>

የወልቃይት ጠገዴ መከራ፣ አጀቡሽ  መብራቱን  እንደማሳያ! (ጌታቸው ሽፈራው)

የወልቃይት ጠገዴ መከራ፣ አጀቡሽ  መብራቱን  እንደማሳያ!
ጌታቸው ሽፈራው
የወልቃይት ጠገዴን መከራ ብዙ ሕዝብ አያውቀውም።  በተለይ ከ2008 ዓም  በፊት  ብዙ ሰው የወልቃይትን መከራ አያውቀውም። አሁንም ድረስ ግን የወልቃይትን ሰቆቃ ብዙ ሰው ያውቀዋል ማለት ይከብዳል። በተለይ ወልቃይት   ጠገዴ የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት የተፈፀመበት  የመሆኑን ያህል የሚገባውን ትኩረት አግኝቷል ለማለት አያስደፍርም። በተለይ የዘር ማጥፋትና ማፅዳቱ “አማራ ነን” ባሉት ላይ በመሆኑና የአማራን ጉዳይ አጀንዳ ማድረግ አሁንም እንደነውር የሚቆጥረው፣  እንዳይታወቅ የሚፈልገውም  በመበራከቱ የወልቃይት ጩኸት የቁራ ጩኸት ሆኗል።
የወልቃይት ስቃይና መከራ በእናቶች ላይ ይብሳል። ባሎቻቸው ተገድለው መንገድ ላይ ሲጎተቱ እንዳያለቅሱ የሚከለከሉት ሴቶች ናቸው። ባሎቻቸው ተገድለው ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚሰቃዩት፣ በጥጋበኛ የትህነግ/ህወሓት ካድሬ የሚደፈሩት ሴቶች ናቸው። ትምህር ቤት የሚደፈሩት፣ መውጫ መግቢያ የሚያጡት ሴቶች ናቸው። ልጆቻቸው፣ ባሎቻቸው፣ ወንድሞቻቸው ታስረው የሚንገላቱት፣ ታፍነው ጠፍተውባቸው የትግራይ እስር ቤቶችን የሚያስሱት ሴቶች ናቸው።
ወልቃይት ጠገዴ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ግፍ የበረታ፣ ኢትዮጵያውያንም ዓለምም የዘነጋው በደል ነው። የአጀቡሽን መከራ ለወልቃይት ስቃይ እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል። አጀቡሽ  ገብሬ የተባለ የወልቃይት አማራን አግብታ ትኖር ነበር።  በግብርና የሚተዳደሩት ጥንዶች አንድ ልጅ አፍርተዋል።  “ሴቶችንና መሬቱን ነው የምንፈልገው” የሚሉት የትግራይ ባለስልጣናት የአጀቡሽን ባለቤት ሲያሰቃዩት ኖረዋል። የሚታሰርበት ምክንያት “አማራ ነኝ ብለሃል” ተብሎ ነው።  የመጨረሻው እስሩ ግን ለእሱ ሕይወቱን፣ ለባለቤቱ አጀቡሽ ደግሞ ባለቤቷንና ክብሯን ያጣችበት፣  የመጨረሻውን መከራ የተቀበለችበት ነበር።
ገብሬ እስር ቤት ውስጥ እያለ ያሰረው ፖሊስ ይደበድበዋል። ገብሬ ብዙ ደም ፈስሶት ይሞታል። ገብሬን አስሮ፣ ደብድቦ የገደለው ከትግራይ የመጣ ሱራፌል የሚባል ፖሊስ   እስረኛ ገደለ ተብሎ አልተከሰሰም። ዘመነኛ ነው። ጭራሹን ወደ ገብሬ ሚስት ዞረ። ባሏን የገደለባትን አጀቡሽን ደፈራት። አስገድዶ አብራው እንድትሆን አደረገ። ስታረግዝ ደግሞ አባረራት።  መኖርያዋ የሆነው ቃፍቲያ ይህ ጉዳይ ሲሰማ “የባሏ ገዳይ አስረገዛት” መባል እንቅልፍ ሲነሳት  ከሟች ባሏ ገብሬ የወለደችውን አዝላ፣ ከባሏ ገዳይ ሱራፌል ተደፍራ ያረገዘችውን በሆዷ ይዛ ወደአብደራፊ ተሰደደች። የባሏ ገዳይ የሆነው ሱረፌል ያስረገዛትን ልጅ ወልዳ ሁለት ልጆችን ብቻዋን ማሳደግ ጀመረች። የገዳይና የሟች ልጅን ማሳደግ የመሰለን መከራ ተቀበለች። አብደራፊም ሕይወት አልቀናላት ሲል እንደገና ተመለሰች።
የወልቃይት ስቃይና መከራ ይህን ይመስላል። ወልቃይት እንደምድር የሟቾችን፣ የታሳሪዎችን የመከረኞችን ልጆች እና የገዳዮችን፣ የአሳሪዎችን፣ የደፋሪዎችን የጥጋበኞችን ልጅ በአንድ ላይ የምታሳድግ ምድር ነች። የሟቾች፣ የታሳሪዎች፣ የተፈናቃዮች፣……ልጆች በስቃይና በመከራ ያድጋሉ። አፈናቃዮች፣ ደፋሪዎች፣ ገዳዮች፣ አሳሪዎች  እትብታቸው የተቀበረበትን አሳር እያበሉ በጥጋብ ይኖሩባታል።  በቅርብ የመጡ ዘር አጥፊዎች እና  እትብታቸው በተቀበረበት ምድር ዘራቸው እየጠፋባቸው ያሉትን የያዘች ምድር ነች፣ ወልቃይት! ወልቃይት የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማፅዳት  የተፈፀመበት የምድር ሲኦል ሆናለች።
ዛሬ ዛሬ ለሴቶች መብት እንቆማለን የሚሉ ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ነገር ግን  የስማቸውን ያህል  ለተበደሉት ሴቶች ሲቆሙ አይታዩም። እንደነ አጀቡሽ ያሉት ላይ ከሚፈፀመው ይልቅ መሃል ከተማ ላይ የኮረዳና የጎረምሳ ብሽሽቅን “በመብት ጉዳይ” ይዘው የሚንቀሳቀሱ የሚመስሉት ብዙ ናቸው። ከዚህ ባሻገር ጉዳዩ የአማራ ጉዳይ ሲሆን ነውር የሚመስለው ብዙ ነው። ዛሬ ጊዜው ሴቶች ወደፊት የመጡበት ነው እየተባለ ነው። የወልቃይት ሴቶችን መከራ የሚያዳምጥ ግን አልተገኘም። መሪዎቹ በአደባባይ ስለ እናትና ሚስቶች መልካም መልካሙን ሲያወሩ እንሰማለን።  ልጆቻቸውን መቅበር የማይችሉት፣ ባሎቻቸው በእስር ላይ እየማቀቁ ሕይወትን መግፋት ያቃታቸው፣ ባሎቻቸውን በገደሉ ነፍሰ ገዳዮች ተደፍረው የገዳይና የሟችን ልጅ የሚያሳድጉትን የወልቃይት ሴቶች ግን ትኩረት የሚሰጣቸው አልተገኘም። ጩኸታቸውን የሚሰማ፣ እንባቸውን የሚያብስ አልመጣም።
Filed in: Amharic