>
5:13 pm - Friday April 20, 1759

ወሬ ሲነግሩህ ሃሳብ ጨምርበት!!!

ወሬ ሲነግሩህ ሃሳብ ጨምርበት!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ኢትዮጵያ ውስጥ ካልተማረው ማይምነት የተማረው ማይምነት ይበዛል። ዶክተርና ፕሮፌሰር እየተባለ  ጎሰኛ  ካድሬዎች ያሰራጩትን ፈጠራ በስፋት ያስተጋባል። ጎሰኛ ካድሬዎች እየፈጠሩ  እንካችሁ የሚሉትን የፖለቲካ  ሸቀጥ «ምንጫችሁ ከምን?» ብሎ የሚጠይቅና እውነት ስለመሆኑ   የሚመረምርና የሚያጣራ  ስለሌለ  ሁሉም ትርክታቸው እንዳወረደው እየተቀበለ  እውቀት እያደረገላቸው ይገኛል።
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከተፈበረኩት የፈጠራ ታሪኮች መካከል «ኢትዮጵያ ሰላማዊ  የስልጣን ሽግግር  ኖሯት አያውቅም» የሚለው የብሔርተኞቹ ወግ ቀዳሚው ነው።  ምሁራንና ተንታኝ ነን በሚሊ ሰዎች ጭምር ኢትዮጵያ ውስጥ ሽግግር ወይንም የመንግሥት ለውጥ በተደረገ ቁጥር ደም ሲፈስ እንደኖረና በዐቢይ ዘመን ብቻ ይህ እንደቀረ ተደርጎ  እየተደጋገመ የሚነገረው  ትርክት እውነት አይደለም።
የሩቁን ትተን የቅርብ ጊዜው እንኳ ብንወስድ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ወደ ዳግማዊ ዓፄ ተክለ ጊዮርጊስ የተደረገው ሽግግር፤ ከዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ፤ ከዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ወደ ልጅ እያሱ የተደረገው ሰላማዊ ነበር። እንደውም የዚያ ዘመን ሽግግር አስቀድሞ የሚታቀድና የሚታወጅ ነበር። ከዐፄ ዮሐንስ እስከ ልጅ እያሱ የነበረው የሥልጣን ሽግግር ደም መፋሰስ ያልነበረበት ብቻ ሳይሆን  ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ እንዳትገባ በማሰብ  ከአንዱ ወደ አንዱ የሚደረገው የስልጣን ሽግግር  በእቅድ በተያዘው መሰረት የተከወነ  ሰላማዊ ጉዞ ነበር።
ዐፄ ዮሐንስና ከንጉሥ ምኒልክ ጋር በተስሟሟቸው ሶስት ስምምነቶች ሁሉ   አልጋ ወራሻቸው  ዳግማዊ ምኒልክ  እንደሆኑ ወደው ፈርመዋል። የዳግማዊ ምኒልክ አልጋ ወራሽ ደግሞ ልጅ እያሱ ናቸው። የሁለቱም መሪዎች አልጋ ወራሽነት  ወራሴዎቹ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የሚታወቅና የታወጀ ነበር።
በርግጥ ዐፄ ዮሐንስና ንጉሥ ምኒልክ ሲስማሙ የዳግማዊ ምኒልክ አልጋ ወራሽ  የዘውዲቱ ባል የዐፄ ዮሐንስ ልጅ  አርያ ሥላሴ ነበሩ። ሆኖም ግን አርአያ ሥላሴ ዐፄ ዮሐንስ በሕይዎት ሳሉ  በመሞታቸው ዳግማዊ ምኒልክ አልጋ ወራሻቸውን ለመምረጥ ተገደዋል።  የዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያው አልጋ ወራሽ  ልጃቸው መርድ አዝማች አስፋው ወሰን ምኒልክ ነበሩ። ለዚህም ነበር ዳግማዊ ምኒልክ ወደ ሐረር ሲሄዱ ለጦር መሪያቸው ለራስ ጎበና ዳጬ  «ከሞትሁ ልጄን  አስፋው ወሰንን አንግሰህ ኢትዮጵያን አብራችሁ እንድትገዙ አደራውን ላንተ ሰጥቼሃለሁ» ብለዋቸው  የዘመቱት።
ሆኖም ግን  መርድ አዝማች አስፋው ወሰን ምኒልክ አስቀድመው ሞቱ። ከእሳቸው ሞት በኋላ ለአልጋ ወራሽነት የታጩት  ወሰን ሰገድ ወዳጆ ጎበና ናቸው። እሳቸውም  አስደቅመው ከዚህ አለም ተለዩ።  ወሰን ሰገድ ወዳጆ ሲሞቱ አልጋ ወራሽነቱ ለራስ መኮነን ተሰጠ።  ራስ መኮነንም አስቀድመው ሞቱ። ራስ መኮነን  ሲሞቱ በመጨረሻ ላይ የአልጋ ወራሽነቱ ሥልጣን  ለልጅ እያሱ ተሰጠ። ይህ ሁሉ ሽግግር የተካሄደው በሰላም ነበር።  ይህ ሁሉ እንዳልነበረ ተቆጥሮ ዐቢይ አሕመድ አመጣሁት የሚለውን «ሽግግር» በኢትዮጵያ ታሪክ የተፈጠረ  ክስተት አድርጎ  ለማቅረብ ሲባል «ኢትዮጵያ ሰላማዊ  የስልጣን ሽግግር  ኖሯት አያውቅም» የሚለው ትርክት ታሪካችንን ካለማወቅ ወይንም ለማወቅ ካለመፈለግ የመጣ እንጂ   ቁም ነገር የለውትም።
ስለዚህ ሳይመረምሩ ሀሳብ የሌለበት ወሬ ይዘው «ኢትዮጵያ ሰላማዊ  የስልጣን ሽግግር  ኖሯት አያውቅም» የሚሉ ወሬ ደጋሚዎችን  «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር ልንለግሳቸው እንደወዳለን!
Filed in: Amharic