>
5:13 pm - Sunday April 19, 3953

ወደፊት መሄድ ያልቻልነው ወደኋላ መሄድ ስላበዛን ነው!!! (አስቻለው አበራ)

ወደፊት መሄድ ያልቻልነው ወደኋላ መሄድ ስላበዛን ነው!!!
አስቻለው አበራ
በታሪክ መኩራት አንድ ነገር ነው ፣ ነገር ግን ከመጠን በላይ ለጥጠነው አሁን ያለውን ሕይወታችንን እና የወደፊቱን የልጆቻችንን ህይወት የሚያደፈርስ ከሆነ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እጅግ ስለሚያመዝን አወዛጋቢ የሆነው ታሪክ ላይ መሟዘዙ ጅልነት ይመስለኛል!
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ችግር ብሔረተኝነት ወይም በአንዳንዶች አገላለፅ ዘረኝነት ሳይሆን ስንፍና ነው፣ ብሄረተኝነታችንን ያጎላው ስንፍናችንን ላለመቀበል በምንሰጠው ሰንካላ ምክንያት ነው የሚል መንፈስ ያለው ነገር ፅፌ ነበር።
ዛሬ ደግሞ ሁልጊዜ በአእምሮዬ ሲብሰለሰል በቆየውና ሌላው ዜግነታችንን ትተን ብሄረተኝነታችን ላይ እንድናተኩር ስላደረገን እና ወደ ኋላ ስላስቀረን ሁለተኛው ምክንያት ለመፃፍ እሞክራለሁ።
የዛሬው ፅሁፌ ጭብጥ የሚያተኩረው  “ወደፊት መሄድ ያልቻልነው ወደኋላ መሄድ ስላበዛን ነው” ከሚለው ከፅሁፌ አርእስት ጋር ይዛመዳል። ይሄውም ለታሪካችን  ከሚገባው በላይ ትኩረት በመስጠታችን ነው በሚል መነሻ የተፃፈ ነው።
ምንም ዕንኳን ኢትዮጵያ ጥንታዊ ፊደል ካላቸው ጥቂት ሐገሮች አንዷ ብትሆንም ካለችበት ድህነት አንፃር እና ብዙ ህዝቧ ያልተማረ በመሆኑ ምክንያት ብዙ ታሪኮች በአፈ ታሪክነት ከትውልድ ትውልድ የተላለፉ እና በከፊል በውጭ ሐገራት ዜጎች የተፃፉ ናቸው።
ታሪክ የሚጻፈው ደግሞ ሁልጊዜ እውነቱን ለመዘከር ሳይሆን የፀሀፊውን እና ያፃፊውን (በከፊል መንግሥታት) በጎ ገፅ ለመገንባት ነው።
ስለዚህ የተፃፈ ሁሉ የግድ እውነት ላይሆን ይችላል። እውነት እንኳን ቢሆን የእኛ አስተዋጽኦ በሌለበት እና አሁን መቀየር በማንችለው ነገር  እርስበርስ መነታረኩ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስለኛል።
ሁላችንም ኢትዮጵያ በታሪኳ በህዝብ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዳልነበራት የምንተማመን ይመስለኛል።
ከዲሞክራሲ አስተዳደር ውጪ ያሉት አማራጮች ደግሞ  የንጉሳዊ አገዛዝ (aristocratic) እና የአምባገነን ስርአቶች ናቸው።
ከደርግ በፊት የነበሩት አገዛዞች የንጉሣውያን ስርአቶች ሲሆኑ፣ የደርግ እና የወያኔ ስርአቶች ደግሞ የአምባገነን ስርአቶች ናቸው።
ሁለቱም የአገዛዝ አይነቶች ጨቋኝ ስርአቶች ናቸው። ጨቋኝ ከአለ ደግሞ ተጨቋኝ ይኖራል ማለት ነው።
አወዛጋቢ የሚሆነው የተወሰንነው ወገኖች የቀደሙት ገዢዎች  ጨቋኝነታቸውን እያወቅን ከጨቋኝነታቸው ይልቅ ጀግንነታቸው ላይ ማተኮራችን ላይ ነው።
የተወሰንነው ደግሞ የቀደሙት ገዢዎች ጨቋኝ ቢሆኑም ቢያንስ የውጪ ጠላትን በመመከት ያላቸውን ጀግንነት ላለመቀበል መፈለጋችን ነው።
በእኔ አስተያየት ሁለቱም እምነቶች በክህደት ወይም denial ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
ለምሳሌ የትግራይ ሰዎች በጀግንነት የሚያሞጉሷቸወ አፄ ዮሐንስ ወሎን አስገድደው ክርስቲያን ያደረጉ እንደሆኑ በታሪክ ይነገራል። ስለዚህ አፄ ዮሐንስ ለትግሬዎች እና ለሌሎች ክርስቲያን ወገኖች ጀግና ቢሆኑም ለሙስሊሞች ደግሞ ላይመቹ ይችላሉ ።
በጎንደሬዎች እና በከፊል ኢትዮጵያዊው ጀግንነታቸው የሚወሳው አፄ ቴዎድሮስ “እጅ ነስተው ሄዱ” ተብሎ እስኪገጠምላቸው ድረስ ጨካኝ እንደነበሩ ይነገራል።
ሸዋዬውና አብዛኛው በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው ወገን እምዬ እያለ በፍቅር የሚጠራቸው አፄ ሚኒሊክ ደግሞ ኤርትራዊያን ለጣሊያን አሳልፈው ሰጥተውናል በሚል እንደ ከሐዲ ሲቆጥሯቸው አብዛኛው ኦሮሞ እና የተወሰነው የደቡቡ ክፍል ደግሞ እንደ ጨካኝ ወራሪ እንደሚያዪቸው ግልፅ ነው።
የቅርቡ መለስ ዜናዊ እንኳን ምንም እንኳን ብዙ ኢትዮጵያዊያን እንደ ከሐዲ እና ከፋፋይ ቢያዪትም ብዙ የትግራይ ሰዎች (በወገንተኝነት) እና ሌሎች በቀደመው ስርአት የአማራ የበላይነት ነበረ ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች እንደ ነፃ አውጪያቸው ያዩታል።
ከላይ ለመዘርዘር እንደሞከርኩት ሁላችንም የቀደሙት መንግሥታት ሁሉ የሆነ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ነው የምንለውን ክፍል በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሲጨቁኑ እንደነበረ ልባችን ቢያዉቅም ጨቋኙ የእኔ ከምንለው ወገን ከሆነ ጀግንነቱ እንጂ ጨቋኝነቱ ሊታየን አለመቻሉ ነው።
ስለዚህ የቀድሞ ስርአቶችን በጨቋኝነት ሣይሆን በጀግንነት ለሚያዪ ሰዎች ምርጫው በጣም ቀላል ይመስለኛል። ይሄውም ከሞቱ ዘመናት ላስቆጠሩ የእኔ ለምንላቸው ነገር ግን ሌላው ወገኔ ነው የምንለውን ኢትዮጵያዊ ላስከፉ ጨቋኝ ገዢዎች  በመወገን አሁን በአካል ከሚኖሩ ወገኖቻችን ጋር መናቆር፣ ወይንስ ያለፈውን ታሪክ ለታሪክ ፀሐፊዎች ትተን በሕይወት ከአሉ ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስራችንን ማጠናከር የሚሉት ናቸው።
በሌላው ወገን ያሉት ማለትም የቀድሞ ገዢዎች ጨቋኝነት እንጂ ጀግንነት (የአፄ ሚኒሊክ እና የእቴጌ ጣይቱ  የጣሊያን ድል) ለማይታያቸው ሰዎችም ምርጫው ቀላል ይመስለኛል።
ይሄውም ቅድመ አያትህ ቅድመ አያቴን ገሎ ወይም አስገድዶ  ከመሬቱ ስላስነሳው እኔ ደግሞ በተራዬ የቅድመ አያቴን መሬት አስመልሳለሁ በሚል አይነት መንፈስ ከወገናቸው ጋር መናቆር ወይስ ያለፈውን መቀየር አይቻልም፣ ምናልባት አፄ ሚኒሊክ በግድም ቢሆን ኢትዮጵያን ባያስፋፉ ኖሮ ጣሊያንን የመመከት አቅም አይኖራቸውም ነበር።
ስለዚህ አያቶቻችን ተበድለውም ቢሆን ከቅኝ ተገዢነት አትርፈውናል በሚል ስሌት በጎ ጎኑን በማየት አሁን በሕይወት ካለው ወገናቸው ጋር በፍቅር መኖር የሚሉት ናቸው።
እጅግ በጣም ይቅርታ ይደረግልኝ እና በታሪክ መኩራት አንድ ነገር ነው ፣ ነገር ግን ከመጠን በላይ ለጥጠነው አሁን ያለውን ሕይወታችንን እና የወደፊቱን የልጆቻችንን ህይወት የሚያደፈርስ ከሆነ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እጅግ ስለሚያመዝን አወዛጋቢ የሆነው ታሪክ ላይ መሟዘዙ ጅልነት ይመስለኛል።
ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገኔ ያለኝ አስተያየት ቢኖር ፣ መቀየር በማንችለው በቀደመው ታሪካችን ምክንያት መናቆር ሁላችንንም የሚያከስረው አማራጭ (loose-loose game) ሲሆን ፣ ታሪክን ለታሪክ ፀሐፊዎች በመተው ብሄር እና ሐይማኖት ሳንለይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር እና አዲስ ታሪክ በጋራ በመስራት ላይ ማተኮር  ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርገው አማራጭ (win- win game) መሆኑን ነው።
Filed in: Amharic