>

የአብይና የለማ ጋሻ ከኦህዴድ ይልቅ ብአዴን ነው !!! (ፋሲል የኔአለም)

የአብይና የለማ ጋሻ ከኦህዴድ ይልቅ ብአዴን ነው !!!
ፋሲል የኔአለም
ብአዴን ተጠናክሮ ይወጣ ዘንድ ጠንካራ መሪዎችን መምረጥ ይጠበቅበታል። ከሁሉም የኢህዴግ ድርጅቶች፣ ለውጡን የማስቀጠል ከፍተኛ ሃላፊነት የወደቀው ብአዴን ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት የአብይ ወይም የለማ አስተማማኝ ጋሻ ብአዴን ነው ብል አልዋሽም። ብአዴን ዘንበል ቢል ለውጡ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ብአዴንን አስተማማኝ ጋሻ ያደረገው ደግሞ እስከ ታች የዘረጋው መዋቅሩ ነው። ብአዴን ውሳኔዎችን በየትኛውም መንገድ ወደ ታች ወርዶ ማስፈጸም ይችላል፤  ኦህዴድና ደኢህዴን  ግን በጣም የሚተማመኑበት እስከታች የወረደ መዋቅር የላቸውም። እንዲያውም በአንዳንድ የኦሮምያ ቀበሌዎች  ውስጥ መዋቅሩ የኦህዴድ ነው ሲባል የኦነግ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ አለ። ለዚህም ነው የአብይና የለማ ጋሻ ከኦህዴድ ይለቅ ብአዴን ነው የምለው። ህወሃት እንደ ብአዴን ታች ድረስ የወረደ ጠንካራ መዋቅር ቢኖረውም፣  መዋቅሩን የአብይን  መንግስት ለማፍረስ እየተጠቀመበት በመሆኑ እዚህ ውስጥ አይገባም ።
ብአዴን ህዝባዊ ድርጅት መሆን ጀምሯል።  የህዝብ ጥያቄ ሰምቶ ለመመለስ ተፍ ተፍ እያለ ነው።  ብአዴንን ከህወሃት መንጋጋ በማላቀቅ ድርጅት ሆኖ እንዲወጣ ያስቻሉት ደግሞ የተወሰኑ አመራሮች ናቸው። አመራሮቹ የህዝብን ፍላጎት አዳምጠው ቆራጥ እርምጃ ባይወስዱ ኖሮ ዛሬ የምናየውን ለውጥ ላናይ እንችል ነበር። ይህን ስል ብአዴን ሙሉ በሙሉ የህዝብ ድርጅት ሆኗል እያልኩ አይደለም፤ አሁንም ብዙ ጉድለቶች አሉበት ግን በሂደት አስተማማኝ ሃይል ሆኖ ለመውጣት መንገዱን ጀምሯል። ለብአዴን መለወጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካደረጉት ከእነ አቶ ደመቀ እና አቶ ገዱ በተጨማሪ፣ ጎልማሶቹ ፖለቲከኞችን አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ አቶ ሻምበል ከበደን ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ከእነ በረከት ስምዖን ጋር ተፋልመው ብአዴንን ከህወሃት እቅፍ ነጻ አውጥተውታል። ብአዴንን ህዝብ እያመነው እንዲመጣ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል። እነዚህን ታጋዮች ፊት ለፊት አምጥቶ ለውጡን እንዲመሩ ማድረግ ከተቻለ፣ ብአዴን የአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠብቅበትንም ሃላፊነት በአስተማማኝ መልኩ መወጣት ይችላል። አቶ ደመቀ መኮንን የብአዴን መሪቱን  እንደሚያስረክብ እገምታለሁ፤ በመጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ደግሞ እነዚህን ፖለቲከኞች ወደ ፊት በማምጣት ለውጡ አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ። ልብ በሉ ስለእነዚህ ሰዎች የሁዋላ ታሪክ የማውቀው የለም። ነገር ግን ለውጡ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በቅርብ እንደተከታተልኳቸው ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያላቸው ቆራጥነት ከልቤ እንድደግፋቸው አድርጎኛል። መሪዎችን መምረጥ የእያንዳንዱ ጉባኤተኛ ሃላፊነት ቢሆንም፣ ለውጡ ሳይቀለበስ  በስርዓት እንዲቀጥል የሚፈልግ ሃይል ሁሉ እነዚህ ሰዎች ወደፊት እንዲመጡለት ይመኛል።  የእኔም ምኞት በዚሁ መነጽር ይታይልኝ።
Filed in: Amharic