>

ዝክረ ዶክተር በላይ አበጋዝ  (ደሴ ሙጋድ)

ዝክረ ዶክተር በላይ አበጋዝ
ደሴ ሙጋድ
* ልብን ለልብ ማስገዛት ልባዊነትን ይጠይቃል፤ ልብን በልብ መተካት ልበኛነትን ይታጠቃል፤ ልብን በልብ ለማዳንም አዋቂ ልብን ያስናፍቃል።
 ዶክተር በላይ ህዳር 13 ቀን 1937 ዓ/ም ኩታበር ዉስጥ ነበር የተወለዱት በወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡
 በሀረር ወታደራዊ ትምህርት ቤትም የወታደር ሳይንስ ተምረው የሌተናል ኮሌኔልነት ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡
 ጎበዝ ወታደር ሆነውም በንጉስ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ አራት ጊዜ ተሸልመዋል;የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን እንደጨረሱ ዩኒቨርሲቲ ገብተው አጠቃላይ ህክምናን ነበር ያጠኑት።
 30 ዓመት ሲሞላቸዉ ነዉ የልብ ሕክምናን በተለይም የሕፃናትን ልብ ሕክምናንና ለማጥናት የወሰኑት።
 ምክንያታቸዉንም ሲናገሩ “በየዓመቱ ከ50ሺህ ህፃናት ከልብ በሽታ ጋር ይወለዳሉ።
 በተጨማሪ ከ50 ሺህ- 60ሺህ ደግሞ ከተወለዱ በኋላ የልብ በሽተኛ ይሆናሉ። ሕክምናዉን ስለማያገኙ ደግሞ ይሞታሉ።” ይላሉ።
ዉሳኔያቸዉን በተግባር ለዉጠዉ በሕጻናት ልብ ህክምና ስፔሻላይዝድ አደረጉ፡፡
 ዶክተር በላይ ከ1973 ዓም ጀምረው ላለፉት ከ35 ዓመታት በላይ በሕጻናት ሕክምናና በሕጻናት ካርዲዮሎጂስትነት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር አገልግለዋል፡፡
 ዶ/ር በላይ ከሕክምናው በተጨማሪ ፔዲያትሪክስን በማስተማር፣ ስለ ሞያውም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማሳተምም ይታወቃሉ፡፡
 በተጨማሪም በተለያዩ አካዳሚዎች ዉስጥ ተሣትፎ በማድረግ ይታወቃሉ።
 ከነዚህም ዉስጥ ከ1981 ዓም ጀምረው የአሜሪካ ፔዲያትሪክስ አካዳሚ አባል ሲሆኑ፣
በInternational Society of Hypertension in Blacks,
The Pan African Society of Cardiology,
The National Drug Advisory Board of Ethiopia አባል ሲሆኑ በEthiopian Medical Journal በአባልነት፣ በረዳት ዋና ጸሐፊነትና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል፡፡
 የHealing the Children USA, Save a Child’s Heart ISREAL and Chain of Hope UK ተባባሪ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ላየንስ ክለብ አባልና ዋና አራማጅ ናቸው፡፡
 ዶክተር በላይን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በስፋት ያስተዋወቃቸዉ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ድርጅት ነዉ። የልብ ሕመም ያለባቸው ሕጻናት ውጭ አገር ሄደው ለመታከም የሚያስችል ዐቅም ስለሌላቸው የሚያጋጥማቸውን ጉዳት ለመቀነስ በመላው ዓለም ዞረው የመሠረቱት ከሀገራችን ችግር ፈቺ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ የህጻናት የልብ ህክምና ሆስፒታልን ለመክፈት ያላሰለሰ ጥረት አድርገው ራዕያቸውን አሳክተዋል፡፡
ስለ አመሠራረቱ እንዲህ ይላሉ፡-
“በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ማዕከል የማቋቋም ሀሳብ የተጠነሰሰው የዛሬ 40 ዓመት ገደማ በ1970 ዓ.ም በአሜሪካ ነው፡፡ በልብ ህክምና ሙያ ለመሰልጠን (ስፔሻላይዝድ ለማድረግ) በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቅኩበትን የትምህርት ማስረጃና የወደፊት ፍላጎቴን የሚገልጽ ሀሳብ ለኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ አቀረብኩ፡፡
ቃለ-መጠይቅ ያደረገችልኝ ፕሮፌሰር ኢጂኒ ዶይል፤ “የምንቀበለው 10 ሰዎችን ነው፡፡ አንተ የተቀመጥከው 10ኛ ላይ ነው፡፡ ባቀረብከው ማመልከቻ ውስጥ ጥሩና ደስ የሚሉ ነገሮች አይቻለሁ፡፡ ስላቀድካቸው ነገሮች ከአንደበትህ መስማት እፈልጋለሁ፡፡ እውነት ትምህርትህን ስትጨርስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ፣ በልብ ህክምና ትሰራለህ?” በማለት ስትጠይቀኝ፡፡ “አዎ!” በማለት መለስኩላት፡፡
ፕሮፌሰሯም፣ “ኢትዮጵያ ተመልሰህ የልብ ሆስፒታል በሌለበት፣ መሳሪያ በሌለበት፣ ባለሙያ በሌለበት፣ እንዴት ነው የልብ ህክምና እሰራለሁ የምትለው?” ሲሉ ደግማ ስትጠይቀኝ ፤ “መላ እፈልጋለሁ – I will find a way” አልኳት፡፡
ቤት ስመለስ ፊቴ ላይ የመከፋትና የኀዘን ስሜት ያየችዉ ባለቤቴ፣ “ምነው ተከፋህ? አልተቀበሉህም እንዴ?” በማለት ጠየቀችኝ ፡፡ “መቀበሉንስ ተቀብለውኛል፡፡ ነገር ግን አራት ነገሮች አርግዤ መጣሁ” አልኳት።
ዶ/ር በላይ አበጋዝ የፀነሷቸው አራት ነገሮችም፡-
– የልብ ሆስፒታል መገንባት፣ 
– ውድና ልዩ የሆኑትን የልብ ህክምና መሳሪያዎች ማሟላት፣
– የሰው ኃይል (ካርዲዮሎጂስት) ማፍራትና 
– ሆስፒታሉ በገንዘብ አቅም ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል ናቸው፡፡ 
ይዘግይ እንጂ የዶ/ር በላይ አበጋዝ ራዕይ እውን ሆነ፡፡ ሆስፒታሉ፣ በኢትዮጵያ ህዝብና በሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አላሙዲ ትብብርና ድጋፍ ተሰርቶ በ2001 ዓ.ም ተመረቀ፡፡ ውድ የሆኑት ዘመናዊ የልብ ቀዶ ህክምና መሳሪያዎች፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ በሆነው “ቼይን ኦፍ ሆፕ ዩኬ” ተሟላ፡፡ የልብ ቀዶ ሀኪሞች (ካርዲዮሎጂስቶች) የሚኒያፖሊስ የልብ ቀዶ ሀኪም በሆኑት በዶ/ር ቪብ ክሸንትና ታዋቂ በሆነው የህንድ ናርያና ሆስፒታል ሰለጠኑ፡፡
#የብሩክ የሕክምና አገልግሎቶች ድርጅት ባለቤት የሆኑት ዶክተር በላይ ለበርካታ አመታት ደከመኝ ሠለቸኝ ሳይሉ በወቅቱ የሚያጋጥማቸው መስናክሎችና ችግሮች ሳይበግራቸው ለሀገራቸው በህክምናው ዘርፍ የማይረሳ አሻራ ጥለዋል በዚህም ምክንያት በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጭ በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በ2008 ዓ/ም በልብ ህክምና ዘርፍ ባደረጉት በጎ አስተዋጽኦ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማእረግ ተቀብለዋል፡፡በአሁኑ ሰአት ኑራቸውን በአዲስ አበባ በማድረግ የማማከርና የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
*ረጅም እድሜና ጤና ለዶክተራችን*
ምንጭ:- አማራ መገናኛ ብዙሃን፣ጀማል ሙሄ፣ዊኪፒዲያ እና ከተለያዩ
Filed in: Amharic