>
7:09 pm - Monday May 16, 2022

ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?

ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?

በአለማየሁ አንበሴ – አዲስ አድማስ

በኢትዮጵያዊነት ላይ ውይይቶች ተደርገው፣ የህግ መቋጫ ማግኘት አለበት ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያውያን አብረን ለመኖር የተፈረደብን ነን ሁላችንም ወደ ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነታችን መመለስ አለብን የዜግነት ፖለቲካን እንደ ሩቅ ጊዜ ግብ ነው የማየው 

አቶ ዩሱፍ ያሲን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በቀይ ባህር ዳርቻ ቲዖ በምትባል መንደር ነው፡፡ ትምህርታቸውንም በአስመራ ነው የተከታተሉት፡፡ ራሳቸውን እንደ ኤርትራዊ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለው እንደሚያስቡ ይናገራሉ፡፡ በውጭ አገር ለ26 ዓመታት የኖሩት አቶ ዩሱፍ፤ በቀድሞ “ጦቢያ”መፅሔት ላይ ሐሰን ኡመር አብደላ በሚል የብዕር ስም በኢትዮጵያዊነት ጉዳዮች ላይ ሲያቀርቧቸው በነበሩት ጥልቅ ትንታኔዎችና ፅሑፎች ይታወቃሉ፡፡ሀገራቸውን በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አቶ ዩሱፍ፤ አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ “ኢትዮጵያዊነት፤ አሰባሳቢማንነት በአንድ ሀገር ልጅነት” በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በዚህ መፅሐፋቸውም የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ሰፊ ትንተና በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ አቅርበዋል፡፡ በመጽሐፉ ላይፖለቲከኞችና ምሁራን ግምገማና ውይይት አድርገውበታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በመጽሐፋቸው መነሻነት ከአቶ ዩሱፍ ያሲን ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡

በመፅሐፍዎ ከብሔርተኝነትና ኢትዮጵያዊነት ጋር በተያያዘ በርካታ አከራካሪ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ለእርስዎ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?

ኢትዮጵያዊነት የቅርፅም የይዘትም ገላጭ ባህርያት ይኖሩታል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ስሜታዊ ይዘት አለው፣ ባህላዊ ይዘት አለው፡፡ ዋናው ትልቁ ነገር፤ አቃፊና ደጋፊ የሆነ ማንነትን ነው፣ ኢትዮጵያዊነት የምንለው። ይህ እንግዲህ ባህላዊ ይዘቱ ነው፡፡ ከስሜታዊ ይዘቱ አንፃር ስንመለከተው ደግሞ “በቃ ኢትዮጵያዊነት” ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዝምታ የሚገለፅ ነው፡፡ ከርዕዮተ ዓለም አንፃር ስንመለከተው፣ ራሱን ኢትዮጵያዊ ብሎ የሚጠራው ሰው፤ ለሀገሩ የሚኖረው ሃሳብ፣ ራዕይ፣ ህልም ይሆናል፡፡ ይሄ ከስሜት በላይ ነው፣ ከባህል በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በስሜታዊነት፣ በርዕዮተ ዓለምና በባህላዊ መልኩ የሚገለፅ፣ ጥልቅ የሆነ አሰባሳቢ ማንነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ለኔ፡፡

የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎችስ ምንድን ናቸው ይላሉ?

ለአንዱ ክትፎ፣ ለአንዱ እንጀራ፣ ለአንዱ ገንፎ፣ ለአንዱ ቡሉኮ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ናቸው መገለጫዎቹ። በዩኔስኮ የተመዘገቡ የማይዳሰሱ የማንነቶች መገለጫዎች አሉ፡፡ ጨምበላላ፣ ደመራ፣ አሸንዳ፣ የገዳ ስርዓት– እነዚህ ሁሉ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከመገለጫነታቸው አልፈው ውስጠ-ገጻችን ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጨምበላላን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል አያውቀውም፣ አይረዳውም፤ ግን በዓለም እኛን አሳውቆናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ውስጠ ገፆች ተጠራቅመው፣ ተሰባስበው ነው ኢትዮጵያዊ የሚያስብሉን፣ ኢትዮጵያዊነታችንን የሚያሳውቁት፡፡ ኢትዮጵያዊነት መጠኑ እየጨመረ እንደሚፈስ ጅረት ነው፡፡

በመፅሐፍዎ ስለ ሀበሻነትና ኢትዮጵያዊነት አንስተዋል፡፡ ሀበሻ ማን ነው? ሀበሻና ኢትዮጵያዊነትስ ምንና ምን ናቸው? 

“ጦቢያ” መጽሄት ላይ ሃሰን ኡመር አብደላ በሚል ስም በምፅፋቸው ፅሁፎች፤ “ሀበሻ ማን ነው? ሀበሻ ያልሆነውስ ማነው” የሚል መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። እንግዲህ “ሀበሻ”፤ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው የራሱ ትርጉም አለው፡፡ ወደ አስር የሚሆኑ ትርጉሞች ተሰጥቶት አይቸዋለሁ፡፡ ሀበሻ ጥቁር ማለት ነው፤ ኢትዮጵያዊ በሙሉ ሀበሻ ነው፣ የሰሜን ኢትዮጵያ (አማራና ትግሬ) ብቻ ነው ሀበሻ — የሚል ትርጉምም ይሰጣል፡፡ ከየመን የፈለሰ ነው ሀበሻ የሚልም አለ፡፡ የተለያዩ አተያዮችና ትርጉሞች ናቸው፤ ሀበሻ ማን ነው በሚለው ላይ የሚቀርቡት፡፡ ነገር ግን ዋናው ቁምነገር በተለይ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ያሉ ህዝቦች ራሳቸውን ሀበሻ ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ አማራዎች፣ ኤርትራዊያን ራሳቸውን ሀበሻ ብለው  ይጠራሉ፡፡ ለአረቦቹ ደግሞ ሀበሻ ማለት ኢትዮጵያ ማለት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአረቦች ሀበሻ ነው፡፡ በታሪክ መፅሐፍቶቻቸውም ሀበሻ ሲሉ ኢትዮጵያዊ ማለታቸው ነው፡፡ ኤርትራዊያን የነፃነት ትግል በሚያደርጉበት ጊዜ ሀበሻ የሚለውን ስም አይፈልጉም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሀበሻ እንዴት ሀበሻን ይወጋል እንዳይባሉ ነው፡፡ በኋላ ግን ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ፣ በኩራት ራሳቸውን ሀበሻ ብለው መጥራት ጀምረዋል፡፡
ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ደግሞ እኛ ሀበሻ አይደለንም ይላሉ፡፡ ይሄ እንግዲህ ከዘመኑ ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ግን ሀበሻ የሚለው በአረቡ አለም፣ መላ ኢትዮጵያን የሚወክል አጠራር ነው፡፡ ለምሳሌ ሶማሌዎች ሀበሻ ነን አይሉም፡፡ ከጊዜው ፖለቲካ ጋር ተያይዞም፣ አንዳንድ ኦሮሞዎችም ሀበሻ አይደለንም ይላሉ፡፡ ስለዚህ ሀበሻ ብዙ ትርጉሞች ያሉት የፍረጃ ስም ነው፡፡ እኔ ነኝ ሀበሻ የሚለው፣ ሀበሻነቱን የተቀበለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሀበሻ አይደለሁም የሚለውም መብቱ ነው፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት “ብሔር ብሔረሰብ” ከመጠን በላይ ከመቀንቅኑ የተነሳ የ”ኢትዮጵያዊነት” ስሜት ተዳክሟል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ?

ከአውራው ህግ፣ ህገ መንግስት ጀምሮ እስከ ሌሎች ህጎች ድረስ፣ ብሔር ብሔረሰብ የሚለው ሰፍቶ ነው የምናገኘው፡፡ ችግሩ ብሔረሰቦች ማንነታቸው ተከብሮላቸው፣ ታውቆላቸው በሚኖሩበት አካባቢ ላይ በቋንቋቸው የሚተዳደሩበት ስርአት መስፈኑ ላይ አይደለም፡፡ ይሄ ዲሞክራሲያዊ የሆነ አሰራር ነው፡፡ የትም የሰለጠነ ሀገር ይህ አይነቱ አሰራር አለ፡፡ ለምሳሌ ጀርመን ማንነትን የምታስከብር ሀገር ነች፡፡ ፌደራላዊ ሀገር ነች፤ ነገር ግን በፌደራል ደረጃ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ነው ያላት፡፡ እኔ የምኖርባት ኖርዌይ፤ የፌደራል ስርአትን የምትከተል ሃገር ባትሆንም፣ እስከ ታችኛው የህብረተሰቡ ክፍል ድረስ ማንነቶች የሚከበሩባት፣ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩባት ሃገር ነች፡፡ ይሄ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 27 ዓመታት ብሔር ብሔረሰቦች ከሚለው እሳቤ ጋር ተያይዞ የታየው ነገር ግን የተሳሳተ አቅጣጫን የያዘ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አንድ ብሔረሰብን ለማስተዳደር የተመደበ አካል፣ ስርአቱን ዲሞክራሲያዊ ከማድረግ ይልቅ ስልጣኑን፣ ለቅራኔና ፉክክር ምንጭነት ሲጠቀምበት ነው የታየው፡፡ ብዙ ነገሮችን ያበላሹት፣ ያወሳሰቡት እነዚህ ናቸው፡፡  በዚህ ምክንያት ነው “ችግሩ ስርአቱ ነው ወይስ ስርአቱ ጥሩ ሆኖ ዲሞክራሲያዊ ያለመሆኑ ነው?” እያልን በየጊዜው የምንከራከረው፡፡ ችግር እየተፈጠረ ያለው፣ ብሔር ብሔረሰብ የሚለው ወይም አንድ ሰው በማንነቱ “እኔ የዚህ ወገን ነኝ” ብሎ በመኩራቱ ሳይሆን  የስልጣን፣ የሀብት ድርሻ ይገባኛል ጉዳይ ነው፡፡ የስልጣን አደላዳይ አካል ነው የችግሮቹ ምንጭ ሆኖ የሚታየው፡፡ አሁን ያለው የፌደራል ስርአት ዲሞክራሲያዊ ቢሆን ኖሮስ ምን ሊፈጠር ይችል ይሆናል? የሚለውም መተንተን ያለበት ነው፡፡ ለወደፊት ለሚደረገው የሀገር ግንባታም ቢሆን፣ ነገሩን ከዚህ አንፃር ማየቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ጠለቅ ያሉ ውይይቶች ያስፈልጋሉ፡፡

አሁን ጎሰኝነቱ (ብሔርተኝነቱ) የደረሰበት ደረጃ ለኢትዮጵያ ህልውና ምን ያህል አስጊ ነው? መፍትሄውስ ምንድን ነው?  

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ማም ሰው ቢጠየቅ፤ ስጋቱን በአንድ በኩል፣ ተስፋውን በሌላ በኩል አስቀምጦ ነው የሚገልፀው፡፡ ስጋቱ ከምን መጣ ካልን፤ በኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነት ላይ የተጋረጠ፣ በግልፅ የሚታይ ፈታኝ ፅንፈኝነት መኖሩ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ለዚህ ስጋት መፍትሄ ለማግኘት መትጋት ያስፈልጋል። አሰባሳቢ ማንነት ማን ነው? የቱ ነው? እንዴት ወደ መድረኩ እናምጣው? በሚለው ላይ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ውይይት እያደረግንበት አይደለም። አሁን እየተወያየን ያለነው በቅርፆች፣ በምልክቶች ላይ ነው፡፡ ይሄም የሚደረገው በስሜታዊነት ነው፡፡ አንዱ አንዱን በማብሸቅ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከዚህ መበሻሸቅ ወጥተን ቁም ነገር ወዳላቸው የውይይት አጀንዳዎች መግባት አለብን፡፡ የወደፊት ተስፋችን የሚታየውም፣ ከነዚያ ውይይቶች ውስጥ ይሆናል፡፡ በጋራ ለመኖር በሚያስችሉን ጉዳዮች ላይ መወያየት አለብን፡፡ የተወያየነውንና የተስማማንባቸውን ጉዳዮች አሰባስበንም፣ “የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” እንደሚባለው፣ በህግ ማሰር ያስፈልጋል፡፡ አሊያ ግን ስጋቱ እያየለ ይሄዳል፡፡ አሁን እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች በአብዛኛው ስሜታዊነት የሚንጸባርቅባቸው ሲሆኑ ጊዜያችንን እያጠፋን ያለውም  ዋናው ጉዳይ ላይ ሳይሆን ቅርፊቶቹ ላይ ነው፡፡

እንደ ህዝብ ከተስማማንባቸው ጉዳዮች ይልቅ ያልተስማማንባቸው ጉዳዮች ይበዛሉ ብለው ያስባሉ?

የተስማማንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በአንድ የፖለቲካ ስርአት፣ በአንድ የተወሰነ ድንበር ባላት ሃገር ውስጥ እንደምንኖር ተስማምተናል፡፡ ስምምነት የሌለው ይሄን አብሮነታችንን በምን መልክ ነው የምናስኬደው በሚለው ላይ ነው፡፡ ከመንግስት አቀራረፅ፣ አደረጃጀት ጀምሮ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አለመስማማታችንን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ባለፉ ታሪኮች ትርክት ላይም አልተስማማንም፡፡ ባልተስማማንባቸው ጉዳዮች ላይ ከጥልቅ ውይይት የሚመነጭ ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሃገር አለችን ካልን፣ እንዴት በዚህች ሃገር እንኑር በሚለው ላይ ነው መስማማት የሚያስፈልገን፡፡ በጋራ መግባባት ስምምነት ላይ ካልተደረሰም፣ ህዝበ ውሳኔዎች መደረግ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በፌደራሊዝም፣ ሰንደቅ ዓላማና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ህዝበ ውሳኔ ሊደረግ ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ በኢህአዴግ ህገ መንግስት ላይ ህዝበ ውሳኔ አልተደረገም፡፡ እንዳጋጣሚ በደርግ ህገ መንግስት ላይ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎ ነበር፡፡

ህዝበ ውሳኔ አልተደረገም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

የህግ ሰነዱ ከተዘጋጀ በኋላ ይሄ ህግ ይገዛኛል አይገዛኝም በሚለው ላይ ህዝበ ውሳኔ አልተደረገም ማለቴ ነው፡፡ ሌሎች ሃገራት እኮ በትንሽ ነገር ሳይቀር ህዝበ ውሳኔ ያደርጋሉ፡፡ “የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገራችን ይግቡ አይግቡ” እየተባለ፣ ህዝበ ውሳኔ ሲደረግ ተመልክተናል፡፡ እኛም ሀገር የህዝበ ውሳኔ ሂደት መጀመር አለበት፡፡ ትልቁ ችግር መፍቻ መንገድ ነው፡፡ የሚያናቁሩ፣ የሚያለያዩ ጉዳዮችን በኃይል ከመጨፍለቅ ለህዝበ ውሳኔ ማቅረቡ የተሻለ ነው፡፡

በመፅሐፍዎ “ኢትዮጵያውያን አብረን እንድንኖር የተፈረደብን ነን” ብለዋል፡፡ ይሄ አገላለጽ ግራ የሚያጋባ  ይመስላል፡፡ ምን ለማለት ፈልገው ነው?

አብረን እንድንኖር የተፈረደብን ነን በሚባልበት ጊዜ፣ አብረን በአንድ መንግሥት ስር አንኖርም ካልን፣ ያለን አማራጭ በጉርብትና መኖር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ መሬቱን ነቅለን ሌላ ቦታ መሄድ አንችልም፡፡ በጉርብትና ለመኖርም አብሮነት ያስፈልጋል፡፡ በአንድነት መኖር ያልቻለ ኃይል፣ በጉርብትና መኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም በኃይል ነው የሚለያየው፡፡ ነፃ ሲወጣ በጉርብትናም መኖር አይችልም፡፡ በጉርብትና መኖር አለመቻል ማለት ደግሞ፣ አካባቢው የማያባራ ጦርነት ውስጥ ይገባል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመጠፋፋት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡ በዚህም የተነሳ  ያለን ብቸኛ አማራጭ አብሮ መኖር ነው፡፡ የኛ ሀገር እውነታ ይሄ ነው፤ መለያየት የምንችል አይደለንም፡፡ ቀመሩ ለዚያ የተመቸ አይደለም፡፡ አብሮ የሚያኖረንን ቀመር ነው የበለጠ አውጥተን መጠቀም ያለብን፡፡ ስለዚህ ወደድንም ጠላንም፣ ኢትዮጵያውያን አብሮ ለመኖር የተፈረደብን ነን፡፡
በህገ መንግስቱ  አንቀፅ 39 ላይ የተቀመጠውን የመገንጠል መብት እንዴት ይመለከቱታል?
ብዙ የሚያከራክር አንቀፅ ነው፡፡ በእኔ እይታ በጭራሽ ተግባራዊ መሆን የማይችል ነገር ነው በአንቀፁ የተቀመጠው፡፡ እውነተኛ  ውይይቶች በሚጀመሩበት ጊዜ፣ ይሄ አንቀፅ ይሰረዛል የሚል ግምት አለኝ፡፡ እኔ በግሌ፣ አንቀፁ ድሮም አሁንም አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡ ዝም ብሎ የተቀመጠ የማወዛገቢያ አንቀፅ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ብሄር-ተኮር ጥቃትና  መፈናቀል እንዴት መፍትሄ ያገኛል ይላሉ?

ያለ ጥርጥር ብሄርተኝነት የሀገሪቱ ስጋት ነው፡፡ አንድ የራሱን ስም መጠበቅ የሚችል መንግስት፤ የመጀመሪያ ተግባሩ የህዝብን ህይወት መጠበቅ ነው፡፡ ዛሬ በየቦታው የምናየው ብሄር ተኮር ጥቃትና መፈናቀል ትልቅ ስጋት ነው፡፡ በእነ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው ለውጥ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ምርጫ ማድረግ ወደሚያስችለን ሁኔታ የሚሸጋገረው፣ እነዚህ ጥቃቶች መላ ሲያገኙ መሆኑም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ ወርቃማ እድሎች እንዳያመልጡን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ይሄን እድል እየመራ ሊያሻግር የሚችል አመራር ከገዢው ፓርቲ ውስጥ ወጥቷል፡፡ አሁን የሚጠበቀው ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተመስርቶ ስልጣን በምርጫ ብቻ የሚያዝበት ስርአት መመስረት አለበት፡፡ ከሰሞኑ ከሚታዩ ግጭቶች አንፃር ብዙዎች በስጋትና በተስፋ ውስጥ ናቸው፡፡ ስጋቱን አጥፍቶ ተስፋውን የበለጠ ለማለምለም፣ ሁላችንም  ወደ ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነታችን መመለስ አለብን፡፡

በስፋት የገነነው አክራሪ ብሄርተኝነት እና  ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ማስታረቅ ይችላል?

በመጀመሪያ በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው የሚለውን በሰከነ ጥናት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ለሁሉም እንደየ መልኩ ምላሾችን ማዘጋጀት ነው፡፡ አብሮ ለመኖር ፍላጎት የለንም የሚሉ ወገኖች ሀሳብ ተደምጦ፣ በአኗኗር ረገድ ከተቀመጠው ቀመር አንፃር፣ ክርክርና ውይይት መደረግ አለበት፡፡ መታረቂያ መንገዶቹ፣ እንዲህ ያሉ ጠንካራ ውይይቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን መንግስትም  ለህዝብ መብት ጥሰትና የመኖር ዋስትና አደጋ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እየወሰደ፣ ከህገ-ወጥነት ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ አለበት፡፡ መንግስት ጠንከር ያለ ስራ መስራት ይገባዋል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ላይ ሰፋፊ ውይይቶች ተደርገው፣ የህግ መቋጫ ማግኘት መቻል አለባቸው፡፡

ከብሄርተኝነት ፖለቲካ በመውጣት ወደ ዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ መሸጋገር የምንችልበት ዕድል አለ ብለው ያስባሉ?

ይሄ በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚመጣ ጉዳይ ነው። እኔ ኖርዌይ ስኖር፣ እንደ አንድ ሰው፣ ሰው በመሆኔ ብቻ መብቴ ይከበራል፡፡ ማንም ተቆጥሮ የተሰጠንን መብት መጋፋት አይችልም፡፡ የጤና፣ የህይወት ዋስትና የማግኘት መብት ሁሉ አለኝ፡፡ ይሄ እንግዲህ ከፍታ ላይ የመድረሳቸው ውጤት ነው፡፡ እነሱ የብሔረሰብ ችግርን ፈትተው ዜጋ በዜግነቱ ብቻ የሚከበርበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ አይነቱ ሥርዓት እንዲፈጠር ረጅም  ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የዜግነት ፖለቲካ ጉዳይን እንደ ሩቅ ጊዜ ግብ ነው የማየው፡፡

ከ26 ዓመት በኋላ ነው ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት። ኢትዮጵያን እንዴት አገኟት?

እውነቱን ለመናገር ብዙ ተዘዋውሬ አልተመለከትኩም፡፡ ነገር ግን ይሄ የብሄርና የማንነት ክፍፍሉ፣ እዚህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው የውጭ ሀገራትም የሚታይ ነው። ያው የዚህ ነፀብራቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ማህበረሰባዊ ስነ ልቦናው ቀድሞ ከማውቀው መለወጡ ብዙም አልገረመኝም፡፡ ይሄን ለመለወጥ፣ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎች አካላት በሙሉ በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

እርስዎ የተወለዱት በኤርትራ – ቀይ ባህር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነዎት ወይስ ኤርትራዊ?

እኔ ራሴን እንደ ኤርትራዊ ቆጥሬ አላውቅም፡፡ ያኔም ኤርትራዊነትን አልመረጥኩም፡፡ በህዝበ ውሳኔው ወቅትም አልተሳተፍኩም፡፡ በካይሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማት በነበርኩበት ወቅትም፣ ሁኔታውን ተቃውሜ ነው ስራዬን የለቀቅሁት፡፡ በዚያው ወደ ኖርዌይ ሄድኩ፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ ነው የማምነው፤ ነገር ግን አይደለህም ከተባልኩ እንግዲህ፣ ኖርዌይ ተቀብላኛለች ማለት ነው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን የቀይ ባህር አፋር ህዝብ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ እንደሚያምን መናገር እችላለሁ፡፡

Filed in: Amharic