>

የኦነግን አቋም ሌሎች ታጣቂ ኃይሎችም መጋራት ነበረባቸው! (አምሳሉ ገብረኪዳን)

የኦነግን አቋም ሌሎች ታጣቂ ኃይሎችም መጋራት ነበረባቸው!
አምሳሉ ገብረኪዳን
“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ!” አሉ አበው ሲተርቱ፡፡ አንድ የገባኝ ነገር ቢኖር ኦነግ መታለሉንና የጠራ ስምምነት ሳይኖረው ሆን ተብሎ በተድበሰበሰ ስምምነት ተዋክቦ እንዲገባ መደረጉን ነው፡፡ መድበስበሱ የጠፋቸውና የፈለጉትም አይመስለኝም፡፡ ነገርግን ከሸአቢያ በኩልም ስምምነቱን ገብተው እንዲጨርሱት ጫና ሳይደረግባቸው የቀረ አይመስለኝም፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሳ አሁን ማምሻውን ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ስኳር ስኳር የሚል ነገር ተናግረው ነበር፡፡ አሳዛኙ ነገር ሊሆን የሚችል አለመሆኑ ነው፡፡
ኦነግ የሀገር ሠራዊትንና የሕወሓት/ኢሕአዴግን ሠራዊት ነጣጥሎ ነው የሚያየው፡፡ ይቀጥልና “በሽግግር መንግሥት ወቅት ግፍ የፈጸመብኝ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሠራዊት ታጥቆ ባለበት ሁኔታ እኔ ትጥቅ የምፈታበት ምክንያትና አግባብነት  አይታየኝም! እኔ ትጥቅ እንድፈታ ከተፈለገ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሠራዊትም ይፍታ! የታጠቀ ኃይል ለሰላም አስተዋጽኦ የለውምና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ውጭ ያለነው የታጠቅን ኃይሎች ሁሉ ትጥቅ መፍታት አለብን!” የሚል የሚጣፍጥ ነገር ተናግረዋል (which is interesting and favorable idea)
ይሄ የኦነግ አቋም ከልብ ቢሆንና ቢፈጸም እንዴት ጥሩ ነበረ መሰላቹህ፡፡ ነገር ግን ይሄንን ኦነግ “ከመንግሥት ጋር የተስማማነው ይሄንን ነው!” የሚለውን ስምምነት ይፈጸማል ብሎ ተስፋ ማድረግ እጅግ ሲበዛ የዋህነት ነው፡፡
ቆይ ግን ግራ የገባኝ ነገር ኦነግ “የተስማማነው በዚህ ነው!” የሚለው ነገር ተፈጻሚ የሚሆን ባይሆንም ቅሉ የሕወሓት/ኢሕአዴግን ሠራዊት ከኢትዮጵያ ሠራዊት እንዴት ነው መለየት የሚቻለው??? ተዋግቶ የገባውን የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሠራዊት ነው ካላልነው በስተቀር፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በተለይም “የኢትዮ/ኤርትራ ጦርነት” በሚሉት ጦርነት ወቅትና ከዚያም በኋላ ለሀገር ብሎ መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀለውን ደግሞ የኢትዮጵያ ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊት  ብለን ልንለየው ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምን መለየት ይቻላል??? እንዲህ ብለን ከለየነው ግን አሁን ብዙዎቹ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሠራዊት አባላት በጡረታ የተገለሉ በመሆናቸውና የቀሩትም ጥቂቶች በመሆናቸው እነሱን ጠራርጎ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ማስወገድና ትጥቅ ማስፈታት ቢቻል እንዴት ጥሩ ነበረ፡፡
ለማንኛውም ይሄንን የኦነግ አቋም ሌሎች ትጥቅ ፈተው የገቡ ታጣቂ ኃይሎችም መጋራት ነበረባቸው፡፡ ዋናው አሸባሪ ቡድን ታጥቆ ባለበት ሁኔታ ትጥቅ ፈትቶ መግባት እውነትም የለየለት እብደት ነው፡፡ ለማንኛውም ኦነግ የሚለው ነገር ፈጽሞ ይሳካል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በሉ እንግዲህ እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ያፈሰሳቹህት የንጹሐን ደም አሳልፎ ሰጥቷቹሃል ደኅና ይሁኑ!!! ወያኔ ደግሞ ቀኑን ይጠብቅ!!!
Filed in: Amharic