>

መንግሥት ሕግን ለማስከበር ለምን ዳተኛ ሆነ? (ውብሸት ሙላት)

መንግሥት ሕግን ለማስከበር ለምን ዳተኛ ሆነ?
ውብሸት ሙላት
ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ንግግሮች ግራ ያጋቡኝ ሦስት ነጥቦች፦
1. ስለ ትጥቅ ማስፈታት አልተወያየንም ካሉ አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ኤርትራ ሄደው ከኦነግ (በዳውድ ኢብሳ ከሚመራው) የተስማሙት ምንድን ነው? ከእነ ትጥቃቸው በኦነግ አመራር ሥር ሆነው በአገር ዉስጥ መቀጠል እንደማይችሉ አይደለም አቶ ዳውድ ይቅርና ማንም ሰው የሚያውቀው ነው። ስለዚህ አቶ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከኦነግ አመራር ጋር ያደረጉትን ስምምነት ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ግን…. ምንድነው ስምምነቱ ታዲያ?
2. አቶ ዳውድ ኢብሳ የተናገሩት ሌላው ነጥብ የታጠቀው አካል መሳሪያ ሳይፈታ ኦነግም አይፈታም የሚል ይዘት አለው። ይሄ መቼም መንግሥት ትጥቅ መፍታት አለበት ማለት ሊሆን አይችልም። መንግሥት ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል ማንም ጤነኛ ሰው የሚያስበው አይደለም። ስለሆነም ይህ የታጠቀ ኃይል ማን ነው?
አንድ ግምት ብቻ ላስቀምጥ። በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው የነበሩ ሦስት ድርጅቶች ነበሩ። ኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት 7። ኦብነግና ግንቦት 7ም ወደ አገር ቤት ገብተዋል። እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ምን ያህል ወታደር እንደነበራቸው ካላቸው ደግሞ ትጥቅ ስለመፍታት አለመፍታት ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም።
ምናልባት የአቶ ዳውድ ጥቆማ ግንቦት 7 ይሆን? በእርግጥ ግንቦት 7 ወታደር ካለው እና ትጥቅ ካልፈታ እሱንም ቢሆን ማስፈታቱ የመንግሥት ኃላፊነት እንጂ ያ ካልፈታ እኛም አንፈታም አይባልም።
ግንቦት 7ም ይሁን ሌላ አካል ታጣቂ ካለው ማስፈታት የመንግሥት ግዴታ ሆኖ ኦነግ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ስለሌለበት እንቶኔ ካልፈታ አልፈታም ማለት ተገቢ አይደለም።
ግን …ማነው ባለትጥቁ?
3. አቶ አዲሱ አረጋ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የካማሼ ዞን አመራሮች ግድያ ላይ የተፈጸመው በኦነግ አማካይነት እንደሆነ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በኦነግ ላይ እርምጃ ሲወሰድ አልተስተዋለም። ይባስ ብሎ አቶ ዳውድ ኢብሳ አዲስ አበባ ላይ ሁነው ኦነግ ትጥቅ አይፈታም ብለዉ ቢናገሩም መንግሥት ምንም ዓይነት መግለጫ ወይም እርምጃ አለወሰደም።
ያልገቡኝ ጉዳዮች ናቸው።
Filed in: Amharic