>
6:08 pm - Friday August 19, 2022

ሰፊ ህዝባዊ መሠረት ያለው አገር አቀፍ ፓርቲ በመቋቋም ላይ ነው!!! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ሰፊ ህዝባዊ መሠረት ያለው አገር አቀፍ ፓርቲ በመቋቋም ላይ ነው!!!
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
እስከ ሐምሌ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ በቁጥር ከ50 (ሃምሳ) በላይ የሚደርሱና ከዚህ በኋላ ቁጥራቸው እንድሚጨምር የሚጠበቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ምሁራን አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ በማቋቋም ላይ ናቸው፡፡ የሚቋቋመው ፓርቲ ሁሉን አቀፍና ሰፊ ህዝባዊ መሠረት የሚኖረው ሲሆን አደራጆቹ ከአዲስ አበባ፣ ከጅጅጋ፣ ከቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ከአፋር፣ ከድሬደዋ፣ ከሃረር፣ ከደቡብ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራና ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ የአደራጆቹ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፆታና ሙያዊ ስብጥር ኢትዮጵያን ከምሥራቅ እስከምእራብ ከሰሜን እስከደቡብ ሊወክል የሚችል ሲሆን፣ አደራጆቹ ባገኙት አበረታች ውጤትም በአሁኑ ሰዓት ስለፓርቲው ምስረታ ለህዝብ ይፋ እናድርግ ወይስ እንቆይ በሚለው ጉዳይ ላይ እየተነጋገሩ  ይገኛሉ፡፡
 የፓርቲው አደራጆች በሞያ ዘርፍና በፖለቲካ ልምድ ረገድ ከዚህ በፊት በተቃውሞ ፖሊቲካ ውስጥ ረጅም ልምድና ተቀባይነት ያላቸውና አዲስ ነገር ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅጡ የተረዱና ማብራራት የሚችሉ እንዲሁም አስፈላጊው ከፍተኛ ተነሳሽነትና የሃላፊነት እንዲሁም የአገር ፍቅር ስሜት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው።  በሙያቸው ስብጥር የሕግ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የዓለማቀፍ ግንኙነት፣ የፖለቲካ ሳይንስ አዋቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የህዝብ ግኑኝነትና ኮሚዩኒኬሽንስ ባለሞያዎች፣ ጦማሪያን፣ የዩኒቨርስቲ መምህራንና መሰል ባለሞያዎችን ያካተቱ ናቸው።
ይህ ፓርቲ ኢህአዲግንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን በሚገባ መገዳዳርና ተፎካክሮ ሊያሽንፍ የሚችል ሲሆን ስያሜውን በተመለከተም ፓርቲው የሚከተለውን ርእዮተ-ዓለም፣ ዓላማና ግቡን በበቂ ሁኔታና በትክክል የሚገልጽ መሆን እንዳለበት በዚህ ሳምንት አደራጆቹ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተወያያተዋል፡፡ በዚህም መሠረት “የኢትዮጵያ ነፃ ተራማጅ ፓርቲ/ Ethiopian Liberal Partyˮ የሚለው ስያሜ የፓርቲውን ርእዮተ-ዓለም፣ ዓላማና ግብ የሚገልጽ ሆኖ በመገኘቱ በዚሁ ስያሜ ሊቀጥል ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪ “የኢትዮጵያ ነፃ ተራማጅ ፓርቲ/ Ethiopian Liberal Progressive Partyˮ እስከዛሬ በተቃውሞው ትግል (በተለይ በአንድነቱ ጎራ) ያልተካተቱ ወይም አንዳልተካተቱ ስሞታ ሲያሰሙ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ከጅምሩ ተሳታፊ ለማድረግ፣ በጋራ ብሄራዊ ወይም አገር-ዓቀፍ አጀንዳ ለመቅረፅና የኢትዮጵያን አንድነትም ለማጠናከር ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
ይሁንና የአደራጆቹ ስብጥር በማንነት “ኮታ” ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ይልቁንስ የፖለቲካ ብቃትን፣ የለውጥ ፍላጎትንና የትግል ተነሳሽነትን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም አደራጆቹ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን (አብዛኞቹ ከዚያ በላይ የት/ት ደርጃ ያላቸው ሆኖ) የኢትዮጵያን ፖለቲካ (ሁሉም ማለት ይቻላል) በቅርበትና በጥልቀት መረዳት፣ መገምገም፣ መተንተንና ደርዝ ባለው መንገድ መግለፅ የሚችሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህም ፖለቲካን ለ”ብሶትና ለ”እልህ” መወጫነት ከመጠቀም ባሻገር ተግባራዊና አገር-አቀፍ ለውጥ ለማምጣት፣ እንዲሁም በጭፍን “ፍረጃ”ና በ”ጠላትነት” ስሜት ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ ባህል ለመቀየርም እንደሚረዳ ከፍተኛ እምነት ተጥሎበታል፡፡
በተነሳው በዚህ የፓርቲ ርእዮተ-ዓለምና መርህ ላይ ተመርኩዞ  “የኢትዮጵያ ነፃ ተራማጅ ፓርቲ/ Ethiopian Liberal Progressive Partyˮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ቅፅ በመውሰድ በመላ አገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመሥራች አባላት ፊርማ ማሰባሰብ ጀምሯል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ አንድነት በፅኑ የሚያምኑ፣ የዜጎችን እኩልነት የሚያከብሩ፣ በዘር/በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መነሻዎች በሰዎች መካከል ልዩነትና አድሎ የማያደርጉ፣ ከግል ፍላጎታቸው ይልቅ የአገርንና የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙ፣ ለአገራቸው በጎ/ቅን አሳቢዎች፣ የእምነት፣ የሀሳብና የአመለካከት ልዩነቶችን በትዕግስት ለማስተናገድ ዝግጁ የሆኑ፣ ከማንኛውም የጥላቻ፣ የቂመኝነትና የበቀል ስሜት የፀዱ፣ በአገር ጉዳይ ላይ የግል ተነሳሽነት፣ ቅንነትና የዓላማ ቁርጠኝነት ያላቸው፣ ከግል ስሜት በላይ አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት የሚሰማቸውና የፖለቲካ ዲስፕሊን ያላቸው ወይም የፓርቲ ደንብና ዲስፕሊን ሊያከብሩ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በመሥራች አባልነት እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል፡፡
አደራጆቹ የፓርቲ ምሥረታ ሥራውን በደመ-ነብስ አልገቡበትም፡፡ ይልቁንም የፓርቲውን ምሥረታ ሂደትና ጠንካራ መሠረት ያለው ፓርቲ ለማቋቋም መከናወን ያለባቸውን ተግባራትና የአሠራር ስልቶች በግልፅ የሚያሳይ ፍኖተ-ካርታ (roadmap) ተዘጋጅቶ በአደራጆች ጠቅላላ ስብሰባ   እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የመሥራች አባላት ፊርማን ከማሰባሰብ በመለስ፣ ሌሎች ልዩ ልዩ የቅድመ-ፓርቲ ምሥረታ ተግባራትን ለማከናወን በአደራጆች ጠቅላላ ስብሰባ የተመረጡ 15 (አሥራ አምስት) አባላት ያሉት አስተባባሪ (አብይ) ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን በሥሩም የሚከተሉት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ፣
የረቂቅ ፕሮግራም ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ፣
የረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ፣
የመሥራች አባላት ፊርማ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ፣
የፋይናንስ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ፣
የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ፣
የፖሊሲ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ፣
የሴቶች ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ፣
የአቅም ግንባታ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ፣
የመረጃ አሰባሰብ፣ ትንተናና ጥንቅር ንዑስ ኮሚቴ፣
የውጭ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ፣
የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ፣
ምናልባትም ከፓርቲ ምሥረታ ጋር በተያያዘ እስካሁን ከተለመደው አሠራር ወይም ከነበረው ግንዛቤ በመነሳት፣ ፓርቲው ከመመሥረቱ በፊት ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ንዑሳን ኮሚቴዎችን ማቋቋም ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን፣ በአደራጆች ጠቅላላ ስብሰባ በፀደቀው ፍኖተ-ካርታ መሠረት፣ ሁሉም ንዑሳን ኮሚተዎች ግልፅ የሥራ ድርሻ መዘርዝር (job description) ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ይህም የሚቋቋመው ፓርቲ መሥራች ጉባኤውን አካሂዶ መደበኛ እንቅስቃሴውን ሲጀምር ከባዶ እንዳይነሳ፣ ብሎም ጥሩ መሠረትና ግልፅ መንገድ/መርህ እንዲኖረው ያግዘዋል ከሚል እምነት የመነጨ ነው፡፡
ይሁንና፣ በንዑሳን ኮሚቴዎቹ መካከል የተደረገው የሥራ ክፍፍል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንዳስፈላጊነቱ የሁሉንም አደራጆች ንቁና የጋራ ተሳትፎ የሚጠይቁ ጉዳዮች መኖራቸውም እሙን ነው፡፡ በተለይም በፓርቲው ረቂቅ ፕሮግራም ቀረፃና ዝግጅት ላይ ሁሉም አደራጆች በጥናት የተደገፉና ምሁራዊ ትንተናን የተንተራሱ ሀሳቦች በማቅረብ ላይ ሲሆኑ በውጤቱም የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ እምነትና ፍላጎት ግንዛቤ ውስጥ ያስገባና፣ ይህንኑ መሠረት ያደረገ አገራዊ አጀንዳና የጋራ ራዕይ ለመቅረፅ እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡
ይህን ሁሉ የምናደርግበት ዓላማ አለን፡፡ ዓላማችን አሁን በአገራችን አሉ የሚባሉ (በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ) ፓርቲዎችን ቁጥር በአንድ ከማሳደግ ባሻገር ነው፡፡ እንደተለመደው በትንሽ በትልቁ የፖለቲካ እንካ-ሰላንቲያና አተካራ ውስጥ በመግባት አጉል ትኩረት ለመሳብ በመሞከር ላይ የተመሠረተና ግልብነት የሚያጠቃው የትግል ስልትና ስትራቴጂም የለንም፡፡ ምርጫን ተደግፈን መድረክ በማግኘት “በአቋራጭ እውቅናን ማትረፍ” በሚል አጭር እይታ የተገደበ ግብም የለንም፡፡ የገዥውን ፓርቲ ድክመቶችና ክፍተቶች ነቅሶ በማውጣት፣ አጉልቶ በማሳዬትና በመተቼት ብቻም ህዝብ እንዲመርጠን አንሻም፡፡ እኛ ከዚያ ባለፈ፣ የራሳችን የፖለቲካ አጀንዳና፣ ከገዥው ፓርቲ ላይ ነቅሰን ላወጣናቸው ችግሮችም አማራጭ መፍትሔ ይዘን መቅረብ እንፈልጋለን፡፡ ስለሆነም ገዥው ፓርቲ የሚጥልልንን የአጀንዳ ፍርፋሪ እየጠበቅን እንደዶሮ በመንጫጫት ህዝብን ማንደንቆርና እንደዋዛ ጊዜ ማጥፋት አንፈልግም፡፡
እኛ ህዝቡ አወዳድሮ ለመምረጥ የሚያስችሉት የተሻሉ አማራጮች እንዲኖሩት እንፈልጋለን፡፡ ህዝቡ የተሻለ አማራጭ የማይቀርብለት ከሆነ ደግሞ ያለውን ይዞ ቢቀጥል እንደሚሻለው እናምናለን፡፡ በእኛ እምነት የአገርና የህዝብ ጉዳይ ከፓርቲና ፓርቲን ከሚመሩ ግለሰቦች ፍላጎት በላይ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም የፓርቲንና ግለሰብ መሪዎችን ፍላጎት ከማርካት ባለፈ፣ የተሻለ አማራጭ ሆነን/ይዘን ለመውጣት ጠንክረን/በትጋት መሥራት እንዳለብን እናምናለን፡፡ እናም አገርና ህዝብን መምራት በሚያስችል ቁመና ላይ መሆናችንን ማረጋገጥና በተግባ ማሳየት እንዳለብን በግልፅ እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም በተገኘው መንገድ ሁሉ የፖለቲካ ሥልጣን ከመያዝ ባለፈ፣ አገርና ህዝብ የሚመካበት ፓርቲ/ተቋም የመገንባት አገራዊ ግብና ራዕይ አለን፡፡ በርግጥ ይህን ግብ ከዳር ለማድረስና ራዕያችንን ዕውን ለማድረግ፣ መንገዱ አስቸጋሪና ጊዜውም ሩቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን፣ ይዘን የተነሳነው ብሄራዊ ራዕይ የማይደረስበት ግብና የማይሳካ/እውን ሊሆን የማይችል አይደለም፡፡ የምናስቀምጣቸው ግቦች ሊሳኩ የሚችሉና ራዕያችንን ዕውን ለማድረግ የሚያንደረድሩን ናቸው፡፡
ስለሆነም፣ ኑ! ይህን አገራዊ ግብ አብረን እናሳካ፤ የጋራ ራዕያችንን እውን እናድርግ!!!
Filed in: Amharic