>
5:13 pm - Saturday April 19, 2690

ፖለቲካዊ ድብብቆሽ የተስተዋለበት ጉባኤ:-  (ቹቹ አለባቸው)

ፖለቲካዊ ድብብቆሽ የተስተዋለበት ጉባኤ:- 
ቹቹ አለባቸው
* ሌላዉ አስገራሚ ነገር; አቶ ጌታቸዉ አሰፋ  “የአማራ ህዝብ ማንኛዉንም ህዝብ; የመጨቆን ባህሪ የሌለዉ ህዝብ ነዉ” ሲል የተናገረዉ ንግግር ነዉ። ጎበዝ ህወሀት ገረጀፈች ይሆን?  በማኒፌስቶዋ ጀምራ ”  ጨቋኟ የአማራ ብሄር” ብላ ስታበቃ..
ሁላችንም እንደምናዉቀዉ; ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች የጋራ ግንባር እንጅ;  አንድ ወጥ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም። ስለሆነም; በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል; ያዉ; አንድና ወጥ የሆነ አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊኖር ይገባል ተብሎ አይጠበቅም። ምክንያቱም; ሁሉም ድርጅቶች; የኢህአዴግ አባል የሆኑት; የየራሳቸዉን  አንጻራዊ ድርጅታዊ ነጻነት እንደያዙ ስለሚሆን ነዉ። ስለሆነም; በአንዳንድ መለስተኛ ጉዳዮች ዙሪያ; በአባል ድርጅቶቹ መካከል ልዩነቶች ቢስተዋሉ; የሚጠበቅ ነገር ነዉ ማለት ነዉ።
—-
ይሁን እንጅ; ምንም እንኳን; በአንድ ግንባር ስር በተደረጁ የተለያዩ ድርጅቶች መካከል; መለስተኛ ልዩነቶች የሚጠበቁ ቢሆንም; ከቅርብ አመታት ጀምሮ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የሚታየዉ ልዩነት ግን; የጤና አይመስልም። የዚህ ችግር የቅርብ ማሳያ የሆነዉ; ሰሞኑን በሚካሄዱት የኢህአዴግ የአባል ድርጅቶች ጉባኤወች ዙሪያ የሚስተዋሉት ልዩነቶች ናቸዉ።
በዛሬዉ የብአዴን ጉበኤ; በተጋባዥነት ተገኝቸ ነገሮችን ተከታተልኩ። ከዝግጅት አንጻር; የጉባኤዉ አዘጋጅ ኮሚቴ የተዋጣለት ይመስላል። በተለይ በህጻናት የቀረበዉ መዝሙር በጣም ዉብ ነበር። በዚህ ጉባኤ “እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ;  ታጋይ የህዝብ ልጅ; በደሙ በላቡ ደማቅ ታሪክ ጻፈ” የሚለዉ የህላዊ መዝሙር ቀርቶላችሁዋል። ብአዴን በነካ እጁ; አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለዉን ነገርም በጣለዉ።
እንደ ጉባኤ ባለቤት ;  የአቶ ገዱና አቶ ደመቀ; የመክፈቻ  ንግግርም አይከፋም። በመክፈቻ ንግግር ;ከዚህ የተለየ ብዙም ነገር አይጠበቅም። እነሱ የሚወደሱትም ሆነ; የሚነቀፉት ; ነገ የሚቀርበዉን ሪፖርት አይተን ነዉ; የነሱ መለኪያ; ሪፖርቱ ምን ያክል የአማራን ህዝብ ችግር ዳስሷል? የሚለዉ ነዉ። በዚህ በኩል ስለሚኖረዉ ነገ  ልመለስበት።
—–
የነአቶ ገዱንና አቶ ደመቀን ንግግር ተከትሎ; ” እህት ድርጅቶች” የሚባሉት ድርጅቶች; ማለትም; የኦዴፓ; ህወሀትና ደኢህዴን; በተወካዮቻቸዉ አማካኝነት የድጋፍ መግለጫ አቅርበዋል። የየድርጅቶቹን  የድጋፍ መግለጫ ይዘት; በጥንቃቄ  ለመረመረዉ ሰዉ; ነገሩ እንዴት ነዉ? እዉን ኢህአዴግ የሚባል ግንባር; እዉነተኛ ግንባር ነዉ? ነዉ ወይስ ድርጅቶቹ; አንድ ሳይሆኑ; አንድ መስለዉ ለመታየት እየሞከሩ ነዉ? ነዉ ወይስ እየተሸዋወዱ ነዉ? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም።
—-
የዛሬዉን የብአዴን ” እህት ድርጅቶች”  የድጋፍ መግለጫ ይዘት በአጭሩ ላንሳ :-
1.የ ኦዴፓ:- ድርጅታዊ የድጋፍ መግለጫ; ሸጋ ነዉ ሊባል ይችላል።
2. የ ህወሀት:- ድርጅታዊ የድጋፍ መግለጫ:-
 በህወሀቱ ሰዉ ; አቶ ጌታቸዉ እረዳ; የቀረበዉ የድጋፍ መግለጫ; አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ አይነት ነዉ። አልፎ አልፎም; የቀደሙን የአለቃነት ባህሪዉን ለማንጸባረቅ ሞክሯል። ከዛሬዉ የህወሀት የድጋፍ መግለጫ ንግግር; በቲንሹ 3 አስገራሚ ነገሮችን ታዝቢያለሁ:-
#. የመጀመሪያዉ ነገር; ህወሀት የኦሮሞንና አማራን ህዝብ ግንኙነት  ” በሳትና ጭድ” የመሰለዉንና በዚህ ንግግሩ; በተለይም በአማራ ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠላዉን; አቶ ጌታቸዉ እረዳን ; በብአዴን ጉባኤ ተገኝቶ; የህወሀትን የድጋፍ መግለጫ እንዲያቀርብ መደረጉ; አላማዉ ምንድን ነዉ? የአማራን ህዝብና የብአዴን አባላትን አበሳጭቶ ያልተገባ ነገር ዉስጥ ለማስገባት ታስቦ ይሆን? ይመስላል። ደግነቱ ጨዋዉ የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤተኛና ታዳሚ ; የአቶ ጌታቸዉን ዉለታ ; በጨዋነትና በጭብጨባ ነዉ የመለሰለት። ከታላቅ ህዝብ ወኪልና ድረሸጅት የሚጠበቀዉ ይሄ ነዉ።
#. ሌላዉ አስገራሚ ነገር; አቶ ጌታቸዉ; የአማራ ህዝብ ማንኛዉንም ህዝብ; የመጨቆን ባህሪ የሌለዉ ህዝብ ነዉ ሲል የተናገረዉ ንግግር ነዉ። ጎበዝ ህወሀት ገረጀፈች ይሆን? ህወሀት በማኒፌስቶዋ ጀምራ እስከዛሬ ድረስ የምትመራበት ”  ጨቋኟ የአማራ ብሄር” የምትለዉ አባባል የት ገባች? ኧረ ጉድ ነዉ ጎበዝ; ነዉ ከኦህዴድ/ከኦዴፓ መኮረጁ ነዉ? በዚህ በኩል; ዛሬ ህወሀትና አቶ ጌታቸዉ ትዝብት ዉስጥ ገብተዋል። እየተዋወቅን! እነዲህ በአደባባይ ጭልጥ አርጎ እዉነትን አወላግዶ መናገር?
#. ሶስተኛዉ የአቶ ጌታቸዉ አስገራሚ ነገር; ደግሞ  አካባቢወቻችን ( ወልቃይትና ራያን እንደሆነ ነዉ የገባኝ ); የልማት ኮሪደር ነች እንጅ; የግጭት ማእከል መሆን የለባቸዉም ; በማለት የተናገረዉ ነገር ነዉ። ይህ አባባል ምን ማለት ነዉ? እነዚህን የዉዝግብ አካባቢዎች ; በጋራ እናልማቸዉ ለማለት ይሆን? ነዉ ወይስ ህወሀት ነገሩ ገብቷት; ሰላም እንዲወርድ ወስና ይሆን? ብቻ በዚህ በኩል የአቶ ጌታቸዉ ንግግር ግልጽ አይደለም።
3. የ ደኢህዴን መግለጫ:- የደኢህዴን ነገር አሰቸጋሪ ነዉ። የዛሬዋ ተናጋሪ በጥሩ ሁኔታ ነዉ ያቀረበችዉ። ሴትዮዋ; ድርጅቷን ወክላ; ለብአዴንና የአማራ ህዝብም ክብር ሰጥታለች። ነገር ግን በቀደምለት; በህወሀት ጉባኤ ተገኝታ; ለህወሀት የድርጅቷን የድጋፍ ያቀረበችዉ;ሌላኛዋ የደኢህዴን ሴት አመራር; ህወሀትና የተግራይ ህዝብ “የአጼዉን” ስርአት ታግለዉ በማስወገድ በኩል; የከፈሉት ዋጋ ምናምን; ስትል ሰማናት። የዛሬዋ ደግሞ ሌላ ተናገረች። እነዚህ የደቡብ ልኡኮች አይናበቡም እንዴ? ነዉ ደኢህዴን ; ቋሚ ጥቅም እንጅ; ቋሚ ወዳጅ የላትም? ነዉ በህወሀትና ብአዴን መካከል ሁና;  አጫዋች ለመሆን ፈልጋለች? ለሁሉም ደኢህዴን አልጨበጥ ብላለች።
—–
በአጠቃላይ; የህወሀትንና ብአዴንን ድርጅታዊ ጉባኤወችና; አንዱ ድርጅት ለሌላኛዉ የሚሰጠዉን የድርጅት የድጋፍ መግለጫ ስመለከት; በድርጅቶቹ መካከል; እንደሚባለዉ አንድነት ያለ አይመስልም። በርግጥ በኦዴፓ እና በብአዴን መካከል ; በአይን ጥቅሻ መግባባቱ እንዳለ መገንዘብ አይከብድም። ነገር ግን; በብአዴንና ደኢህዴን: እንዲሁም ; በብአዴንና በህወሀት መካከል; ድብብቆሽ እንጅ ; በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት አለ ለማለት ይከብዳል። ይህ ማለት ምን ማለት ነዉ? የዚህ ነገር ትርጉሙ; ኢህአዴግ አንድ አይደለም ማለት ነዉ። እንዲሁም ይህ አሰላለፍ; ምን አልባትም;  በቀጣዩ የኢህአዴግ ጉባኤም ላይ ተንጸባርቆ; ብአዴንና ኦዴፓ በአንድ ጎራ; ደኢህዴንና ህወሀት ደግሞ በሌላ ጎራ ሁነዉ ይጠዛጠዙ ይሆናል።
ነገን እንዴት እናሳልፋት?
የዛሬዉ የጉባኤ ዉሎ; መክፈቻና ዘፈና ዘፈን የበዛበት ነበር። ጥሩ ጥሩ ዘፋኞች; ዘፋኞችና ተወዛወዦች አፍርተናል። ነገሩን ነገ የምናየዉ ቢሆንም ; ምን አልባትም; ጥሩ ጥሩ  ዘፋኞችንና ተወዛዋዦችን ብቻ ሳይሆን;  ጥሩ ጥሩ ተናጋሪወችንም አፍርተን ይሆናል።
እንግዲህ ; ቁልፉ የጉባኤዉ አጀንዳ; የሚጀመረዉ ነገ ነዉ ። በነገዉ እለት ደግሞ በዋነኛነት; በመጀመሪያ ደረጃ; ጉባኤዉን የሚመሩ ቁጥራቸዉ ከ 5 ያልበለጡ አካላት(የፕሬዝድየም አባላት) በተሳታፊዉ ይመረጣሉ። በተለምዶ; ለዚህ ስራ የሚመረጡት;  የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ናቸዉ። ይሄ  አሰራር ግን; ተለምዷዊ እንጅ ግድ አይደለም። ስለሆነም; በነገዉ እለት; በሚካሄድ የፕሬዝድየም ምርጫ; ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የነዚህ አካላት ምርጫ; በጉባኤዉ አጠቃላይ ሂደትና ዉጤቱ ላይ ከባድ ተጽኖ አለዉ።
ለምሳሌ:- ብዙዉን ጊዜ; በፕሬዝድየም የተመረጠ ሰዉ; ለማእኮ የመመረጥ እድሉ ሲበዛ ከፍተኛ ነዉ። ሌላዉ ነገር; ይሄ አካል; ለተሳታፊዉ እድል በመስጠትና በመንፈግ; እንዲሁም ጥቆማበመቀበልና በመከልከል; ወዘተ…..ያለዉ ሚና ከፍተኛ ነዉ። ስለሆነም; ጉባኤተኛዉ; ለፕሬዝድየም አባል ተመራጮች ማንነትና አስፈላጊነት; ከፍተኛ ትርጉም ሰጥቶ መምረጥ አለበት።
 ለምሳሌ:- እኔ የመምረጥ መብት ቢኖረኝ ኖሮ; ዘንድሮ  ለማእኮ አልመርጠዉም ብየ የወሰንኩበትን ሰዉ; ለፕሬዝድየምነት አልጠቁመዉም;ሌሎቹም እንዳይጠቁሙት እመክራለሁ; ከጠቆሙትም እቃወማለሁ። ይሄን የማደርገዉ; የማልፈልገዉ ሰዉ በፕሬዝድየምነት ከተመረጠ; በሁዋላ ለማእኮም የመመረጥ እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ስለማዉቅ; ከወዲህ  ለመከላከል ነዉ። ለምሳሌ ነዉ ያቀረብኩት።
—-
 ከፕሬዝድየም ምርጫ ቀጥሎ የሚኖረዉ አጀንዳ; በዛሬዉ እለት; ከስአት በፊት የጉባኤ ተሳታፊወች; በየቡድኑ ሁነዉ; ገለብ ገለብ ባለ መልኩ; ሲወያዩበት እንደዋሉ የሚገመተዉ ; ድርጅቱ ባለፉት ሶስት አመታት ስላከናወናቸዉ ፖለቲካዊ; ድርጅታዊና መንግስታዊ ስራወችን አስመልክቶ;  በቀረበዉ ሪፖርት  ላይ ተመስርቶ ዉይይት ማካሄድ ነዉ። ይህ ከ100 በላይ ገጽ የሚሆን ሪፖርት;  እንዴት በግማሽ ቀን እንደተሸፈነ ባታ ትወቀዉ።
ያም ሆነ ይህ; ነገ ጠዋት መድረኩ ሲከፈት; በተለምዶ እንደሚደረገዉ; በቡድን መሪወች አማካኝነት;  በየቡድኑ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች; ለጠቅላላዉ ቤት ይቀርባሉ (ምን አልባትም በዛሬዉ እለት; ለሚመለከታቸዉ አካላት ደርሰዉ አድረዉ ይሆናል) ሁሉም ሰዉ ይሰማቸዋል። ከዚያ መድረክ መሪወቹ; ጥያቄወቹን በየ ፈርጁ አደራጅተዉ ለዉይይት ይዘረጓቸዋል።
—-
እንግዲህ ችግር የሚጀምረዉ እዚህ ነጥብ ላይ ነዉ። የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር; ሁሉም ጉዳዮች እንዲዳሰሱ ስለሚፈልግ; ለሁሉም ጉዳዮች; ቅደምተከተልና ተገቢዉን ጊዜ ይመድብላቸዋል። ተሳታፊዉ ደግሞ እንደሚፈልገዉ አጀንዳ አይነት; ቅድምያ; በቂ ጊዜና ትኩረት እንዲሰጥለት ይፈልጋል። በዚህ ምክንያት የተወሰነ ጊዜ ይባክናል።
በአጀንዳወቹ ቅደም ተከተልና; የጊዜ ምደባ ስምምነት ከተደረሰ በሁዋላ ዉይይት ይጀምራል። እዚህ ላይ የሚገጥመዉ ችግር; አንዳንድ ተናግሮ አይጠግቤ ; ተሳታፊወች መኖራቸዉ ነዉ። እነዚህ ሰወች ለ5 ሰዉ የሚሆነዉን ጊዜ ለብቻቸዉ ይበሉታል። በዚህም ምክንያት ጊዜ ይጠባል;  መናገር የሚፈልጉ የተለያዩ ሰወች ሀሳብም ሳይደመጥ ይቀራል።
መፍትሄ:-
1. ቁልፍ ነጥበችን ብቻ መርጦ; በነዚህ ነጥቦች ላይ  ብቻ አስተያየት መስጠት; ለአሰስ ገሰሱ ነጥብ ሁሉ ጊዜን አለማባከን። ለምሳሌ እኔ እድሉን ካገኘሁ ትኩረት የማደርገዉ:- ስለ ኢትዮ-ሱዳን ደንበር ሁኔታ: ስለ ወሰንና የማንነት ጥያቄወቻችን:  ለዉጡን የሚያስቀጥል አመራር ቁመናችን: ስለ ወቅቱ ሁኔታ: በህወሀትና ብአዴን ግንኙነት ዙሪያ;ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ; በመሳሰሉት ዙሪያ ይሆናል።
2. ንግግርን; አጭር; ግልጽ; ያልተንዛዛ; ሳቢና ተደማጭ ማድረግ። ሌሎች ያሉትን አለመድገም; ለዚህም ሲባል ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና ማዳመጥ;
3. ቁልፍ ነገሮቹ በርካታ ከሆኑ; ከሌላ ጓደኛ ጋር መከፋፈልና እድልን መሞከር።
4. እጅግ ወሳኝ ጥያቄ በማንም ሳይነሳ ከቀረ; በማስታወሻ ወደ መድረክ መላክ።
እስኪ በዚህ እንሞክረዉና; ዉጤቱን አይተን ደግሞ እንደገና እናየዋለን።
Filed in: Amharic