መስፍን ነጋሽ
በረከት ስምዖን በ“ታዲያስ አዲስ” ከሰይፉ ፋንታሁን እና በጀርመን ድምጽ ከነጋሽ መሐመድ ጋራ ያደረጋቸውን አጫጭር ቃለ ምልልሶች አደመጥኳቸው። መቼም ከሰይፉ ጋራ ያደረገው ቃለ መጠይቅ በራሱ በበረከት አነሳሽነት የተደረገ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ሰይፉንም በረከትንም እናውቃቸዋለን፤ ከብዙ በጥቂቱ! ብሎ ሐተታ እንደማሳጠር። የነጋሽ ቃለ ምልልስ በብአዴን ውሳኔ ወይም በሰይፉ ቃለ መጠይቅ ንሸጣ የተጀመረ ሊሆን ይችላል፤ ይህም ግምት ነው። የሁለቱም ቃለ ምልልስ አላማው ተመሳሳይ ነው፤ በብአዴን አመራር ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን መጀመር እና መጽሐፉን ማሻሻጥ ነው። ሁለቱም የሚያጓጓኝ ጉዳይ አይደለም።
በቃለ ምልልሶቹ፣ በረከት መጽሐፉን የጻፈው “ሙግት ለመቀስቀስ” እንደሆነ ገልጾ “በኢትዮጵያ ጉዳይ በአጀንዳዎች ላይ መነጋገር አለብን” ይላል። በነጻነት ስለመከራከርም ያወራል። ይህ ንግግር ከበረከት አፍ ሲደመጥ፣ በሰሚው ጎሮሮ ኡኡታና እልልታ ቀደሞ ለመውጣት ሲሽቀዳደሙ ትንፋሽ ያሳጣሉ፤ ማን ቀድሞ ሊወጣ?! ደግነቱ፣ ኡኡታውም እልልታውም ለስላቅ ነው።
በአገሩ ላይ የተለየ ሐሳብና መረጃ እንዳይሰማ፣ ለሃያ ዓመታት የሰፈነ የአፈና ስርዓት የዘረጋው ሰውዬ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ “በአጀንዳ ላይ” ስለመነጋገር የሚሰብክ፣ በበረሃ-ኢሕአዴግ የሚንከራተት ሰሚ ያጣ ነቢይ ሆኖ መጣ። ነቢይ የበዛበት ዘመን! በመጨረሻም፣ “ከሚናደው ተራራ” ስር ሆኖ ከአለቃው የሰማቸውን አጀንዳዎች ጻፈልን፤ እነወያይባቸው ዘንድ። ኡኡታ እና እልልታ ግርርርር ብለው ወጡ።
“በአጀንዳ፣ በፍልስፍና፣ በፖሊሲ መግጠም” ተገቢ መሆኑን በመጥቀስ የብአዴንን አመራር ይተቻል። የብአዴንን አመራር በጥልቀት አላውቀውም፣ የእነርሱ ሽኩቻ አያገባኝምም። ሆኖም፣ በረከት ምናልባት “ከእነርሱ እሻላለሁ” (ይሻል አይሻል አላውቅም) የሚል ምስል ለመፍጠር አስቦ ካልሆነ በቀር፣ እርሱን የምናውቀው “በአጀንዳ፣ በፍልስፍና፣ በፖሊሲ” እንግጠምህ ያሉትን ቀርቶ የሰነዘሩትን ሁሉ በጅምላም ይሁን በተናጠል ሲያሳስር፣ ሲያሸማቅቅ፣ በመንግሥት ሚዲያ ጭምር ስም ሲያጠፋና ሲያስጠፋ፣ በፈጠራ ክስ ሲከስና ሲያስከስስ፣ ሲያሳድድ መኖሩን ነው። ይኼ ደሞ በወሬ የሰማነው አይደለም፤ በዐይናችን ያየነው፣ አንዳንዶቻችንም የኖርነው ነው። ይህንን ሸፍጥና ግፍ ሲፈጽም ትእዛዙን በወረቀት እየጻፈ፣ በደብዳቤ እየበተነ ስላልነበረ፣ ዛሬ ደርሶ “በግሌ የፈጸምኩት በደል የለም” ብሎ እነደሚሸመጥጥ የሚገመት ነው። ድርጅት በሚባል ታቦት ስር ተደብቆ፣ የሕሊናና የሕግ ተጠያቂነትን አሽቀንጥሮ መጣል ከነበረከት የፖለቲካ አዕማደ ምሥጢራት አንዱ ስለሆነ እንግዳ አይሆንብንም። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ፣ ሌላው ቀርቶ የግፉ ሰለባ የሆኑ ጋዜጠኞች ብቻ በጥራዞች የሚሰደር “ገድሉን” ይተርኩ ነበር፤ ትሑት ሕሊና እንዳለ ቢጠረጥሩ ኖሮ። አይጠረጥሩም!
በረከት፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በብራሰልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆን ጠይቆት እንዳልተቀበለም ተናግሯል። መቼም ለዚያ ሹመት ያንሳል አልልም፤ ደሞ ለኢትዮጵያ አምባሳደርነት! ቀልቤን የሳበው ግን ሹመቱን ካልተቀበለባቸው ምክንያቶች አንዱ ያለውን ሲገልጽ “ከኢትዮጵያ ውጭ መኖር አልችልም…. ፍጥረቴ እርሱ ነው” ማለቱ ነው። ምናልባት፣ እውነተኛ ስሜቱ ሊሆን ይችላል። ለራሱ እንደዚያ የሚያስብ ሰው፣ ይቃወሙኛል የሚላቸው ሰዎች ከመታሰርና ከመሰደድ ውጭ ምርጫ እንዳይኖራቸው ማድረግን የአስተዳደር ዘይቤው አድርጎ ሃያ ዓመት መዝለቁ እርግማን ይሆን ወይስ በሽታ? ከነግፋቸውም ቢሆን፣ በረከትም ሆነ ጓዶቹ እንዲሰደዱ አልመኝላቸውም።
ለነገሩ፣ ዛሬ ባለው ሁኔታ፣ ባህር ዳር እና ደብረ ማርቆስ እንኳን ለመሔድ የማይችል እስረኛ ሆኗል። በነደመቀ/ገዱ ላይ ያለውን የክስ ማስረጃ ያዳበረ መስሎት ችግሩን በሙሉ አሁን ባለው የብአዴን አመራር ላይ ለመደፍደፍ ደፈረ እንጂ፣ የዛሬውን እውነታ በመሠርቱ የፈጠረው መለስና እርሱ የመሩት የሚኩራራበት አስተዳደር ነው። የከተሜ ወይም የተደባለቀ ማንነትና ባህል አለ፣ የወላጆቻችንን ብሔረሰብ ስነልቦናና ባህል በሙሉ አንጋራም ወዘተ ስንል፣ የደም ጥራት ልክፍት በተጠናወተው አስተምህሯችሁ ስትዘልፉን ከርማችሁ፣ ዛሬ ያሰለጠናችኋቸው የብሔር ማንነት ጥራት ደረጃ መዳቢዎች የእናንተን ፋይል ሲመረምሩ መደንገጣችሁ ከምን መጣ? “ከዚህ ተወልጄ፣ እዛ መንደር አድጌን፣ ስነልቦና ጂኒ ጂቡቲን” ምን አመጣው? የዘሩትን ማጨድ ነው እንጂ፣ ዘግይቶ የመጣውን ማሳ ጠባቂ መክሰስ ምን ይረባል? ለማዘንም አልተመቻችሁን!
በረከት ቀልደኛ ነው። በ2006 የሰብአዊ መብት ጥሰት አሳስቦት ለደመቀ መኮንን እንደነገረውም ገልጿል። በረከትን ያሳሰበ የመብት ጥሰት እኮ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው ማለት ነው። ቢቸግረኝ፣ ሰውየው በፈረንጅ ቀን አቆጣጠር እያወራ ይሆን ብዬ ራሴን ጠየኩት። እንደዚያማ አይሆንም። በፈረንጅ ከሆነ መለስ በሕይወት እያለ መሆኑ ነው። እርሱ እያለ ደሞ በረከትን የሚያሳስብ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞ አያውቅም። ስለዚህ የዛሬ አራት ዓመት ገደማ መሆኑ ነው። በኀይለማርያም ደሳለኝ ዘመን፤ ሁሉም ነገር በአንድ ምሽት መበላሸት በጀመረበት ዘመን! ይኼ እነደመቀ ላይ ነጥብ ለማስመዝገብ ካለሆነ በቀር ሰው ፊት የሚቀርብ ማስተዛዘኛ አይደለም። ታስሮ ፍርድ ቤት ሲቀርብ “ይቺ አገር ወደየት እየሔደች ነው” ብሎ ከተገረመው የቀድሞ ሹመኛ “ቀልድ” እንኳን የሚያንስ ጨዋታ ነው። በ97 “ባንክ ቤት ሊዘርፉ ሲሉ” የመገደላቸው ዜና በኢቲቪ የተነገረላቸው የአዲሳባ ልጆች እነማን ነበሩ?
ለማንኛውም፣ የሰሞኑ የብአዴን-በረከት-ኢቲቪ ድራማ በረከት ምጸታዊ ፍትሕ (poetic justice) በአደባባይ የተቀበለበት ይመስላል። “የፍትሑ” ምጸት በሁለት ወገን ነው። ለበረከት ለራሱም ሆነ ለሚከራከሩለት ሰዎች፣ “በረከት ሙስና ውስጥ የለበትም” የምትለዋ ሙግት እጅግ ቀዳሚዋ ነች። ከነአባባሉ “እሱ…. እንዲህና እንዲያ ቢያደርግም/ባያደርግም… በሙስና አይጠረጠርም” የሚል የኖረ የምከታ ስልት አለ። የምጸታዊ ፍትሑ አንዱ ምንጭ የብአዴን ክስ በረከት እጅግ የሚኩራራበትን “የንጹሕነት” ካባውን ለማሳደፍ የተወረወርች መሆኗ ነው። በሌላ ጉዳይ ቢያግዱት ይህን ያህል አሸማቃቂ አይሆንም ነበር። የሙስና ክሱ እውነት ሆነም አልሆነም ምጸታዊ ፍትሑ ተፈጽሟል። የክሱ ሐቅ ምንም ቢሆን፣ አይዞህ ለማለት አይመችም፤ እርሱም ይህንኑ ሲያደርግ ከርሟልና።
ሁለተኛው ምጸታዊ ፍትሕ ዜናው የተነገረበት ሁኔታ ነው። ኢቲቪ፣ የነበረከትን መታገድ በሰበር ዜና፣ በምሽት ስርጭቱ ዐቢይ ሰዓት አወጀው። የብአዴን ውሳኔ ሙሉ ዝርዝር እስኪደርስ፣ መሽቶ እስኪነጋ ድረስ እንኳን አልታገሱትም። ዜናው ከሌሎች በፊት በኢቲቪ ቀድሞ እንዲነገር የተደረገው ታስቦበት ይመስላል። ምናልባትም በረከትና ወዳጆቹ እንቅልፍ ሳይተኙ እንዲያድሩ፣ እንዲበሳጩ ታስቦም ሊሆን ይችላል። በረከት ኢቲቪንና ሌሎቹንም የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን እንዴት ሲጠቀምባቸው እንደከረመ ለሚያውቅ ሰው ቀልዱ ግልጽ ነው። በረከትና ተላላኪዎቹ፣ ኢቲቪን የብዙ ንጹሐንን ስም ለማጥፋት፣ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በሐሰት ለመወንጀል፣ ለማሸማቀቅና ለማስፈራራት፣ አልፎም ለመሳደብ፣ ለማዋረድና ለማንጓጠጥ ሲጠቀሙበት ኖረዋል። የኢቲቪ እና የበረከት ግንኙነት ከሞላ ጎደል ውሸት ከመፈብረክ እና ከአፈና ጋር የተያያዘ ነው። በዚሁ ጣቢያ፣ በሙስና ተጠርጥሮ መታገዱ፣ ደመቅ ብሎ ታወጀለት። በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ለዓመታት ያቋቋመው አሠራርና ባህል ስለሆነ ሊገረምም ሊናደድም አይገባውም። ይህን ማወቁ ግን “የፍትሑን” ምጸታዊነት የበለጠ ያጠልቀው ይሆናል እንጂ አያቀልለትም። በዚያው ልክ፤ ተመልካቾች ደግሞ የታሪክንና የሕይወትን ምጸት እናደንቃለን።
ምጸቱ ገና መጀመሩ ነው።