>
10:10 pm - Tuesday August 16, 2022

አዲስ አበባ ቤቴ (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ)

አዲስ አበባ ቤቴ
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
አዲስ አበባ ያለችው ኦሮሞዎች በሰፈሩበት ቦታ ነው ቢባልም፥ በአፍቃሬ ምኒልክ የሸዋ ኦሮሞች ጉዳይ ውስጥ አርሲዎችንና ወለጎችን ምን አገባቸው። አንድ ነገድ ነን ካሉ፥ መጀመሪያ አንድ ያደረጓቸውን አፄ ምኒልክን ማመስገን አለባቸው። አፄ ምኒልክ አንድ እስኪያረጓቸው ድረስ፥ በግጦሽ የሚገዳደሉ የጎሳ ጥርቃሞዎች ነበሩ። 
 
አምስት የኦሮሞ ድርጅት መሪዎች ስለ አዲስ አበባ ብዙዎችን ያስቈጣ መግለጫ ሰጥተዋል። መግለጫውን በጥሞና ቢያዳምጡት ለጊዜው ከድምፃቸው በቀር ሌላ የሚያስደነግጥ ቁም ነገር የለበትም። “ኦሮሞን ነፃ እናወጣለን። አዲስ  አበባ የኦሮሞ ከተማ ነች፤ ምክንያቱም፥ የተስፋፋችው በኦሮሞ ርስት ላይ ነው” ሲሉ ቆይተው፥ አሁን አንገታቸውን ደፍተው አዲስ አበባ ሲገቡ ለአታለሏቸው ተከታዮቻቸው ምን ተስፋ ይስጧቸው?  ደጋፊዎቻቸውን ያስደስት የመሰላቸውን አንዳች ድምፅ ማሰማት ግድ ሆኖባቸው ነበር።
ወደኋላ መለስ ብለን ስናየው፥ የነዚህ ኦሮሞን ነፃ እናወጣለን የሚሉ ድርጅቶች መሪዎች በስደት በነበሩበት አገር እዚያው አርጅተው እንዳይሞቱ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አዝኖላቸው አገራቸው እንዲገቡ ነፃ ሲያወጣቸው እጅ ነሥተው የመጡት ምን አይተው ነው? “የኢትዮጵያ ክፍሎች ከዛፍ ላይ እንደሚረግፍ ቅጠል አይደሉም” ማለቱን ተቀብለው አይደለም እንዴ?  መግለጫቸው በመሠረቱ ውስጠ-ባዶ ቢሆንም፥ አንድ ቀን ጊዜ ሲያጋጥም እንዲነሡና ጥያቄውን እንዲያነሡ ደጋፊዎቻቸውን ማዘጋጀታቸው ሊሆንም ስለሚችል፥ አገር ወዳዱ ሕዝብ ዝም ማለት አይገባውም። አንዳንድ በሽታ ያገረሻልና ስሕተታቸውን ማሰማትና ተከታይ ያላቸው እነሱ ብቻ እንዳይደሉ ማሳየት ተገቢ ነው።  የተቈጡባቸው ኦሮሞዎችም መሆናቸውን ይዩት።
ለአሁኑ ግን የመረዋ ድምፅ ናቸው። ለመረዋ ድምፅ መዘጋጀት እንጂ መበሳጨት አያስፈልግም። አዲስ አበባ የሁላችንም ናት። እየኖርንባት የሁላችንም ከሆነችነቷ የሚለያት ኃይል የለም። መግለጫው የልጆች ጫወታ ይመስላል። ከድኻ ቤተ ሰብ የሚመጡ ልጆች ከመንገድ ዳር ቁጭ ብለው፥ መኪና ሲያልፍ እየጠበቁ ጥሩ መኪና ስትመጣ፥ “የኔ መኪና መጣች” ለማለት ይሽቀዳደማሉ። የነዚህ የኦሮሞ ድርጅቶች ድምፅ ከመረዋ ድምፅ የሚበልጠው፥ የአዲስ አበባ ዕጣ በሕገ መንግሥት ሲለወጥ ብቻ ነው። እስከዚያ፥ ከዚያም በኋላ፥ ከተማዋ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ነች፤ (መኪናዎቹም የባለቤቶቻቸው ናቸው።)
አዲስ አበባ ያደገችው አውላላ ባዶ ቦታ ላይ ነው። ባዶ ቦታ ማለት ማንም ሰው ያልሰፈነበት ውድማ ማለት ነው። ለውድማነቱ ማስረጃ፥ በአፄ ምኒልክ ዘመን አቧሬ አንበሳ ይታደን እንደነበረ ያድኑ ከነበሩ ሰዎች የተነገረን ታሪክ ነው።
በጠቅላላ የሀገሪቱ ታሪክ እንደሚያመለክተው፥ ከተሞች የተመሠረቱት የሀገሩ መሪና ሹማምንቱ በሚኖሩበት ቦታ ነው። ንጉሡ በሰፈረበት አጃቢዎቹ ይሰፍራሉ። ጠቅላይ ግዛት የሚያስተዳድሩ ሹማምንት በሰፈሩበት ወታደሮቻቸውም ይሰፍራሉ። የኢትዮጵያ ከተሞች ያደጉት አገር አስተዳዳሪዎች ከሰፈሩበት ተነሥተው ነው።
ኦሮሞዎች ከብት የሚያረቡ ዘላኖች ስለነበሩ፥ ግጦሽ ወደሚገኝበት ቦታ ከብታቸውን ተከትለው መጓዝ እንጂ አንድ ቦታ አይከትሙም ነበር። እያደር መስፈር ሲጀምሩ፥ አንድ ጎሳ ከብቶቹን ለግጦሽ ያሰፈረበት ቦታ በስሙ ይጠራል። ከነዚህ ሰፈሮች ውስጥ  ወደ ከተማነት ያደገ አንዳቸውም ቦታ የለም። ከብት ማርባትና መከተም አብረው ስለማይሄዱ ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ከተማ የለም። “ኦሮሞዎች በሰፈሩበት አካባቢ ከተማ አለ” ማለትና “የኦሮሞች ከተማ” ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አንድ ከተማ ኦሮሞዎች በሰፈሩበት አካባቢ ቢመሠረት ከተማውን የመሥራቾቹና በውስጡ የሚኖሩበት እንጂ የኦሮሞ ከተማ አያደርገውም።
ከተማ የነጋዴዎች፥ የሸቃዮዎች አገር ነው። ከተማ ገበያ ነው። ገበያ በመሠረቱ የሻጮችና የገዢዎች መገናኛ  ሆኖ፥ እቃ አቅራቢው፥ በአንድ በኩል፥ ሰብልና ከብት አምራቹ ባላገሩ፥ በሌላ በኩል ሣሪያና ልብስ አምራቹ (ቀጥቃጩ፥ ሸማኔው፥ ልብስ ሰፊው) ከተሜው ናቸው።  ሰብልና ከብት አምራቹ ባላገር ያመጣውን ምርት ሸጦ አገሩ ይመለሳል። ተመላሹ ከብት አርቢውና አራሹ ባላገር ነው። እከተማ የሚቀረው ከተሜው ነው፤ ባለ እጁ፥ አናጢው፥ ቀጥቃጩ፥ ወታደሩ ማለት ነው። ብዙ ኦሮሞዎች ወታደርም ስለሚሆኑ ከተሜዎች አሉባቸው። ግን እነዚህ ከተማውን የኦሮሞ ንብረት አያደርጉትም። የኦሮሞ ድርጅቶች “ከተሞቹ የኛ ናቸው” የሚሉት ሀብት ስላዩባቸው፥ በሰው ዳቦ እንደሚያለቅሰው ሕፃን ልጅ መሆናቸው ነው እንጂ፥ የተማሩ ከሆኑ እዚህ የምጽፈው ሳይታያቸው ቀርቶ አይደለም።
አዲስ አበባ ያለችው ኦሮሞዎች በሰፈሩበት ቦታ ነው ቢባልም፥ በአፍቃሬ ምኒልክ የሸዋ ኦሮሞች ጉዳይ ውስጥ አርሲዎችንና ወለጎችን ምን አገባቸው። አንድ ነገድ ነን ካሉ፥ መጀመሪያ አንድ ያደረጓቸውን አፄ ምኒልክን ማመስገን አለባቸው። አፄ ምኒልክ አንድ እስኪያረጓቸው ድረስ፥ በግጦሽ የሚገዳደሉ የጎሳ ጥርቃሞዎች ነበሩ።
ሆኖም አንድ ተገቢ ጥያቄ አላቸው። አዲስ አበባ እንደሚጠበቀው እያደገ ሄዷል። ሲያድግ መስፋፊያው ወደ ዳርና ወደ ሰማይ ነው። ወደ ዳር ሲያድግ የግድ የአርሶ አደሩን መሬት ይወስዳል። አርሶ አደሩ ተገቢውን ካሳ ይጠይቃል እንጂ፥ “ከተማው በኔ መሬት ላይ አይስፋፋ” ሊል አይችልም። ኦሮሞው መሬቱን የአማራ መኳንንት ወሰዱበት ሲባ ኖሮ፥ አሁን አዲስ አበባ ትስፋፋ ሲባል ባለ መሬት ሆኖ ተገኘ። ግዴለም፤ ገዢው ሕግ ከሆነ፥ ከተማ በሚስፋፋ ቦታ ርስት ያለው ገበሬ፥ ኦሮሞም ሆነ አማራ፥ ዕድለኛ ነው። ርስቱ የከተማ ቦታ ሆነለት። ግማሹን ሸጦ በግማሹ ላይ ለከተማ የሚፈለግ ብዙ ነገር ሊያቋቁምበት ይችላል። ካወቀበት ከመናጢ ዐፈር ገፊነት ወጥቶ  የደለበ ጌታ ይሆናል።
የከተማ ወደሰማይ ማደግ ማለት ፎቅ ቤት መሥራት ማለት ነው። ከተማ ወደ ሰማይ ሲያድግ ለአንድ ቤት የታሰበ ቦታ ሃያ ሠላሳ ቤቶች ያስሠራል።
አዲስ አበባ የሁላችንም ቤት ናት። እድሜ ለዶክተር ዐቢይ አሕመድ፥ አስከፊው የወያኔ አገዛዝ አልፎ፥ መብታችንን  የምናስከብርበት ዘመን መጥቷል። አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ እንጂ የጥቂት ሕልመኞች ሀብት እንዳትሆን መብታችንን የምናስከብርበት፥ የሌላ መብት መዳፈሪያ የማናደርገው ኀይል አግኝተናል፤ እንጠቀምበታለን።
ዶክተር ዐቢይ ኢትዮጵያን በዲሞክራሲ  የምትደዳር ገናና አገር ሊያደርጋት ያሰበው እንዲፈጸምለት አማሮች የሚጸልዩለትን ያህል ኦሮሞችም እንዲጸልዩለት እንጠይቃለን።
Filed in: Amharic