>
6:19 pm - Friday August 19, 2022

ሁሉም ፖለቲከኛና የፖለቲካ አስተማሪ ሆኗል፤ አውቅልሀለሀ ባዩም በዝቷል!!! (ቹቹ አለባቸው)

ሁሉም ፖለቲከኛና የፖለቲካ አስተማሪ ሆኗል፤
አውቅልሀለሀ ባዩም በዝቷል!!!
ቹቹ አለባቸው
* በነፃ ገበያ ቢወዳደር 3000 ብር ዋጋ የማያወጣ፤ አንድ የብአዴን/አዴፓ አመራር፤ዛሬ ላይ እነ እንቶኔ ስለወደዱት ብቻ በትንሹ ባለ 20, 000፤ 30, 000፤ 40, 000 ፣ 50, 000 ደሞዝተኛ ሁኖ ታገኘዋለህ፡፡ታድያ እንዲህ አይነት ሰዎች፤የህዝብን አጀንዳ ወደ ጎን ትተው፤ቀን ከሌት ስለ ራሳቸው ጉዳይ ቢጨነቁ ምኑ ይገርማል???
 
1. ክራሞታችን!!!!
የአማራን ፖለቲካ፤ከኢህዴን -ብአዴን-አዴፓ ጋር ሁኘ ቢያንስ ለ28 አመታት ጥሩ አድርጌ ተከታተልኩት፡፡ በዚህ ቆይታየ እጅግ ብዙ ቁምነገሮችን ገበየሁ፤እጅግ ብዙ ነገሮችንም ታዘብኩ፡፡ የገበየኋቸውን መልካም ነገሮች ለጊዜው ልተዋቸውና፤ የታዘብኳቸውን ፤በተለይም ደግሞ እስከዛሬም የቀጠሉትንና፤ ለወደፊቱም ሊቀጥሉ ይችላሉ ብየ የምሰጋባቸውን አንዳንድ ወሳኝ ነጥቦች ማንሳት ወድጃለሁ፡፡
በኢህዴን/ በብአዴን ቆይታየ ከታዘብኳቸው ችግሮች መካከል ዋነኛዉና ትልቁ ነገር፤ በድርጅቱ ውስጥ የሚካሄደው የሰዎች ሹመትና ምደባ ፍትሀዊነት መጓደል አንዱ ነው፡፡ በዚህ በኩል፤በትክክል የተሰሩ ስራዎች አልነበሩም፤ዛሬም የሉም ባልልም፤ችግሩ ግን ስር የሰደደና፤ምን አልባትም ፈጥኖ ካልታረመ በስተቀር፤የአማራን ክልል ወደ ቀውስ ሊከት የሚችል አደጋ ሊሆን እንደሚችል እስጋለሁ፡፡
በክልለችን፤የሰዎች ምደባና ሹመት፤በዋነኛነት ለትልልቆቹ አመራሮች ባለህ ቀረቤታ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ትልልቆቹ አመራሮች ከወደደሁ፤አንተ ብትማር፤በፖለቲካ ብትበስል ባትበስል፤ችግር የለውም፡፡ ካንተ የሚጠበቀው ትልቁ መስፈርት የነሱ አሸርጋጅ መሆን ነው፡፡ በዚህ መልኩ፤እጅግ ብዙ አመራር ወደ ስልጣን መጥቷል፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ስልጣን የመጣ አሸርጋጅ ሁሉም፤ዛሬ ላይ ከብሯል፤ባለ 1/2/3/ ፎቅ ቤት ባለቤት ነው፤ባለ V8 ወይም ባለ ጥሩ መኪና ባለቤት ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች፤በሆነ አጋጣሚ እንኳን ከሀላፊነት ቢነሱ፤ምርጥ የተባለ ቦታ ተፈልጎላቸው ይመደባሉ፤ይህ ምርጥ ቦታ ከጠፋም፤በህግ ያልታወቀ የስራ መደብ ይፈጠርላቸዋል፤ በዚህመ መሰረት ተዘፍዝፈውበት ከከረሙት ስልጣን በሆነ አጋጣሚ ቢነሱ እንኳን፤ ሰናይ ኖሯቸውን እንዲገፉ ይደረጋል፡፡ይሄ አሰራር ላለፉት 27 አመታት ቀጥሏል፡፡ ይሄን ሁሉ የተበላሸ አካሂያድ ደግሞ፤ መላ የብአዴን አባላትና የአማራ ህዝብ አንጀታቸው እያረረ በአንክሮት ሲከታተሉትና ሲታዘቡት ከርመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት፤በአማራ ክልል የሚካሄደው ሹመትና ምደባ፤ሜሪት ቤዝድ ነው ብሎ ሚያምነው ሰው ቁጥር፤እጅግ ሲበዛ ትንሽ ይመስለኛል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ፤ ምንም አስር ጊዜ የተማርክ ብትሆን፤በአመራርና በፖለቲካው ብትበስል፤እውነት ብትናገር ወዘተ….አንተ ለብአዴን ታላለቆቹ አመራሮች ፤እስካልተመቸሀቸው ድረስ፤ዋጋ ቢስ ነህ፡፡ስለሆነም፤ ሰበብ ተፈልጎልህ ከድርጅቱ እንድትርቅ ትደረጋለህ፡፡ያኔ ልክ ለእነሱ አሸርጋጆች እንደሚደረገው ሁሉ፤ላንተ ጥሩ ቦታ ተፈልጎልህ የምትመደብ እንዳይመስልህ፤ ይልቁንስ ለስቪል ሰርቪስ ቢሮ፤በሚመጥነው ቦታ መድቡት ተብሎ ደብዳቤ ይጻፍልሀል፤ የስቪል ስርቪስ አመራርም፤ቀድሞ ስለሚነገረው፤ ስራውን ይሰራል፡፡ የስቪል ስርቪሱ አመራር ከወደደህ፤ እንደምንም ቦታ ፈላልጎ፤በሚመጥንህ ይመድብሀል፤ከደበርከው ደግሞ፤ቦታው ስለሌለኝ፤አንድ ደረጃ ዝቅ ብለህ ተመደብ ይልሀል፤አንተም ደሀ ነህና እየቆዘምክ ትቀበላታለህ፡፡ ይሄ በግሌ የኔ የሂዎት የገጠመኝ እዉነታ ቢሆንም፤ብዙዎች የብአዴን አመራሮችንም የገጠማቸው እጣ ፈንታ እንደሆነም በደንብ አውቃለሁ፡፡ ይሄንን ኢ-ፍትሀዊ አሰራርም፤ በርካታ የብአዴን አባላት፤በተለይም የመንግስት ሰራተኛ አባላት በትዝብት ሲመለከቱት ኖረዋል፡፡
—–
ለዛሬው ይችን አጭር መጣጥፍ ለመጻፍ ያስገደደኝ፤ ከላይ ያነሳሁት ችግር ዛሬ ድረስ መቀጠሉ ስላሳሰበኝና አሁንም ሊደገም እንደሚችል ስጋቱ ስላደረብኝ ነው፡፡ ሰሞኑን በክልላችን ሽርጉዱ በዝቷል፡፡ የሚታጠፉና የሚዘረጉ የመንግስት መ/ቤቶች እንደሚኖሩ መታወቁን ተከትሎ፤ማታ ማታ፤ አመራሩ  በምናውቃቸው መሸታ ቤቶች ሲዶልት እንደሚያመሽ ደርሸበታለሁ፡፡ወሬው ሁሉ የማን መ/ቤት ሊታጠፍ ነው? እከሌ የት ቦታ ተመደበ/ ሊመደብ ይችላል?፤አይ- እነ እከሌ እንኳን እነ እከሌ እያሉላቸው ምንም አይሆኑም፤የነ እከሌ መ/ቤት ቢታጠፍም፤ ለሰዎቹ ጥሩ ቦታ ተፈልጎላቸው ይመደባሉ፤ወዘተ… የሚሉ ጭንቀቶች መበራከታቸውን ማወቅ ችያለሁ፡፡
አመራራችን፤በአሁኑ ወቅት ስንት አንገብጋቢ የአማራ አጀንዳዎች እያሉ( በተለይም የአዲስ አበባ ጉዳይ፤ የወልቃይትና እራያ ግድያና መፈናቀል: የጣናና ላሊበላ መከራ ወዘተ….)፤በዚህ አይነቱ አሳፋሪ አጀንዳ መጠመዱ፤ነገሩ አሳፋሪ ቢሆንም፤ገራሚ ግን ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም፤ለሱ ስልጣን የኑሮና የገቢ ምንጭ መሰረት ሁናለችና፡፡ አብዛኛው፤አመራር ከበላይ አመራሩ ጋር ባለው ቀረቤታ ብቻ፤ሀብታም ሁኗል፤ስለሆነም፤ይችን አድል ዛሬም እንዳያጣት ሲብተለተል ውሎ ቢያድር ማን ይፈርድበታል? በነፃ ገበያ ቢወዳደር 3000 ብር ዋጋ የማያወጣ፤ አንድ የብአዴን/አዴፓ አመራር፤ዛሬ ላይ እነ እንቶኔ ስለወደዱት ብቻ በትንሹ ባለ 20, 000፤ 30, 000፤ 40, 000/ 50, 000 ደሞዝተኛ ሁኖ ታገኘዋለህ፡፡ታድያ እንዲህ አይነት ሰዎች፤የህዝብን አጀንዳ ወደ ጎን ትተው፤ቀን ከሌት ስለ ራሳቸው ጉዳይ ቢጨነቁ ምኑ ይገርማል?
ይሄ እንግዲህ እስከዛሬ የመጣንበት መንገድ ነው፡፡ ችግሩ ግን፤ ይሄው በኔት ወርክ የመጠቃቀሙና የመመዳደቡ ጉዳይ አሁንም የመቀጠሉ ጉዳይ የማይቀር መምሰሉ ነው፡፡ በዚህ በኩል ድርጅት ጽ/ቤት የሚመደቡ ልጆች፤ትልቅ አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ሚና አላቸው፡፡ ወሳኙ ግን ርዕሰ መስተዳድሩ ናቸው፡፡ ምን አልባት አሁን ላይ ተስፋ የማደርገው፤ በአሁ ወቅት፤ድርጅት ጽ/ቤት በአዲስና ወጣት አመራሮች እየተደራጀ ስለሆነ፤ለሰው ኃይል መረጣና ምደባው፤ልዩ ትኩረት ይሰጣሉ ብየ እገምታለሁ፡፡ እነዚህ ልጆች ካሁን ቀደም፤ውጭ ሁነው በድርጅቱ የምደባና መረጣ አካሄድ ልክ እንደኛው ሲበግኑ የኖሩ በመሆኑ፤አሁን እነሱ እድሉን ሲያገኙ፤ያንን የከረምንበትን ስህት ይደግሙታል ብየ አልገምትም፡፡በርግጥ የመጨረሻው ስልጣን በሌሎች እጅ እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ ቢሆንም ግን፤ድርጅት ጽ/ቤት ያሉ ልጆች፤ይሄንን አብሮን የከረመውን፤ በኔት ወርክ፤በአቀረብሽን፤ በመንደርተኝነትና ጎጠኝነት ላይ ተመስርቶ ሲካሄድ የኖረውን ሹመት/ምደባ አካሄድ በማስተካከል ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ስለሆነም፤አሁን ድርጅት ጽ/ቤት የተመደባችሁ ልጆች፤የምታውቁትን በድርጅታችን ሰፍኖ የኖረውን፤አድሏዊ አሰራር በማስተካከል፤ ከወዲሁ፤የናንተ የድርጅት ጽ/ቤት አመራሮች ሁናችሁ መመደባችሁ፤ትክክል ስለመሆኑ፤ በናንተ ብቃትና ሀቀኝነት ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸውን ወገኖችም፤ እንደምታሳምኗቸውና በአጠቃላይ ማንነታችሁን እንድታስመሰክሩና፤ በሰው ዘንድም እምነት እንድታሳድሩ፤ ስል ወንድማዊ ጥሪየን አቀርብላች ኃለሁ፡፡
2. ቀጣዩ ፈተናዎቻችን ምን ምን ናቸው?
እስከዛሬ ባካሄድነው ተጋድሎ፤እጅግ ጥሩ የሚባሉ ድሎችን ተጎናጽፈናል፤በተለይም በነጻነት የመናገር፤ባንዲራችንን ስለለበስንና ስላውለበለብን አለመገደል፤ በማንም ዲቃላና እንኩዲ አለመሰደብ፤ አማራን በቀላሉ ለመመልከት ሲከጅሉ ለከረሙት ሁሉ፤ከኛ መጣላት ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ወዘተ …የመሳሰሉትን ድሎች ተጎናጽፈናል፡፡ ይሁን እንጅ፤ እነዚህ ውጤቶች፤የትግላችን መንደርደሪያዎች እንጅ፤ የትግለችን የመጨረሻ ግቦች አይደሉም፡፡ ዛሬም ድረስ ኮር አጀንዳዎቻችን( የወልቃይትና እራያ ጉዳይ፤አማራ በየቦታው መፈናቀል፤  የፍትሀዊነት ጠጠቃሚነት.ወዘተ….) አንዳቸውም አልተነኩም፡፡
አሁን ጥያቄው፤አሁን ላይስ ሁነን ቢሆን፤እነዚህን ኮር አጀንዳዎቻችን ለማስመለስ በሚያስችል ቁመና ላይ እንገኛለን ወይ? የሚለው ጥያቄው ነው ፡፡ በዚህ በኩል በግሌ ስጋት አለኝ፡፡ አሁንም ቢሆን ወደ ትክክለኛው ግብ የሚያደርስ መንገድ እየተከተልን አይደለም፤ በመሆኑም ጊዚያችን በወሬ ማለፉ አይቀርም፡፡ ችግራችን በወሬ ጊዜ ማሳለፋችን ብቻ ሳይሆን፤ ውስጣዊ አንድነታችንን አዳክመው፤ለሌሎች መጫዎቻ ሊያደርጉን የሚችሉ፤በግልጽ የሚታዩ ስጋቶችም አሉብን፡፡በነዚህ ስጋቶች ዙሪያ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል፤ዛሬ እያወቅን እንዳላወቅን፤ እየሰማን እንዳልሰማን፤ብናልፋቸው፤ነገ መከራው ሲመጣ፤ድሮም እናውቀው ነበር ብንል ዋጋ የለውም፡፡ ስለሆነም፤እኔ እስካለኝ ግንዛቤ ደረስ፤በቀጣይ የአማራን ፖለቲካ ውጥንቅጡን ሊያወጡት የሚችሉት ሁለት ዋና አደጋዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
ሀ . በጎጠኝነት፤ መንደርተኝነትና፤ መቀራረብ፤ እንዲሁም አስሸርጋጅና -አሸርጋጅነት፤ በመሳሰሉት ዘ-ልማዳዊ አሰራሮች ላይ ተገንብቶ የከረመው የመጠቃቀም ልማድ፤ክልሉን ወዳልተፈለገ ቀውስ ሊከቱት ይችላሉ፡፡ሰው ከውጭ ሆኖ፤ሰዎች ሲመደቡ ይታዘባል፤ወንበር ላይ የቅርብ ሰው ያላቸው ግለሰቦች፤ያላቅማቸው ሲመደቡ፤ቦታ ከጠፋም ለነሱ ተብሎ ብቻ አዲስ መደብ ሲፈጠርላቸው፤ሰው የሌላቸው ደግሞ እንደ አሮጌ ቁና የትም ሲወረወሩ፤ ይታዘባል፡፡ ብቻ በአሁኑ ወቅት የሆነ ሰው ከሆነ ቦታ ሲመደብ፤የተመደበው በችሎታው ሳይሆን፤ እነ እከሌ ስላሉለት  ነው የሚለው አመለካከት ገዥ ሆኗል፡፡ ይሄ አሰራ፤ ከላይ ተንጠልጥሎ የሚቀር ሳይሆን፤ሲስተም ሆኖ፤ነገሩ በሁሉም የክልሉ አካበባቢዎች የተለመደ አሰራር ሁኗል፡፡ ስለሆነም፤ችግሩ ክልል አቀፍ ነው ማለት ነው፡፡አሁን ችግሩ ካሁን በኃላ  ይሄን  የተበላሸ አሰራር በዘለቄታው ሊሸከም የሚችል ወጣት አይገኝም፡፡ ይሄንንን አድሏዊ አሰራር የሚመለከት ወጣት፤ አንድ ቀን ባልተጠበቀ ስአት፤አደባባይ ወጥቶ ነገሮችን በሙሉ ፍርስርስ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ስለሆነም፤ አዴፓ፤ከሁሉ በፊት ይሄንን የከረመ ችግር በድፍረት ቶሎ መቀየር አለበት፡፡ ካልሆነ እመኑኝ፤ይሄ አሰራር ካልተስተካከለ፤ክልሉን ወደ ቀውስ ያመራዋል፡፡
ለ.  ሌላው: ለክልሉ በቀጣይ  እንደስጋት ሆኖ ሊታይ የሚገባው፤ የአገራችን በተለይም የክልላችን ፖለቲካ፤ መደማመጥ የማይታይበት፤ ያልተረጋጋና ብስለት የጎደለው፤አላዋቂ ፖለቲከኛ የበዛበት መሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት፤ሁሉም ፖለቲካኛና የፖለቲካ አስተማሪ ሆኗል፤የፖለቲካ ተማሪ ነኝ ብሎ ሚያስብ ብዙም ሰው የለም፤ነገርን አሰላስሎ አቋም ከመውሰድ ይልቅ በስሜት መነዳት ካደር አደር እየጨመረ መጥቷል፡፡ አንዳንዱ ተሳድቦ ስለተናገረ ብቻ ፤ድል አድርጎ የሚያድር ይመስለዋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ እሱ የሚናገራት ቃል፤ስንት ጠላት አፍርታ እንደምታድር አይገባውም፤ በቃ! ለሱ ፖለቲካ ማለት፤ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፤የመሰለውን መናገር ነው፡፡ይሄ አካሄድ አደገኛ ነው፤ቶሎ ካልተስተካከለ፤አሁንም እመኑኝ፤ አይደለም ኮር አጀንዳዎቻችንን ማስመለስ፤ያገኘናትን  ትንሽ ድልም በቅጡ ሳናጣጥማት፤ወደ ነበርንበት የመመለስ እድላችን ዝግ አይደለም፡፡
3. ማጠቃለያ:-
ለሁሉም፤ለጊዜው ሰሚ ካገኘሁ፤ከላይ የጠቀስኳቸው ስጋቶች፤ ለአማራ የተረጋጋ ፖለቲካ ወሳኝ ስለሆኑ፤ ባለቤት ቢኖራቸው ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ እኔ በበኩሌ ላለፉት 27 አመታት እራሴንና  ቤተሰቦቸን ጭምር ጎድቸ፤በግሌ የሚጠበቅብኝን አማራዊ ድርሻየን ተወጥቻለሁ ብየ አምናለሁ፡፡ስለሆነም፤ካሁን በኃላ፤ ተተኪው ወጣት፤የአማራን ፖለቲካ፤ተረክቦ በጥንቃቄ መርቶ ወደ ግቡ እንዲያደርሰው እመክራለሁ፡፡ በኔ በኩል፤ ካሁን በኃለ፤በአማራ ክልል ያለው ፖለቲዊ ሁኔታ፤ውሀ ቢወግጡት እምቦጭ እየሆነ ስላስቸገረኝና ተስፋ እያስቆረጠኝ  ነው፡፡ ስለሆነም ፤በክልሉ ዙሪያ የሚኖረኝን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ቀነስ አድርጌ፤ እስኪ ደግሞ ፊቴን ወደ አዲስ አበባ ፖለቲካ ዘወር አድርጌ፤ እድሌን ለመሞከር  ወሰኛለሁ፡፡
ቸር ለሊት: ከሌሊቱ ከ8-9 ስአት ተጻፈ።
Filed in: Amharic