>

የብሔሮች አብይ ጾም መቼ ነው? (ደረጄ ደስታ)

የብሔሮች አብይ ጾም መቼ ነው?
ደረጄ ደስታ
* ከሚተኩሱብን ስንት ጠቃሚ ነገር እንዲተኩሱልን እምንጠብቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ የብሔር ብሔረሰብ ልፊያና ኩርፊያ እንቶፈንቶ መባከናቸው አይቀርም። 
እንደ ታላላቆቹ የክርስትናና እስልምና ጾሞች ከክፉ ቃልና አስተሳሰብ ጭምር ታቅበን እምንውልባቸው የተወሰኑ ቀናትና ወራት ቢኖሩን ምንኛ በጸደቅን። በተለይ በተለይ ለአንዲት ቀን እንኳ ኦሮሞ አማራ ትግሬ ምንትስ ብለን አንዲት ቃል ሳይወጣን ስለ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ትምህርት፣ ጤና፣ ብልጽግና፣ ፖሊሲ፣ ዴሞክራሲ ወዘተ እየተከራከርን እምንውልበት ቀን ይኖረን ይሆን? ወይስ ዝባዝንኬ እማናወራበት ለአንዲትም ቀን ልቀን ከላቀው እምንገኝበት ብሔራዊ ቀን ይታወጅልን? ለጽድቁም ቢሆን እኮ ፣ በብሔርተኞች ፖለቲካ፣ ጅጅጋ ላይ ተጎድተውና ተፈናቅለው የእርዳታ ያለህ እሚሉ ወገኖችን ጩኸት መስማት እንኳ አቅቶን ሌላ ሌላውን እናወራለን።
 በዚህ የተማረረው የፌስቡኩ ትንታጉ አፈንዲ ሙተቂ  “በዘበዛ ሁላ!” እያለ ሲራገም ሰማሁት። ሰሜንና ደቡብ ምስራቅና ምዕራብ እየወረደ ስለ ህዝቦችና ከተሞች ስለታላላቅ ሰዎቻችንና ክስተቶች ድንቅ የኢትኖግራፊክ ምርምር ጽሑፎችን እንኳ እሚያስነብበን አፈንዲ በፖለቲካው ተጠምዶ ሳየው ትልቅ ብክነት መሰለኝ። ስንት ሰው ስንት ባለሙያ ባክኗል። ከሚተኩሱብን ስንት ጠቃሚ ነገር እንዲተኩሱልን እምንጠብቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ የብሔር ብሔረሰብ ልፊያና ኩርፊያ እንቶፈንቶ መባከናቸው አይቀርም።
ወይ በቃ የብሔር ብሔረሰቦች ወሳኝ ውድድር ተደርጎ ፣ “ጀግናው አይበገሬው ታላቁ ሊቁ ብሔረሰብ ዋንጫ አንስቶ ካልታየ ሞተን እንገኛለን” እምትሉ ወገኖች፣ አንድ ሰፊ በረሃ ወይም ሜዳ ይፈለግላችሁና፣ እዚያ ወርዳችሁ እምትደራረጉትን ተደራርጋችሁ፣ ጨርሳችሁም ሆነ ተጨራርሳችሁ ስትጨርሱ ንግሩን። እኛ እስከዚያ መንገዱን ክሊኒኩን ትምህርት ቤቱን መብራቱን ቴክኖሎጂውን ገንብተን እንጠብቃችሁ! አብይም ይህን የአብይ ጾም ጊዜ ቢያውጁልን ምን ይመስልዎታል?!
Filed in: Amharic