>
5:50 pm - Monday May 16, 2022

ሰራዊቱን የሚያዘው ጀነራል  ሰዓረ... ወይስ ነብይ እዩ ጩፋ?!? (ሸገር ታይምስ)

ሰራዊቱን የሚያዘው ጀነራል  ሰዓረ ወይስ ነብይ እዩ ጩፋ?!?

ሸገር ታይምስ

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተቋቋመበት አላማ እና በህገመንግስቱ አንቀፅ 87 ከቁጥር 1 እሰከ 5 ከተቀመጡ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የብሄር ብሄረሰቦች እና የህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅኦ ያካተተ ይሆናል፣የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ህገ መንግስት መሰረት በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል ፣ሚኒስትሩ ሲቪል ይሆናል ፣ የመከላከያ ሰራዊት በማንኛውም ግዜ ለህገ መንገስቱ ተገዢ ይሆናል፣እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል ሲል መርሆዎቹን ቆጥሮ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ማለት ሰራዊቱ በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የእምነት ተቋም የውስጥ ጉዳይ እጁን ማስገባት እንደሌለበት የሚገልፅ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ይህ ሰራዊት ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር፣ምንግዜም የተሟላ ስብእና፣ ያልተሸራረፈ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እና በማንኛውም ግዳጅ የላቀ ውጤት በሚሉ እሴቶች የተገነባ እና እነዚህንም እሴቶች ተላብሶ የሚኖር የሀገሪቱ ዋነኛው የደህንነት ክፍል እንደሆነ የሚታመን በመሆኑ ስህተቶችን ስንመለከት ለምን ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡

በአንድ ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ  ከዚህ በታች የተቀመጠው ሃሳብ ሰፍሮ እናገኛለን “ሰራዊቱ በመመሪያና በአሰራር የሚሄድ ይህን ሲያደርግም በአድርግ አታደርግ ስሜት ሳይሆን ኃላፊነት ተሰምቶት የሚፈፅም በሌላ መልኩ ለህግ ተገዢ የሆነ መሆን እንዳለበት ይታመናል ከዚህ በዘለለም በስርአት ውስጥ ሆኖ ተልእኮውን እንዲፈፅም፤ ለህግ ተገዢ የሆነ መሪና ተመሪ እንዲኖር ለማድረግ  እስ ቅርብ ዓመታት ድረስ ቁጥራቸው አስከ ሀምሳ የሚደርሱ  ደንቦች፣ መመሪያዎችና ማንዋሎች ተዘጋጅተው ወደ ሰራዊቱ ተሰራጭተዋል፡፡ እነዚህ ሰነዶች ህገመንግስት፣ አዋጆችና ህዝባዊ ባህሪውን መነሻ አድርገው የተዘጋጁ ቅጣት እና ማስፈራራት ሳይሆን ግንባታን ማዕከል ያደረጉ የሰራዊቱን የመምራትና የመፈጸም ብቃት የሚያሳድጉ ሆነው ከመዘጋጀታቸው በተጨማሪ የሰራዊቱን ዲሞክራሲያዊ ባህሪ  በሚያንጸባርቅ መልኩ ከዝግጅታቸው ጀምሮ ጸድቀው ለህትመት አስኪበቁ ድረስ ሁሉም የሰራዊት አባላት በየደረጃው የተሳተፈባቸውና የኔ ናቸው ብሎ የሚያምንባቸው ሆነው የተዘጋጁና  በመዘጋጀት ላይ ያሉ ሰነዶች ያሉት ሰራዊት በመሆኑም ለየት ያደርገዋል፡፡

ሆኖም በመመሪያና አሰራር ጸንቶ በመሄድ በኩል በሂደት ብቅ ጥልቅ እያሉ የሚታዩ  ችግሮች በተልዕኮው ላይ ሊፈጥረው የሚችለው አሉታዊ ተፅእኖ ቀላል አለመሆኑን ይጠቁማል፡፡

እንዲህ የሚነገርለት እና “ላብ ደምን ያስቀራል” በሚል የእለት ተእለት መሪ ቃሉ የሚታወቀው የመከላከያ ሰራዊት ሰሞነኛ መነጋገሪያ በሆነ አንድ ጉዳይ ላይ አባላቱ ከህግ እና ከተቋሙ አላማ ጋር በሚጣረስ መልኩ እጃቸውን ሲያስገቡ ስንመለከት ይሄ ጉዳይ ምንድነው የሚል ጥያቄን እንድናነሳ አርጎናል፡፡ ጉዳዩ የተፈፀመው በወላይታ ሶዶ ከተማ ሲሆን በርካታ ተከታዮች ባሉት እዩ ጩፋ (ነብይ) በተባለ ግለሰብ ፕሮግራም ላይ የተፈፀመው ድርጊት ከላይ በጠቀስነው ሁኔታ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ህገ ወጥ በሆነ መልኩ እጃቸውን አስገብተው መታየታቸው ነገሩን ትኩረት እንድናደርግበት ጭምር አስገድዶናል፡፡

እዩ ጩፋ (ነብይ) በርካታ ተከታዮች ያሉት ብሎም በቦዲ ጋርድ ጭምር ጥበቃ እየተደረገለት የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ሲሆን ክርስቲያን አርሚየተሰኘ ቤተ እምነት እና በዚሁ ስም የሚጠራ የሃይማኖት የቴሌቭዥን ጣብያን እና የፌስ ቡክ ገፅ ያስተዳድራል ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ሳሪስ አከባቢ በሚገኘው በዚሁ ሰው ቤተ እምነት ደጃፍ ላይ ምስሉን የያዙ ዘይቶች ሲሸጡ ለማየት የቻልን ሲሆን በርካቶች እሱ በሚያገለግልባቸው መድረኮች በመገኘት ተፈወስን፣ ዳንን፣ ተሳካልን፣ ሆነልን በማለት በቴሌቭዥን መስኮት ቀርበው ሲመሰክሩም ለመመልከት ችለናል፡፡

ከእነዚህ ተፈወስን ፣ ዳንን፣ ሆነልን ከሚሉ ግለሰቦች መካከል ደግሞ አቶ መንግስቱ በለጠ ይገኙበታል አቶ መንግስቱ መስከረም 12/2011 ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ እዩ ጩፋ (ነብይ) ፊት ቀርበው በነበሩበት ወቅት የተፈጠረው እና በርካቶችን ያነጋገረው ጉዳይ በዚሁ ጣቢያ ላይ ቀርቦ ታየ፡፡ ሁኔታው ይህን ይመስል ነበር አቶ መንግስቱ ወደ መድረኩ በሰዎች ተይዘው ቀረቡ፡፡ እጁ ላይ ቢላ የያዘው እዩ ጩፋ (ነብይ) መጠየቅ ጀመረ ፡፡

 

እዩ፡- ከየት ነው የተላካችሁት?

መንግስቱ፡- እኛ ሶርያ ነበርን::

እዩ፡- ከሶርያ ነው የተላካችሁት?

መንግስቱ፡- አዎ ከሶርያ አሁን ወደ ኢትዮጵያ መጣን ኢትዮጵያን ልንበጠብጥ መጥተን ከለከልከን እንደ ሶርያ ልንበታትናት…

ጥያቄው አንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥል እና እዩ ጩፋ ( ነብይ ) የያዘው ቢላ አቶ መንግስቱ በአጋንንት ኃይል ተልኮ ሊገድለው እንደመጣ በመተንተን  እኔ የእግዚአብሄር ቀኝ አይን ነኝ፡፡ በማለት እኔን ነካህ ማለት የእግዚአብሄርን ቀኝ አይን ነካህ ማለት ነው የሚል ትርጉም ያለው መልእክት ያስተላልፋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአቶ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት 5 ሚልዮን አጋንንት እንደሆኑ ተገልፆ በእዩ ጩፋ( ነብይ) አማካኝነት በውስጡ የነበሩት አጋንንንቶች እንደወጡለት እና ከእስርም እንደተፈታ ተገልፆ በመድረኩ ላይ 5 ሺህ ብር ለአቶ መንግስቱ ሲሰጠው ያሳያል፡፡ ይህ ቪዲዮ ከተለቀቀ በኋላ በርካቶች በማመን እና ባለማመን ስሜት በማህበራዊ ድረገፆች ሲቀባበሉትም ከረሙ፡፡

ይህ በሆነ በጥቂት ቀናት 5 ሚሊየን አጋንንት አለብህ የተባሉት አቶ መንግስቱ በአስደንጋጭ መረጃ ማህበራዊ ሚዲያውን ተቆጣጠሩት “ስሜ መንግስቱ በለጠ እባላለሁ የትውልድ ሃገሬ ወላይታ ዞን ድቡና ፋንጎ የሚባል ወረዳ ነው” በሚል ንግግራቸውን የጀመሩት ግለሰቡ ፈውሱም ሆነ እኔ ያደረኩት ተግባር ቀድሞ የተጠና እና ገንዘብ ስለተከፈለኝ የተሰራ ድራማ ነው ሲሉ ተፈጠረ ያሉትን እንዲህ ባለ መልክ አስቀመጡ፡፡

“ነብይ እዩ ጩፋ ቤተክርትያን ሻሸመኔ መስከረም 12 በተደረገው ፕሮግራም ላይ 5 ሚሊየን አጋንንት እንደወጣልኝ ተናግሬ ነበር ይላሉ”በመቀጠል ስለ ሁኔታው ሲያስረዱም ሁለት ሰዎች መጥተው አነጋገሩኝ አንደኛው የራሱ የእዩ ጩፋ ወንድም ሳሙኤል ጩፋ ነው ሁለተኛውም እዛው የሚያገለግል በረከት የሚባል ፓስተር ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ይህን ፊልም እንድሰራ በፅሁፍ ሰጡኝ፡፡ በፅሁፍ የቀረበውን አጠናን ይህን ስፈፅም ገንዘብ እንደሚከፈለኝ እና በቦታው ማለትም ፊልሙ የተሰራበት ቀን እስከ 50 ሺ ብር በእጄ እንደሚሰጠኝ በተመልካቹ ፊት ግን 5 ሺ ብር እንደሚሰጠኝ ያንን ከሰራሁ በኋላ እዛ ተቀጥሬ እንደምሰራ ተነግሮኝ ነበር፡፡

መንፈሱ ከሶርያ ይመጣል፣ አረብ ኤምሬትን ያናጋ መንፈስ ነው የሚባለው መንግስትን ለማስቦካት እና ራሱን እንደ ትልቅ ነብይ እንደሆነ እና ለዚህች ሃገር እሱ ትልቅ ነብይ እንደሆነ ሰዎች እንዲረዱት የሚያደርገው ተራ ማጭበርበር ነው፡፡ ህዝቡ እንዴት እንዳልነቃ… አብዛኞቹ ልጆች ምንም አጋንንት ሳይኖርባቸው በኢኮኖሚ የወደቁ በኑሮ እና በድህነት ችግር ምክንያት የተለያየ ሁኔታ ውስጥ የገቡ ሰዎችን ለዚህ አላማ እንደሚጠቀሙ ደሃ የሆኑ ስራ ፣ እጥ የሆኑ ከእስርቤት የወጡ ወንጀለኞችን አደራጅቶ ለዚህ አላማ ያውላል ይላል፡፡ ሲቀጥልም “እነዚህ ሰዎችም የዚህ አላማ ተጠቂ ናቸው፡፡ ነብይ እዩ ሀዋሳ ላይ ስላለ ሃዋሳ ላይ ምንም አይደረግም ያለችው ልጅ ተከፍሏት ይህን ድራማ ከሰራች በኋላ የተወሰነ ጥቅማ ጥቅም ተስጥቷት ዘይት ምናምን እየሸጠች እዛው እያገለገለች ነው፡፡ እቀባችኋለሁ፣ ትፈወሳላችሁ፣ ትፈታላችሁ እያለ አብዛኛው ሰው በሽታውን ተሸክሞ ሄዶ በተለያዩ ሆስፒታሎች ሄዶ እንዳይታከም ተፈውሰሃል ፣የህክምና ማስረጃውን ጣል፣ ቅደድ እየተባሉ ሰዎች እየሞቱ ነው፡፡ እስከዛሬ ፊት ለፊት ወጥቶ እሱን የተቃወመ ሰው ባይኖርም ሰዎች በጥጣሬ እና በሚሰራው ድራማ እውነትም ይሄ እግዚአብሄር የላከው የተቀባ ሰው ነው እየተባለ ብዙ ስጋት ውስጥ እንዳትገቡ እዩ ማለት አጭበርባሪ ፣እልም ያለ ቦዘኔ በህግ መጠየቅ ያለበት ሰው ነው፡፡” በማለት በቪዲዮው ላይ ይናገራል፡፡

ይህን የአቶ መንግስቱን ቨዲዮ ተከትሎ ቀደም ብለን ባነሳነው የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ከክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያን የተሰጠ አስቸኳይ መግለጫ በሚል ርዕስ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ማስተባበያ ቀረበ…

 “መስከረም 12 2011 ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ በክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያን በተደረገው ፕሮግራም መንግስቱ በለጠ የተባለው ግለሰብ የክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያን የማታውቀውን የሀሰት መረጃ  በማህበራዊ ድረገፅ እያሰራጩ በመሆኑ ከዚህ ወንድም ጀርባ ከቤተክርስቲያን በስነምግባር ጉድለት ምክንያት የተገለሉ ሰዎች እጅ ያለበት እና የእግዚአብሄር ሰው ነብይ እዩ ጩፋን ስም የማጥፋት እና የክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያንን መልካም የወንጌል ተሀድሶ እንቅስቃሴን ጥላሸት ለመቀባት ሲሆን ቅዱሳን በዚህ የሀሰት ቃል ምንም ሳይረበሹ እና ሳይደናገጡ ይህን ክፉ ዘመቻ ሊቃወሙ ይገባል ከዚህ ቀደምም የቤተክርስትያኗ ባለ ራዕይ ነብይ እዩ ጩፋ ቅዱሳን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቡ አይዘነጋምና በአንድ ወቅት በታላቅ የወንጌል ተሀድሶ እንቅስቃሴ የነበሩ የእንዲህ አይነት ተግባር ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋምና በወላይታ ሶዶ  ከተማ የሚኖረው ታላቅ መንፈሳዊ ኮንፍረንስ ለማበላሸት በእነዚህ ሰዎች የሀሰት እንቅስቃሴ ባለመገታት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በወላይታ እና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ቅዱሳን ለዚህ ታላቅ የወንጌል ተሀድሶ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡

የክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያንም እነዚህን ግለሰቦች መንገስቱ በለጠን በገንዘብ በመያዝ ይህንን ግለሰብ መስከረም 12/2011 ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ በክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያን በቅዳሜ አገልግሎት ከአጋንንት እስራት ነፃ ከወጣ በኋላ በሳምንቱ በሻሸመኔ ከተማ በቅዳሜ አገልግሎት መስከረም 19/2011 ምስክርነት ለመስጠት ቢገኝም የእግዚአብሄር ሰው ነብይ እዩ ጩፋ በእለቱ ባለመገኘቱ መስከረም 20/2011 አዲስ አበባ በሚገኘው የክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያን በመምጣት ሙሉ ምስክርነቱን የሰጠ ሲሆን ነገር ግን ይህን ግዜ በመጠቀም እነዚህ በስነ ምግባር ጉድለት ከቤተክርስትያን የተቀጡ ግለሰቦች አቶ መንግስቱን በመጠቀም ይህን ስርአት ያልጠበቀና መልካም ያልሆነ ተግባር በመፈፀም የክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያን ከጥቅምት 16 እስከ 18 / 2011 ዓ.ም  በወላይታ ሶዶ ከተማ ያለውን የወንጌል ተሃድሲ ክሩሴድ ለማሰናከል ቢሆንም  ነገር ግን ቤተክርስትያኗ በንቃት እና በሃይል ለማገልገል ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡

የክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያን አቋም፡- አይምሮን ለመልካም ከተጠቀምንበት መልካም ዘር ለክፉ ከተጠቀምንበት ጥፋት እና ውድቀት ነው እና መንፈሳዊ ካልሆኑ ተግባራት በመታቀብ የእግዚአብሄር መልካም ዘር የሆነውን ወንጌል ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል እና  ወንድም እና ወንድምን ከሚያጋጩ ተግባሮች ልንወጣና ለሌሎች በጎ ትምህርት ልንሆን ይገባል፡፡ የክራይስት አርሚ አለም አቀፍ ቤ/ክርስትያንም ይህን እኩይ ተግባር በፍፁም ከተጀመረው የወንጌል ጉዞ የማያቆመውና ግለሰቡን በህግ አግባብ እንደሚጠይቅና ቤተክርስትያናችን እንዲህ አይነቱን በሌሎች ቤ/ክርትያናት ቢኖር እንኳን የምታወግዝና በእግዚአብሄር ዘንድም ኃጥያት እና አሳፋሪ ተግባር እንደሆነ ታምናለች የእግዚአብሄር ሰው ነብይ እዩ ጩፋም በመጨረሻ እግዚአብሄር አምላክ በእሱ የጀመረው የወንጌል እሳት በፍፁም እንደማይቆምና እንደማይገታ ገልፆአል፡፡” ይላል::

 በዚህም ብቻ ሳያበቃ እዩ ጩፋ ( ነብይ) በዩቲዩብ የአቶ መንግስቱን የሚቃወም ሌላ ቪዲዮ ለቋል፡፡ በዚህ ቪዲዮ ላይ አቶ መንግስቱ የተናገሩትን በማጣጣል “ሲጀመር አይምሮው የሚሰራ ሰው አይመስለኝም፡፡” ይላል ሲቀጥልም “18 ማረሚያ ቤት ታስርያለሁ ፣ነፍስ ገድያለሁ፣ ዘራፊ ነኝ በመንፈስ ሶርያ እና አረብ ኤምሬት እሄዳለሁ ያለው ሰውዬ ሲጀመር እብድ ይመስላል እንጂ ጤናማ አይደለም፡፡ እኔ ደግሞ ከፍዬ ሳንጃ ለማስወጣት እና ከፍዬ አጋንንትን ለማስወጣት ምን ጎድሎብኝ ነው? እንደምታውቁት አጋንንት እኔ ጋር ከመጮህ አልፎ እጅ ባነሳ፣ እግር ባነሳ፣ ሂድብል ተንቀጥቅጦ እየሄደ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ስም በኔ ላይ ስለተጠራ እየሱስ የሚለውን ስም ገና ከመጥራቴ ተንቀጥቅጦ ለሚሄደው ከፍዬ ለምን አስጮሃለሁ? ፌስ ቡክ ላይ ስለተወራ መንግስቱ ራሱ ቁጭ ብሎ እግዚአብሄርን የማይፈራ ሰው ስለሆነ ያ የወጣው 5 ሚሊየን አጋንንት ምናልባት 150 ሚሊየን ሆኖ ተመልሶ ገብቷል ብዬ አስባለሁ፡፡

መንግስቱ ሳይሆን ከሱ ጀርባ ከዚህ በፊት ከቸርች የወጡ ሰዎች አሉ ማሳሰቢያውን ነግሬያለሁ እነሱ ሰዎች ገንዘብ ሰርቀዋል፣ ማህተም ይዘው ወጥተዋል የተለያዩ ንብረቶች ይዘው ወጥተዋል” የሚለው እዩ ጩፋ(ነብይ) ከዚህ ቪዲዮ ጀርባ ያሉት እነዛ ሰዎች እንደሆኑ እርግጠኛ ነኝ” ይላል፡፡ “አስከትሎም ቪዲዮው የሚያመጣው ምንም ነገር የለም እንደ ሰው ግን መንግስቱ በለጠን  በህግ አግባብ ተከታትዬ መጠየቄ የሚቀር አይደለም” ብሏል፡፡

ይህን ተከትሎ በሳለፍነው ቅዳሜ ከወደ ወላይታ የተሰማው ሌላ አነጋገሪ ጉዳይ ነበር፡፡  ከላይ በጠቀስነው ክርስቲያን አርሚ ወርልድ ዋይድ በተሰኘው ኦፊሻል የፌስ ቡክ ገፅ ላይ  “መንግስቱ በለጠ በወላይታ ሶዶ በ1 ሚሊየን ህዝብ ፊት ይቅርታ ጠየቀ” በሚል በተለጠፈው ምስል ላይ እዩ ጩፋ (ነብይ) ቀይ መለዮ ባደረገ የመከላከያ ልዩ ሃይል ባልደረባ ሲጠበቅ ይታያል፡፡ ይህን ተከትሎ በማሃበራዊ ድረገፆች ከስፍራው መለቀቅ የጀመሩት ምስሎች ጉዳዩን ትኩረት እንድንሰጠው አደረገን፡፡ በእነዚህ ምስሎች ላይ አንድ የሻንበል ማእረግ ያደረገ እና አንድ ሌላ የልዩ ሃይል ባልደረባ አቶ መንግስቱን ሲያነጋግሯቸው እና አቶ መንግስቱም በተጨነቀ ሁኔታ እጃቸውን አጣምረው የመማፀን ሁኔታ ሲስተዋልባቸው በምስሉ ላይ በግልፅ ይታያል፡፡

ሰኞ እለት ደግሞ አቶ መንግስቱ በወላይታ ሶዶ ከተማ ይቅርታ መጠየቃቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ መሰራጨት ጀመረ፡፡ በዚህ ቪዲዮ ላይ እንደተመለከትነው እና በግልፅ እንደሚታየው እዩ ጩፋ(ነብይ) በመከላከያ ልዩ ሃይል አባላት ከፊት እና ከኋላ ሲጠበቅ የሚታይ ሲሆን ይቅርታ ጠያቂ የተባሉት አቶ መንግስቱም በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡ አሁን ከአዲስ አበባ ነው የመጣሁት የሚሉት አቶ መንግስቱ የተገኙበትን ምክንያት ሲገልፁ በነብዩ ላይ ስሙን ለማጥፋት በተለያየ መንገድ ሲሰሩ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ በጭንቀት ላይ እንዳሉ ማንምበሚገምተው ሁኔታ አንዴ የሚንበረከኩት አንዴ የሚነሱት አቶ መንግስቱ በመቀጠልም በእኔ ላይም የማፈን፣ የመደብደብ ብዙ ነገር ደርሶብኛል ይላሉ፡፡  እዚህ ጋ ደብዳቢው እና አፋኙ አካል ማነው የሚል ጥያቄን ማንሳት ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም እንደተባለው የእዩ ጩፋን(ነብይ) ስም ለማጥፋት የሚፈልግ ሃይል አቶ መንግስቱን በመደብደብ እና በማፈን የሀሰት ወሬ እንዲያሰራጩ አደረገ  የሚለው ብዙም የሚያስኬድ እና ውሃ የማያነሳ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡  ወደ ምስክርነቱ ስንመለስ አቶ መንግስቱ ቀጥለዋል፡፡ “ይሄ የተደረገው እኔ ከአጋንንት መንፈስ ከወጣሁ በኋላ እግዚአብሄር በቅርቡ ሚያጋልጠው ጉዳይ በመሆኑ ሰዎች ስማቸውን ከማልጠራው የተለያዩ ሃይማኖቶች ወስደውኝ የተለያየ ነገር አደረጉኝ፡፡ የእግዚአብሄር ነብይ እኔን ከብዙ ነገር ያወጣ ነው፡፡ ይህንን የሚቃወም ደግሞ ከተለያየ ቦታ እና አቅጣጫ የተነሱ ሰዎች አሉ መፅሄት ላይ ትወጣለህ ተብዬ ፎቶ ላይ ተደርጎ  ስሜን ተጠቅሞ… እኔ የተናገርኩትን እንትን አድርጎ… ይሄንን ተናግረሃል ተብዬ… ይሄንን ለአዲስ አበባ ፖሊስም ለፌደራል ፖሊስም ቃል እንድሰጥ አንዳንድ ነገር ሆኗልና እግዚአብሄርን ሊያገለግል የመጣ የእግዚአብሄር ሰውን ስሙ እኔ የመጣሁትም ለዚህ ምስክርነት ነው፡፡ የሆነው ከኔ ሳይሆን ከተለያዩ ሰዎች ነው፡፡ የተፈጠረው በኔ ስም ቢሆንም እኔ ያላደረኩት ቢሆን በእኔ ስም በመሆኑ አዝኛለሁ” ሲሉ ይታያሉ፡፡

ሀምሳ ሺ ብር ከፍዬህ ነው የጮህከው? ለሚለው የእዩ ጩፋ (ነብይ) ጥያቄ አቶ መንግስቱ ሲመልሱ “አንተ ሀምሳ ሺብር አልሰጠኸኝም አግንቼህም አላውቅም” በማለት ይመልሳሉ፡፡ ወደ ቪዲዮው መጨረሻ ላይ እዩ ጩፋ (ነብይ) ሁሉም ነገር ለእግዚአብሄር ሲል እንደተወው እና እግዚአብሄር ስለ እሱ አንደሚዋጋለት ከገለፀ በኋላ በእኔ በኩል ጨርሻለሁ ከዚህ ቀጥሎ ያለው የህግ ሰዎች ጉዳይ ነው በማለት ሲያጠናቅቅ ከጀርባ ቆሞ የነበረው የመከላከያ ልዩ ኃይል ባልደረባ አቶ መንግስቱን ከመድረክ ይዞት ሲወርድ ይታያል፡፡

በመድረክ ላይ ከቀረበው ከዚህ ቪዲዮ በተጨማሪ የቤተ እምነቱ በሆነው በጠቀስነው የፌስ ቡክ ገፅ ላይ እጅግ ባልተገባ እና ህግን በተፃረረ መልኩ ግለሰቡ በወላይታ ሶዶ ፖሊስ መምሪያ በቁጥጥር ስር ውሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት ባሉበት በሁለትየክልሉ የፖሊስ አመራሮች ሲጠየቅ የሚያሳይ  የቪዲዮ ምስል ተለቆ ለማየት ተችሏል፡፡ አንድ ግለሰብ ክስ ቢቀርብበት እንኳን ፍርድ ቤት የግራና ቀኙን መርምሮ ጥፋተኛ ነህ ብሎ ባልወሰነበት ሁኔታ በእንዲህ አይነት ደረጃ በቪዲዮ እየቀረፁ ስም ያጠፋሁት በሀሰት ነው ብሎ አምኗል ብሎ ነጋሪት መጎሰም ማስፈለጉ ከነገሮች ጀርባ ሌላ የተደበቀ ነገር እንዳለ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው እና ዋንኛው ነገር  ጥፋት ያጠፋን ሰው የመያዝ እና የመመርመር ስራ የፖሊስ ስራ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ልዩ ኃይል ባልደረቦች እንዴት እጃቸውን ሊያስገቡ ቻሉ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

ከስፍራው በደረሰን ጥቆማ አቶ መንግስቱ ቅዳሜ እለት ከመድረኩ እንደወረዱ በወላይታ ሶዶ ፖሊስ መምሪያ ለሁለት ቀናት ታስረው ሰኞ እለት እንደተፈቱ የታወቀ ሲሆን የሰራዊቱ አባላት  ድጋፍ እንዳደረጉ እና አቶ መንግስቱንም በማስፈራራት በእዩ ጩፋ (ነብይ) ላይ የተናገርኩት በሀሰት ነው ብሎ እንዲመሰክር አስገድደውታል ድብደባ እና ዛቻም ተፈፅሞበታል ይላሉ፡፡ ግለሰቡ የሰራዊቱን የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎችን በመጠቀም ያልተገባ ክብር እና ተፈሪነት ለማግኘት እንዲሁም በሰራዊቱ ዘንድ የተለየ ቀረቤታ እንዳለው አድርጎ ይንቀሳቀሳል የሚሉት የመረጃ ምንጮቻችን የፖሊስ ሰራዊት አባላትን በመድረክ ላይ እስከ ደንብ ልብሳቸው እና ማዕረጋቸው አስወጥቶ “የኢየሱስ ወታደርነኝ” እያለ ሲያዘምራቸው የተለቀቀውን ቪዲዮ በማንሳት በሰራዊቱ ላይ የህዝባዊነት ጥያቄ የሚያስነሳም ነው ያነሳሉ፡፡ ግለሰቡ በተጨማሪ በፌስ ቡክ ገፁ እነኚህን መሰል ፎቶዎች በመልቀቅ ግለሰቦች ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል ሲሉም ይከሳሉ፡፡ የተፈፀመው ድርጊት በህገመንግስቱ ላይ በግልፅ የተቀመጠውን መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለውን የህገመንግስት አንቀፅ በግልፅ የሚፃረር ነው የሚሉት  እነኚሁ አስተያየት ሰጪዎች በወላይታ ሶዶ በኢዩ ጩፋ (ነብይ)  አገልግሎት ላይ ለቁጥር የሚታክት መከላከያ ሰራዊትና የዞኑ ፓሊስ ህዝቡን በንስር ዓይን ሲጠብቁ ሲብስም መድረክ ላይ ከጀርባው የሰለጠነ የመንግስት ወታደር አስቁሞ ማየት  የተለመደ ነው ይላሉ፡፡  በመንግስት ደረጃ የተፈቀደም ከሆነ ስለምን እነዚህ ወታደሮች በእምነት መድረክ ላይ ቆመው ሰባኪውን ለመጠበቅ እንደተገደዱ ለህዝቡ መንግስት ማብራሪያ መስጠት አለበት ሲሉም ያሰምሩበታል፡፡

ግለሰቦቹ በጠቆሙን መሰረት ክርስቲያን አርሚ ወርልድ ዋይድ የተሰኘውን ኦፊሻል የፌስ ቡክ ገፃቸውን ለመመልከት የሞከርን ሲሆን (የግል እምነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) በርካታ የሰራዊቱ አባላት እንዲሁም ከፍተኛ የፖሊስ መኮንንኖች ጭምር ከተቋሙ አላማ እና ግዴታ ጋር ፍፁም በሚጣረስ እና ህገወጥ በሆነ ሁኔታ በሙሉ ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለግለሰቡ ወታደራዊ ሰላምታ ሲሰጡት፣ ሲፀልይላቸው እና ከመከላከያ ደንብ እና ስርአት ብሎም የውስጥ ህግ በተቃረነ መልኩ እስከደንብ ልብሳቸው ተንበርክከው የሚታዩበት ምስል በእውቅናቸውም ይሁን ያለ እውቅናቸው በዚሁ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ተለጥፎ የቤተ እምነቱን ፕሮግራሞች ሲያስተዋውቁባቸው ለመመልከት ችለናል፡፡ በሰራዊቱ የውስጥ ህግ መሰረት አንድ የሰራዊት አባል የደንብ ልብስ ለብሶ በየትኛውም ቤተ እምነት መገኘት የማይፈቀድ ሲሆን የደንብ ልብሱን አድርጎ መንበርከክ፣ መጠጥ ቤት መገኘት እንዲሁም የደንብ ልብሱን ለሌላ አላማ መጠቀም ወታደራዊ ዲሲፕሊንን የሚቃረን በመሆኑ ከፍተኛ ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችል ሁሉም የሰራዊት አባል የሚረዳው እና ጠንቅቆ የሚያውቀው ወታደራዊ ስርአት ነው፡፡

በሀገር ደረጃ ትላልቅ መሪዎች ጭምር ፖለቲካ እና ሃይማኖትን ሲቀላቅሉ ያየንባቸው በርካታ ወቅቶች ቢኖሩም ሰራዊቱን እና የተከበረውን የደንብ ልብስ ለተራ የገበያ እና የፕሮፓጋንዳን አላማ እነ እዩ ጩፋ( ነብይ) ሲጠቀሙበት የመከላከያው ክፍል አያውቅም ለማለት ግን ይከብዳል፡፡ ለዚህም ነው ይሄ ሰራዊት የሚታዘዘው በጀነራል ሰዓረ መኮንን ወይስ በነብይ እዩ ጩፋ? የሚለውን ጥያቄ ያነሳነው፡፡ አንድየሰራዊት አባል በህግ ከተቀመጠለት አላማና ተግባር ተቃራኒ በሆነ መንገድ በህግ የተሰጠውን አልባሳት ለብሶ ለአንድ የሃይማኖት ሰው ጥበቃ ለማድረግ ማን ፈቀደለት? የክፍሉ ኃላፊዎችና የቅርብ አመራሮችስ ይህን እያወቁ እንዴት ዝም አሉ? የሰራዊቱ (የፖሊስም ሆነ የመከላከያ) የደንብ ልብስ እና የሰራዊቱ አባላት በእምነቱ ተከታይ ባልሆኑ ሌሎች ማህበረሰቦች ዘንድ እንዴት ይታያሉ? የደንብ ልብሱን የለበሱ አባላትን ፎቶ እያነሱ ለአንድ ቤተ እምነት ማስተዋወቂያነት በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በስፋት ሲሰራጭ ወታደራዊ ደህንነት ክፍሉ እና የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት እና ኢንዶክትሪኔሽን ለምን ዝምታን መረጠ? የሚሉትን ጥያቄዎች እንድናነሳም ያስገድደናል፡፡

የእዩ ጩፋ( ነብይ) ጉዳይ በዚህ ብቻ የሚያልቅ እንዳልሆነ ተስፋዬ ሰሙ ንጉስ  በኔ ላይ የደረሰ ሲል በዩቲዩብ የለቀቀው የተቀዳ የስልክ ንግግር ልውውጥ ይጠቁማል፡፡ በ ዩቱብ  TST APP በሚል እና በርካታ ተከታዮች ባሉት ገፅ ላይ ስለ ተለያዩ አፕሊኬሽኖች እና መረጃዎች በመስጠት በርካታ ተከታይ ያፈራው ተስፋዬ ማወቅ መልካም ነው ያወቁትን ማሳወቅ ደግሞ መልካምነት ነው በሚለው አባባሉ ይታወቃል፡፡ ተስፋዬ ከላይ በጠቀስነው በርካታ ተከታዮች ባሉት የዩቲዩብ ገፁ ላይ ከግለሰቡ ጋር ያደረገውን የስልክ ውይይት ቀድቶ አስቀምጦታል፡፡ በዚህ ውይይታቸው ላይ እዩ ጩፋ (ነብይ) ከውጭ የሚላክ ገንዘብ ከዚህ ቀደም በህገወጥ መልኩ በጥቁር ገበያ 60 ሺ ዶላር እንደተላከለት ሲገልፅ ይደመጣል፡፡ የእዩ ጩፋ (ነብይ) ድምፅ እንደሆነ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ በሆንበት በዚህ የስልክ ውይይት ላይ አቶ ተስፋዬ ገንዘቡን በጥቁር ገበያ እንዲልኩለት ሲያግባባ የሚደመጠው ግለሰቡ መላክ የሚፈልገውን ገንዘብ እዛ ላሉ ሰዎች እንዲሰጥ እና እዚህ ያለ ሰው በህገወጥ መንገድ ምንዛሪውን ወደ እሱ አካውንት እንዲያስገባ ይጠይቀዋል፡፡ ይሄ ብላክ ማርኬት ችግር አያመጣም ወይ? ተብሎ ከተስፋዬ የተጠየቀው እዩ ጩፋ( ነብይ) ይህን ሲል ይደመጣል፡፡ “ምንም ችግር አያመጣም፡፡ ምንም የሚያመጣው ነገር የለም ምክንያቱም እነሱ ለራሳቸው ይፈልጋሉ እኛም ስለምንፈልግ ምንም የሚፈጥረው ነገር የለም አሁን ባንክ ላይ 27 ብር ነው ብላክ ላይ ደግሞ 31 ብር ነው በ1 ዶላር የአራት ብር ልዩነት ነው ያለው ያ ደግሞ በ120 ሺ ዶላር ስታበዛው በ100 ሺዎች የሚቆጠር ልዩነት ነው” በማለት ሲያስረዳ ይሰማል፡፡ ተስፋዬ ይህን ንግግር ያደረገው እና የቀረፀው ግለሰቡ ላይ እንዲህ አይነት ክሶች ሲቀርቡበት በመስማቱ ለማጣራት እንደሆነ ያብራራ ሲሆን ለቤተክርስትያኗ ድጋፍ የሚሆን 120 ሺ ዶላር እንደሚሰጥ ሰው ሆኖ እንዳነጋገረም ይገልፃል፡፡

ይህን ቪዲዮ በማህበራዊ ድረገፅ ካሰራጨ በኋላ ድምፁን በመቀየር በድጋሚ ቪዲዮው ተለቆ እንዳየው እና እንዳዘነ የህግ ባለሙያ በመሆኑ ሊያግዘው እንደሚፈልግ ብሎም ከ15 ቀን በኋላ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመጣ ለእዩ ጩፋ (ነብይ) ሲነግረው ቪዲዮውን እንዲልክለት እና ሲመጣ እንደሚያገኘውም ሲናገር የሚሰማበትን ድምፅ ይፋ አድርጎታል፡፡ እዩ ጩፋ (ነብይ)ከፖሊስ እና የፀጥታ ሰዎች ጋር እንደመቅረቡ ህግን መስበክ እና ማክበር ሲገባው በህገወጥ መንገድ ገንዘብ እስከማስተላለፍ መድረሱ ትክክል እንዳልሆነም ተስፋዬ በቪዲዮው ይወቅሳል፡፡

ተስፋዬ ስለ ግለሰቡ ተጨማሪ የድምፅ መረጃዎች እንዳሉት እና በቅርቡም ሙሉውን ይፋ እንደሚያደርገውም በማህበራዊ ሚዲያ ገልፆአል፡፡ በተነሱት ጉዳዮች ላይ እዩጩፋ(ነብይ) ያላቸውን ምላሽ ለማግኘት በተለያዩ ሶስት የስልክ ቁጥሮቻቸው ላይ ብንደውልም ሊሰራልን ባለመቻሉ በፅሁፍ መልእክት የላክን ሲሆን ለህትመት እስከገባንበት ቀን ድረስ ግን ምላሻቸውን አላገኘንም፡፡ በተጨማሪም ለዚህ ዘገባ መነሻ የሆኑት የአቶ መንግስቱም ስልክ ዝግ በመሆኑ ምክንያት ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

በጉዳዩ ላይ ከህግ አንፃር የሚታዩትን ጉዳዮች ለህጉ ሰዎች ትተን ከሰራዊቱ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ያነሳናቸውን እና የደረሱን መረጃዎችን በተመለከተ ሸገር ታይምስ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው ክፍል ጋር ውይይት ያደረገች ሲሆን በቀጣዩ እትማችን የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት እና ኢንዶክትሪኔሽን ኃላፊ የሆኑትን ሜ/ጄ መሀመድ ተሰማን አነጋግረን ምላሻቸውን እንዲሁም ተጨማሪ እየደረሱን ያሉ መረጃዎችን ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን፡፡

Filed in: Amharic