>

የሞያ ጓዶቹ በደም ከተጨማለቀ እጅ ቀለብ ሲሰፈርላቸው፣ እንደ ስሙ ትምኖ ለወገን የቆመው  ታማኝ በየነ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የሞያ ጓዶቹ በደም ከተጨማለቀ እጅ ቀለብ ሲሰፈርላቸው፣ እንደ ስሙ ትምኖ ለወገን የቆመው  ታማኝ በየነ!!!  
አቻምየለህ ታምሩ
* በጭካኔ የተገደሉት፣ የተሰደዱት፣ የታረዙት፣ በግፍ የታሰሩት፣ ጧሪ ቀባሪ ያጡት፣ በረሀ ለበረሀ ሲንከራረቱ የወደቁት፣ አውሬ የበላቸው፣ የውስጥ እቃቸው የተሸጠው፣ ባጠቃላይ የምስኪን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በደል ተጋብቶበት የእድሜውን ግማሽ ዘመን  የሕዝብ ድምጽ ሆኖ ወገኑን አገልግሏል
ኢትዮጵያውያን  በፋሽስት ወያኔ ጥይት እንደቅጠል  እየረገፉ በነበሩበት ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ስንት  ተስፋ የተጠለባቸው  የደስታቢስነት መንፈስ ተጠናውቷቸው  ከአገዛዙ ጋር ሰርግና ምላሽ ሲባጁ ታማኝ በየነ ግን ከሁሉ ባፈነገጠ  አኳኋን  አገሩ የጣለችበትን  ፋሽስታዊውን አገዛዝ የመጋፈጥ ታላቅ ታሪካዊ አደራ በመወጣት ረገድ ከሁሉ በላይ  ልዩ ነበር። ቀርቦ ላወቀው ታማኝ በየነ ግሰለብ ብቻ አይደለም፤ በሰነድ፣ በድምጽና  በተንቀሳቃኝ ምስል እጅጉን  የተደራጀ ተቋም ጭምር ነው። ባለፉት ሀያ ሁለት ዓመታት  የአሜሪካን ቆይታው የወያኔን አገዛዝ ብልግናዎች፣ ነውሮችና ጭካኔዎች ሲያጋልጥ  የኖረው  በሰነድ፣ በድምጽና በተንቀሳቃሽ ምስል ክምችት በዋጁ ዶሴዎች  እየታገዘ  የፋሽስት ወያኔ ቅጥ ያጣ ነውረኛነት፣ ነውጠኛነት፣ ጭካኔና ማፍያነት አጋልጧል።
ታመኝ በየነ ዘረኛነት  የሚባል ዘመን አመጣሽ በሽታ ሳያጠቃው፤ የሃይማኖት ድንበር ሳይገድበው፤ የተገፉት፣ በጭካኔ የተገደሉት፣ የተሰደዱት፣ የታረዙት፣ በግፍ የታሰሩት፣ ጧሪ ቀባሪ ያጡት፣ በረሀ ለበረሀ ሲንከራረቱ የወደቁት፣ አውሬ የበላቸው፣ የውስጥ እቃቸው የተሸጠው፣ ባጠቃላይ የምስኪን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በደል ተጋብቶበት፣ ተፈጥሮ በቸረችም ልዩ ችሎታው የተጋባበትን የወገኖቹን ግፍና  በደል በቋንቋ ጭምር ለማስረዳት ሳይቸገር ፤ የእድሜውን ግማሽ ዘመን  የሕዝብ ድምጽ ሆኖ ወገኑን አገልግሏል። አብረውት የነበሩ የሞያ ጓዶቹ   መቶ ሰማኒያ ዲግሪ ታጥፈው በደም ከቦካ እጅ ቀለብ ሲሰፈርላቸው፣ ታማኝ  ግን  እንደ ስሙ ታማኝ ሆኖ ንቅንቅ ሳይል ሲጀምር በቆመበት ቦታ ላይ ጸንቶ ላገሩ ሲጮህ ኖሯል።
በወንድሙ  ባሕሪ የሚደመመው ወንድሙ ተወልደ በየነ «ድጋሚ የምፈጠር ቢሆን ደግሜ የታማኝ ወንድም ሆኜ መፈጠር ነው የምፈልገው» ሲል  ወንድሙን  ይገልጸዋል!  ታላቁ አባታችን አባ ወልደ ተንሳይ  ደግሞ ታማኝን «ስሙ መጥቶ ያለቀለት!» ብለውታል። እንደዛሬው የተንቀሳቃሽ ምስል ዶክመንተሪ ሳይስፋፋ  ታማኝ በየነ በ1997 ዓ.ም. ያዘጋጀው «ታማኝ ትናንትና ዛሬ»  የተሰኘው ዶክተምተሪ ፊልም እኔን ጨምሮ የማይናቅ  ቁጥር ያላቸው የገጠሪቱ ኢትዮጵያ  ወጣቶች  የወያኔን መልክ እንድናውቅ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል።
ስሙ ወጥቶ ያለቀለት የግራዝማች በየነ ወንድ ይፍራው ልጅ ዛሬ ከ22 ዓመታት የግፍ ስደት በኋላ እጅጉን  ወደሚናፍቃት አገሩ ገብቷል። ውድ ታማኝ እንኳን  ለእናት አገርህ አበቃህ! በአገርህ ውስጥ የሚኖርህ ቆይታ የተሳካና የምትደሰትበት ይሆንልህ  ዘንድ ከልብ  እመኝልሀለሁ።
Filed in: Amharic