>
4:14 am - Friday February 3, 2023

ታዬ ደንድኣ….. የከሳሹ መሥሪያ ቤት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ሆነ!!! (በውብሸት ሙላት)

ታዬ ደንድኣ የከሳሹ መሥሪያ ቤት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ሆነ!!!
በውብሸት ሙላት
ታዬ… ለአንድ ድግሪ 16 ዓመታት…..
ታዬን የማውቀው በ1995 ዓ.ም. ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች ነበርን፡፡ የሕግ ደግሞ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ሆነን፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ እየተማርን!
እኔና ታዬ ጠበቅ ያለ ነው ባይባልም  ትንሽ ትንሽ ብቻ የምንቀራረብ የክፍል ጓደኞች ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ እንጋባባ ነበር፡፡ እናም በአንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡
በ1995 ዓ.ም፣. ሁለተኛ ሴሚስተር ላይ የሕገ መንግሥት አስተማሪያችን “የፌደራል ሥርዓቱ እንዴት መዋቀር፣መቀረጽ አለበት?” የሚል ይዘት የነበረው የክርክር ርእስ በማቅረብ አራት ተማሪዎች እንድንከራከር ተወሰነ፡፡ በአንድ በኩል ታዬ ደንድኣ እና አወል ቃሲም (አሁን ዶክተር) ሆኑ፡፡ ከብሔር አንጻር ሁለቱም ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እኔና ዳኛቸው አስራት፡፡ እኔ አማራ፣ዳኛቸውም የአዲስ አበባ ልጅ ነው፡፡
ለክርክሩ ዳኛ ተሰየመ፡፡ ከ100 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ታደሙ፡፡ ከሁለት ሴክሽን፡፡ ዝርዝር የክርክር ነጥቦችን ባላስታውሳቸውም አወልና ታዬ አሁን በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን አወቃቀር ደግፈው ቀረቡ፡፡ እኔና አጋሬ ደግሞ  አሁን ያለው አወቃቀር ተገቢ አይደለም በማለት በዋናነት መልክአ ምድርን መሠረት ያደረገ አወቃቀር መከተል አለብን አልን፡፡ በተለይ እኔ ደግሞ የፕሮፌሰር መሥፍንን “ ኢትዮጵያ ከየት ወደ የት?“ የምትል አነስ ያለች መጽሐፍ አነበብኩና እንዴት በመልክአ ምድር መከፋፈል እንዳለባት ተናገርኩ፡፡
እንግዲህ ሕግ ተምረን ያጠናቀቅነው  ለአንድ ሴሚስተር ብቻ ነው፡፡ ከኑሮየም ይሁን ከንባቤ ብዙም ስለብሔሮች መብት እና አማራጭ የፌደራል አወቃቀር አቅርቤያለሁ ማለት አይቻልም፡፡
ታዬና አወል ደግሞ ቢያንስ ልምዳቸው ስለብሔር መብት አሳውቋቸዋል፡፡ የዳኛው ውሳኔ ያኔ ባይገለጽም፣ አሁን ላይ ሆኜ ወደ ኋላ ሳስበው የነታዬ መከራከሪያ ቢያንስ ተጨባጭ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የእኔና ጓደኛዬ በዋናነት ያሳሰበን የኢትዮጵያ አንድነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እነ ታዬ ደግሞ በዋናነት የብሔር መብት ነበር፡፡
ከዚያም ትምህርት ቀጠለ፡፡ ታዬ ግን ትምህርቱን አልቀጠለም፡፡ ታዬ ታሰረ፡፡ ሌሎች አራት ወይም ከዚያ ያለነሱ ኦሮሞ የክፍል ጓደኞቻችንም ጭምር ታሰሩ፡፡ በኦነግነትም ተፈረጁ፡፡ ትምህርታቸውንም አቋረጡ፡፡ እኛ ግን ትምህርታችንን ቀጠልን፡፡
ታዬ ተፈታና ትምሀርት ጀመረ፡፡ ያኔ፣ እኛ የሌላ ዓመት ተማሪ ሆነናል፡፡ ከዚያ ደግመ ታሰረ፡፡ ታዬ፣ሲፈታ ትምህርቱን እየቀጠለ፤ ሲታሰር ደግሞ እያቋረጠ ኖረ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ በ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ ድግሪውን ያዘ፡፡ በ1993 ዓ.ም. የጀመረውን ትምህርት በ16 ዓመቱ አጠናቀቀው፡፡
የአገዛዝ ሥርዓቱ ታዬን ምን ያህል እንደበደለው እና እንዳሰቃየው ሌላ ማስረጃ አያስፈልገውም፡፡ ታዬ ግን የመርህ ሰው ነው፡፡ የማይናወጥ አቋም ያለው፡፡ ማረሚያ ቤት እያለም መጽሐፍት አሳትሟል፡፡
ታዬ፡ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትን፣ታዋቂ ሰዎች እና አርቲስቶችን ያካተተው  ቡድን ውስጥ ሆኖ ወደ አማራ ክልል በመጓዝ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን በአማራ ክልል ቴሌቪዥን በመቅረብ የሚገርም አስተያየት ሲሰጥ ተመለከትኩት፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት፣ስለአብሮነት፣ስለአንድነት፡፡ ታዬን ሥርዓቱ ቢጎዳውም ቢያሰቃየውም እጅግ የሚገርም እና ምንም የማይነቀንቀውን የኢትዮጵያዊነት ስሜቱን አካፈለን፡፡
ሥርዓት ያልፋል፡፡ አገዛዝ ይቀየራል፡፡ ሕዝብ ግን ሁልጊዜም ይኖራል፡፡ በዚሁ ዓመት እንኳን በአገዛዙ ተበድሎ፣ልጅነቱን (ወጣትነቱን) በማሰር ቀምቶት እንኳን ስለ ኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ አንድነት፣ አብሮነት ለመመስከር በአማራ ክልል ቴሌቪዥን ሐሳቡን አካፍሏል፡፡
ታዬ ደንድኣ የኦሮሚያ ክልል የፍትሕ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሆነ፡፡ ነገር ግን ታዬ ከኅሊናው ውልፍት (ዝንፍ) ማለት አይሆንለተምና በኦሮሚያ ክልል የተደረገውን ሕገ ወጥ ተግባር ተናገረ፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ክልሎች መግለጫ እንዳይሰጡ ከለከለ፡፡ ከልክሎ ግን ሰው እየተገደለ ነበር፡፡ ታዬ እውነቱን ተናገረ፡፡
ታዬን ማሰር ልማድ ያደረጉ ሰዎች በዚህ ዓመትም አሰሩት፡፡ ጥሩነቱ ወቅቱ ተቀሯል፡፡ ተፈታ፡፡ መስሪያ ቤቱን መልሶ ተቀላቀለ፡፡
አሁን ደግሞ ለስንት ጊዜ ሲከሰው የነበረው ፍትሕ ሚኒስተር (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነ፡፡ የትግል ውጤት ነው!
ታዬ ብርቱም ብረትም ቀናም የፍትህ አርበኛ ኢትዮጵያዊ ነው!
ታዬ ደንድኣ – እንኳን  ደስ አለህ!
Filed in: Amharic