>

መንገዳችን በፍጥነት ይቃና (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)

በብዙ ዓይነት ወንጀሎች የሚታሙት የወያኔ አዛዦች ሥልጣናቸውን እንደያዙ ከሥልጣን ወረዱ ቢባል ግራ ይሆናል፤ ነገር ግን ሆነ! በሕጋዊ ምርመራ ሳይጣራና ከሳሾቹን በፍርድ ቤት ሳይሞግት የሰው ልጅ እንደከብት ከመንገድ በጉልበተኞች እየተያዘ መታሰር የቀረ መስሎን ነበር፤ አልቀረም አሉ! ጉልበተኞች በወንጀላቸው ክብደት ከሕግ ይከለላሉ ይባል ነበር፤ አሁንም ያው ይመስላል! ያነበብሁትን በትክክል ካስታወስሁት በጥንታውያን ግሪኮች ሰርቀው መያዝ እንጂ መስረቅ ወንጀል አልነበረም (የምታስታውሱ አርሙት)፤ የምንመሳሰለው በጥንታዊነት ብቻ መስሎኝ ነበር!

ከዚህ ቀደም ጸጋዬ ገብረ መድኅን (ይመስለኛል) ተረግመናል ብሎ፤ ነበር፤ እኔንም መሰለኝ! ኢትዮጵያውያን መልካቸውን፣ ነብሮች ቆዳቸውን እንዴት ይለውጣሉ ያለው መልካችንን ነበር፣ ወይስ ጠባያችንን ማለቱ ነበር!

ነገሬ ሁሉ የጥንቶቹን አባትና እናት ይህንን የተሸከምነውን ጉድና ነውር ጫኑብን ለማለት እንዳመስላችሁ፤ እነሱ ሊጭኑብን የፈለጉት ክብርንና ኩራትን ነበር፤ ነገር ግን አህያ ወላጆቻችንን እያገለገለች ዱላን የመቻል ትእግስትዋና በዘመናት ለከፈለችው መስዋዕትነት ክብርንና ኩራትን ስትወርስ አበሻ ‹‹አባባ እግርዎትን!›› (ከቃሊቲ የደረጀ ሀብተ ወልድ ትምህርት ቤት የተገኘ እውቀት!) እያለ መለቃቀሙን መረጠ!

የወደቀ ከማንሣት የጣሉትን ማንሣት የሚያኮራና የሚያስከብር ይመስለኛል፤ የጣሉትን ማንሣት ራስን የማረም እርምጃም ነው፤ ራስን ማረም ራስን ማቃናት ነው፡፡

ላለፉት ሦስት ወራት የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅር፣ በምሕረትና በይቅርታ፣ በመረዳዳትና በተስፋ ንግግሮችና በማይናቁ ድርጊቶች አንገቱን ቀና፣ ደረቱን ነፋ ማድረግ ጀምሮ ነበር፤ ለአዲስ ሥራና ለአዲስ እድገት በአዲስ መንፈስና ደበአዲስ ኃይል ታጥቆ እየተሰናዳ ነበር፤ ለማ መገርሳና ዓቢይ አህመድ የእግዚአብሔር መልእክተኞች መስለው የታዩበት ጊዜ ነበር፤ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ላባቸው እየረገፈ ለብዙው ሰው ከመሬት መነሣት እያቃታቸው እየመሰለ ነው፡፡

የአገሩ ችግር ውስብስብ መሆኑ እየታወቀ ብዙ ቡድኖች የበለጠ ውስብስብ እያደረጉት ነው፤ ምክንያቱ የተሰወረ አይደለም፤ የሥልጣን ሰይፍና የጠገራ ብር ቀልቀሎ ነው፤ ሁለቱንም እየተስገበገቡ በመሻማት እርስበርሳቸው ለመጠፋፋት የሚተራመሱት ከራሳቸው በላይ ነፋስ ነው!

ለማና ዓቢይ አዲሱ የፖለቲካ ፍልስፍነናቸው ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው ያውቃሉ፤ ሁላችንም እናውቃለን፤ ለማና ዓቢይ በስንት ወራት የሁለት ሺህ ዓመታቱን ትምህርት ሊያገባድዱ እንዳቀዱ የሚያውቁት እነሱና የላካቸው አምላክ ብቻ ነው፤ እንደጅምራቸው ከሆነ ግን ለማና ዓቢይም እንደክርስቶስ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም! እግዚአብሔር አቋራጩን መንገድ ይግለጽላቸው፡፡

ሕግና ሰይፍ የባሕርይ ዝምድና አላቸው፤ ዝምድናቸውም በጣም የጠነከረ ከመሆኑ የተነሣ አንዱ በሌለበት ሌላኛውም የለም፡፡

Filed in: Amharic