>

አፋርን በወፍ በረር ስንቃኛት...!. (ውብሸት ሙላት)

አፋርን በወፍ በረር ስንቃኛት…!.
ውብሸት ሙላት
1. የአፋር ክልል አብዝኃኛው ክፍሉ በርሃ ነው። ይህንን በርሃ አልምቶ የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል የሚችል፣ የተማረ አመራር ያስፈልገዋል። በርሃን ለማልማት ለሳይንሳዊ እዉቀት ቦታ የሚሰጥ አመራር አስፈላጊ ነዉ። ምሁራንን አሰባስቦ፣ አስተባብሮ የአፋርን ሕዝብ አኗኗር ማሻሻል ከአመራሩ ይጠበቃል። የክልሉ ፕሬዚዳንት 4ኛ (6ኛ?) ክፍል ድረስ ብቻ ነው የተማሩት። ይህን ለማድረግ ከትምህርት አንጻር ብዙ ይቀራቸዋል።
2. የአፋር ሕዝብ ማኅበራዊ ስሪቱ ጎሳን መሠረት ያደረገ ነው። የአፋር ሕዝብ ለጎሳ መሪዎች፣ ለሽማግሌዎች፣ ለባሕላዊ ሕግና ሥርዓት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል። የአፋርን ሕዝብ ለማድተዳደርም ለመምራትም ማኅበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣትም በአንድ በኩል የሕዝቡን ማኅበራዊ ስሪት ጠንቅቆ የተረዳ መሆን ይጠበቅበታል። በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራሉን ሕግጋት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በሚገባ የሚረዳ መሆን አለበት። ሁለቱንም በአግባቡ ተረድቶ የአፋርን ሕዝብ ሕይወት ሊያሻሽል የሚችል ፖሊሲ፣ሕግ፣አሰራር፣ተቋም ወዘተ መፍጠር የግድ ነው። ይህን ለማድረግ የሚችል የፖለቲካ አመራር ክልሉ ያስፈልገልዋ።
3. የአፋር ሕዝብ የአስተዳደር ብሂሉ የሚቀዳው በዋናነት ከባህላዊው የጎሳ ማኅበራዊ ስሪት መሆኑ ይታወቃል። አፋርን እንደ አንድ ሕዝብ ለማስተዳደር የሚዘረጉ የፓርቲም ይሁን የመንግሥት አሰራር ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ወደ ጎን በመተው ሊሆን አይችልም። መለወጥ ቢያስፈልግ እንኳን የጎሳ መሪዎችን ስምምነት ማግኘት ያስፈልጋል። በመሆኑም አሁን በክልሉ ያሉት የተሿሚዎች ስብጥርም በአብዴፓ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥም ያለው የጎሳ ስብጥር የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ማስተካከል ሲጠበቅበት የበለጠ በማጠናከር የተማሩና ብቁ አመራሮችን ከሥልጣን በማንሳት፣ ከሹመት ዝቅ በማድረግ ከአንድ ጎሳ (ከፕሬዚዳንቱ ጎሳ ብቻ) ብቻ በመመልመል ፣ለዚያዉም ብቃትና ትምህርትን ወደ ጎን ትቶ፣ ለአፋርም አይጠቅምም። እርስ በርስም ያጋጫል። በመሆኑም የአፋር ሕዝብን ማኅበራዊ ስሪት አላግባብ በመጠቀም (abuse በማድረግ) ሕዝቡን መምራት አስቸጋሪ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
4. የአፋር ሕዝብ ብዙ የተማሩ ልጆች አሉት። በተይያዩ የሙያ መስኮች የተማሩ። እነዚህን ምሁራን ሳያካትቱ፣ ከአመራር በማራቅ የሕዝቡን ሕይወት መቀየር አይቻልም። የሐጂ ስዩም አወል አመራር ይህንን መረዳት ይገባዋል ባይ ነው።
5. የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ምንም ድርድር አያውቅም። የአፋር ሕዝብን በአግባቡ ከሌላው ጋር አስማምቶ መምራት የሚችል የፖለቲካ መሪ ያስፈልገዋል። ሐጂ ስዩም በዚህም መልኩ ቢሆን መምራት የቻሉ አይመስሉም።
6. የአፋርን ሕዝብ  እያስከፉ፣ እራሳቸውን ከሕግም በላይ አድርገዋል። ሐጂ ስዩም ያሠሩትን ፍርድ ቤት አይፈታውም። የሚያስረውም የሚፈታውም እራሱ ሐጂ ስዩም ከሆነ ሰንብቷል። የድርጅቱንም አመራሮች እንዳሻው ያግዳል፤ ያባራል። እነ ጣሃን አባሯል። ጣሃ ማስተርስ አለው። የአብዴፓ ሊቀመንበር ሆኖ ወዲያውኑ አባረረው። ከዚያ ራሱ ሆነ። አሁን ደግሞ እነ እስማኤል አሊ ሴሮንና አወል አርባብን ከድርጅት አገዳቸው። ሐጂ ስዩም ለክልሉ ሕግ ነዉ። ሐጂ ስዩም ለክልሉ ፓርቲም ነው።
Filed in: Amharic