሳብ አስባለሁ፡፡ምን ላድርግ?እንጂማ ከዚህ በላይ ምን እስኪፈጠር ድረስ ነዉ የሚጠብቁት? ዛሬም በለዉጥ ስም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መገበር አለብን እንዴ?እባክዎትን ዶ/ር አብይ እንዳያስጨርሱን!!

እዉነት ግን እስከመቼ ድረስ ነዉ እንደ እሳት አደጋ መኪና እሳት ወደ ተነሳበት ቦታ ሁሉ እየሮጡ እሳት ሲያጠፉ የሚኖሩት? ከዚህ ሁሉ ለምን በየቦታዉ እየዞሩ ብር እየበተኑ እሳት የሚጭሩትን ሠዎች ለቃቅመዉ አስረዉ ይችን ሃገር አይገላግሏትም!

የዋህና መሃሪ መሆንዎን ያለፍትህ የታሰሩ ወገኖቻችንን በመፍታት እንዳሳዩን ሁሉ አሁን ደግሞ ህገ ወጦችን በማሰር ፍትሃዊ መሆንዎን ያሳዩን፡፡

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በ2016 የተቃጣባቸዉን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ከጉዳዩ ጋር ንክኪ አላቸዉ ብለዉ የጠረጠሯቸዉን በአስር ሺ የሚቆጠሩ የመንግስት ሰራተኞችን አባረዉ፣በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቱርካዊያንን ደግሞ ከያሉበት ለቃቅመዉ ዘብጥያ አዉርደዉ ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል፡፡

እርስዎ ግን በእርስዎ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገብዎትን ሰዎች ማንነት እያወቁ እንኳ ምንም እርምጃ ሳይወስዱ ቀሩ፡፡ሰላም ወዳድነትዎ ቢያስደስተንም ህግና ፍትህን ለማስፈን የሚወሰድ ማንኛዉም እርምጃ ግን ስህተትና ኃጢያት እንዳልሆነ የረሱት ይመስላልአንድ አብይ ቢሞት ሺ አብይ ይተካል ማለትዎ እዉነት ቢሆንም በዚህ ወቅት እርስዎ ማጣት ግን ብዙ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል ሊያዉቁት ይገባል፡፡ይቺ ሃገር እርስዎን የመሰለ መሪ ለማግኘት ግማሽ ምዕተ ዓመት ጠብቃለች፡፡በእርስዎ ዳተኝነት የተነሳ ይህን ዕድል መልሰን ልናጣዉ አይገባም፡፡ስለዚህ ለህዝቡ ሲሉ ከመሞት ለህዝብ ሲሉ ቢኖሩ ይቺን ሃግር እንደሚጠቅሟት ምንም አያጠራጥርም፡፡ ሌላ አምሳ ዓመታት መጠበቅ አይኖርብንም!!

ስለዚህ እርስዎም እንደ ኤርዶጋን እርምጃ ይዉሰዱ!! የተፈለገዉ መስዋዕትነት ተከፍሎ እነዚህ ሰዉ በላ ጭራቆች ከያሉበት ለቃቅመዉ ይሰሯቸዉ፡፡ በየደረጃዉ ያሉ ባለስልጣኖችን ከቀበሌ እስከ ዞን፣ከዞን እስከ ክልል፣ ከክልል አስከፌደራል ያሉ ለፍርፋሪ ያደሩና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮችን በሙሉ በቁጥጥር ስር ያዉሏቸዉ፡፡

የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ አይደለም በመቶ ሺዎች ቀርቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች ይቺ ሃገር እስትረጋጋ ድረስ ቢያስሩ ማንም አምባገነን እንደማይልዎት ይመኑኝ፡፡ግድየለዎትም ለሚዎዱትና ለሚዎድዎት ህዝብ ደግ ለመሆን ሲሉ ጨካኝ ይሁኑ፡፡አዎ!! መቶ ሺህ የለዉጥ አደናቃፊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋልዎ ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ ደህንነት እስከበጄ ድረስ አለሙ እንጂ አጠፉ የሚልዎት ጤነኛ ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡

እርግጥ ነዉ የሚወስዱት እርምጃ ሁሉንም ሰዉ እንደማያስደስት ግልጽ ነዉ፡፡ተነካሁ ያለ ለጊዜዉ ለንቦጩን ሊጥል ይችላል፡፡መብቱ ነዉ፡፡ ነገር ግን ወደፊት ሁሉም ነገር ሲገለጥለት የእርስዎ ዉሳኔ ልክ እንደነበር በርግጥ ይገባዋል፡፡

እናም ዶ/ር አብይ ሆይ ሞተን ከማለቃችን በፊት እባክዎን ዛሬ እንኳ እንደ እባብ ብልህ ይሁኑና የህዝብና የሃገር ጠላቶችን ሰኮን ሰኮናቸዉን እየቀጠቀጡ ሽባ ያድርጓቸዉ፡፡

ያኔ ሁላችንም እፎይ ብለን እንቅልፋችንን እንተኛለን!!!

Filed in: Amharic