>

የኦነግ ወታደሮች ናቸው በተባሉና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ ተካሄደ! (ይድነቃቸው ከበደ)

የኦነግ ወታደሮች ናቸው በተባሉና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያ ተካሄደ !
ይድነቃቸው ከበደ
አቶ ዳውድ ኢብሳ የ40 ዓመት የጦርነት  ቆይታቸው በቀላሉ አልላቀቅ ብሏቸው ፤ ዘንድሮውም ከሰላማዊ ትግል በተፃራሪ መንገድ በመቆም ” ትጥቅ ብሎ መፈታት የማይታሰብ ነው ፤ ትጥቅ መፍታት የሚባል  (sensitive) ጥያቄ ነው” በማለት ” ትጥቅ ፈቱ መባልም ተገቢ እ አይደለም ከማለታቸው በተጨማሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ “ትጥቅ የሚፈታም የሚያስፈታም የለም” ማለታቸው የሚታወቅ ነው።
በአቶ ዳውድ የሚመራው ኦነግ ትጥቅ መፍታት እንደማይፈልግ መግለጽን ተከትሎ መንግስት በሰጠው መግለጫ ” ኦነግ ትጥቅ ያላስፈታቸውን የሰራዊቱን አባላት ትጥቅ የማያስፈታ ከሆነ መንግስት የዜጎቹን ደህንነትና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅ ሲል” እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቦ እንደነበረ የሚታወስ ነው።
በመንግስት እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት አሁን ወደ ለየለት ውጊያ እንደተሸጋገር መረጃዎች እያመላከቱ ነው፤ በተለይ በምዕራባዊ ኦሮሚያ ክልል በሚገኙት አከባቢዎች የኦሮሞ ነፃ አዉጭ ግንባር /ኦነግ/ ስራዊት ናቸዉ በተባሉና በኢትዮጵያ መከላክያ ሰራዊት መካከል ላለፉት ቀናቶች ግጭት ተቀስቅሷል። በሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለልቻ በሚመራው የሃገር መከላከያ ሰራዊትና በዳውድ ኢብሳ በሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወታደሮች መካከል ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ ፤ አቶ ለማ መገርሳ “ሁኔታዉ በጣም እንዳሳዘናቸዉ ገልፀዋል። ወጣቶች መሳርያ በመታጠቅ ዘመናዊ መሳርያ ከታጠቀዉ ከመንግስት ሰራዊት ጋር ለመወጋት ወደ ጫካ መግባታቸዉ ስህተት መሆኑን እና ትክክለኛ የትግል ስልት አለመሆኑን” ተችተዋል ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኦነግ ጦር ምዕራብ ኦሮሚያን እንዲቆጣጠር መንግስት እውቅና እንዲሰጠው ግንባሩ ያቀረበውን ጥያቄ በመንግስት በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ውድቅ መደረጉ ተግልፆሏ። በኦነግና በመንግሥት ወታደሮች መካከል በተደረገ ውጊያ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት የተከሰተ ሲሆን ፤ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የሰው ህይወት የጠፋ ሲሆን ይሄን በተመለከተ እስካሁን ሁለቱም ወገኖች በይፋ የሰጡት መረጃ ባይኖርም፤ በምዕራብ ወለጋ እና ነቀምት መንገዶቹ ተዘግቷል ፣ ባለዉ የፀጥታ አለመረጋጋት ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴን እና የንግድ ሂደት ተቆርጧል ።
Filed in: Amharic