>
2:19 am - Saturday December 10, 2022

ለኃ/ማሪያም ደሳለኝና ለመሩት መንግስት አዘንኩላቸው፡- መለስ ዜናዊስ  አንዴ ሞቷል!!! (ቹቹ አለባቸው)

ለኃ/ማሪያም ደሳለኝና ለመሩት መንግስት አዘንኩላቸው፡- መለስ ዜናዊስ  አንዴ ሞቷል!!!
ቹቹ አለባቸው
የዛሬውን የአቃቢ ህግ-መግለጫ ሲሰሙ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ምን ተሰማቸው ይሆን? ስለዛሬው ወንጀል፤  በየመድረኩ ሲነሳ፤አባላትን ሲቀጠቅጡ የከረሙት፤ የኦዴፓ፤ ደኢህዴንና የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮችስ ምን ተሰማቸው ይሆን? ትምክህትና ጠባብነት አገሪቱን ሊያፈርሷት እንጀ፤አድሏዊ አሰረራ ለም፤ሰብአዊ መብት ጥሰት በአገራችን አልተከሰተም ወዘተ… ሲሉ የከረሙት እነ ነውር ጌጡስ፤የዛሬውን ጉድ ሲሰሙ ምን ተሰማቸው ይሆን ? ለነገሩ ምን አስቸኮለኝ፤ ዛሬ፤ነገ ወይም ከነገ ወዲያ በመግለጫቸው ያስሙን የለ፡፡ ለሁም ስለነዚህ ሁሉም አካላት፤ ስለነሱ እኔን ጨነቀኝ፤ እነሱን ሳስባቸው አዘንኩላቸው፡፡
ለሁሉም የዛሬው  የአቃቢ ህግ መግለጫ ውብና ታማኝነት ያለው ነበር፡፡ መግለጫውን የሰጡት ባለስልጣንም፤ ከጌታቸው አምባየ ጋር ሳወዳድራቸው የሰማይና መሬት ያክል ሆኑብኝ፡፡ ነገር ለመሸፋፈን ብዙም አልፈለጉም፤ የነበረውንና ያለውን  እውነታ በአጥጋቢ ሁኔታ የነገሩን መሰለኝ፡፡ ለሁሉም ዛሬ የተነገረው መርዶ፤በመንግስት በይፋ መነገሩ ካልሆነ በስተቀር፤የአገራችን ህዝቦች፤ላለፉት 27 አመታት ሲጮሁበት የነበረ ድርጊት ነው፤ ሆኖም ግን የመለስ ዜናዊና የኃ/ማሪያም ደሳለኝ መንግስት፤ በህዝቡ ጩከትና ጥያቄ  ሲያላግጡበት ኖሩ፡፡ የመለስን ነገር ልለፈው፤ ባህላችን ሙት ወቃሽነትን ይከለክላልና፡፡
ዛሬ የሰማናቸው ከባድና ለመስማት የሚያስቸግሩ ወንጀሎች፤ መፈጸም የጀመሩት፤ከ27 አመታት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፤ ስፋትና ጥልቀት እያገኙ የመጡት ግን፤የ1977 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ከዚህ ጊዜ በኃላ፤ መለስ ዜናዊ ሁሉንም ነገሮች በኃይልና በጉልበት የመፍታ አባዜ ተላበሰ፡፡ ፈጣሪ መለስን ተመስሎ፤በአገራችን ላይ የሚደርሰውን  ግፍ  ያስቀረ መስሎት፤ ሰውየውን ከብዙ መከራ በኃላ ቢሆንም፤ከመንበሩ አነሳው፡፡ነገር ግን ባለተራው ሰውየ፤ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ተተካብን፡፡
አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ፤ በሟቹ ጠሚ  አቶ መለስ ዜናዊ  መተካቱን ይፋ ለማድረግ በተጠራው  የመጀመሪያው የፓርላማ ስብሰባ ላይ፤ የመጀመሪያውን  የፓርላማ  ንግር ባደረገበት ወቅት ፤ የእኔ ዋነኛ እቅድ ” የታላቁን  መሪያችንን፤ የመለስ ዜናዊን ሌጋሲ ማስቀጠል ነው” አለን፡፡ አወ፤ አቶ  ኃ/ማሪያም ደሳለኝ፤ የመለስ ዜናዊን የማሰር፤ መግደል፤የማኮላሸት፤ የማሰቃት፤ወዘተ…. ሌጋሲውን ቢያንስ ለ6 አመታት አስቀጠለለት፡፡ በእኔ ግምት፤የኢትዮጵያ ህዝቦች፤በከፋ መልኩ ዛሬ ለሰማነው አይነት የከፋ ጥቃት የተጋለጡት፤በ አቶ ኃ/ማሪያም  ደሳለኝ የስልጣን ዘመን ነው፡፡ ይህ ሰውየ ስልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት፤ህወሀትና ጌታቸው አሰፋ፤ አገሪቱን ሙሉ በሙሉ በመዳፋቸው ስር በማስገባት፤ የወደዱትን ወገን ሲተቅሙ፤ ስልጣናቸውን የሚገዳደር መስሎ ታያቸውን ሲገድሉና ሲያጠፉት፤የጠሉትን ሲያርቁት፤ እንዲሁም  በታሪካዊ ጠላትነት የፈረጁትን፤ በተለይም አማራን  ደግሞ ክፉኛ ሲበድሉት የኖሩባቸው አመታት ነበሩ፡፡ ህወሀትና ጌታቸው አስፋ ይሄንን እንዲያደርጉ እድል የሰጣቸው ደግሞ አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ነው፡፡ሰውየው የሚቀርብላቸውን ህዝባዊ ቅሬታ አዳምጠው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፤ከህወሀትና ጌታቸው አስፋ የሚቀርብላቸውን ሪፖርት ብቻ እያዳመጡ፤ሲያስጨርሱን ከረሙ፡፡
—-
ብቻ በዛሬው እለት፤ሁሉም ነገር ግልጥልጥ ብሏል፡፡ይህ ሁሉ ወንጀል የተፈጸመው፤ በኃ/ማሪያም የስልጣን ዘመን ነው(መለስን እርሱት)፡፡ ስለዚህ ዛሬ ለሰማነው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል ተጠያቂው ማን ነው? በሚለው ጭብጥ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመክር ይገባል፡፡ በእኔ እምነት፤ ዛሬ ለሰማናቸው አስደንጋጭ ወንጀሎች፤ ተጠያቂዎቹ፤ ኢህአዴግ (በተለይ የስራ አስፈጻሚው ክፍል) እና መንግስቱን በበላይነት ሲመሩ የነበሩ አካላት (በተለይም አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ናቸው)፡፡ እነዚህን አካላት፤ከተጠያቂነት ነጻ አድርጎ፤ወደ ታች ያሉትን አካት ብቻ ለመጠየቅ መሞከር፤ትግሉን ሙሉ አያደርገውም፤በትምህርት ሰጭነቱም ጎደሎ ይሆብናል፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ የዶ/ር አብይ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው፡፡ አንዳንዴ ለብቻ አስብና ፤ ኦዴፓ ዶ/ር አብይንና ኦቦ ለማን የመሳሰሉ ዘመኑ ሰዎች ባይሰጠን ኖሮ፤እንዲህ የህወሀትን ገመና፤ዘረጋግፎ የሚያሳየን ሌላ ኃይል ከየትኛው የኢህአዴግ አባል ድርጅት ይገኝ ነበር? ስል ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ከህወሀት፤ከአዴፓ፤ከደኢዴን?  አይመስለኝም፡፡ ብቻ አገራችን ተባቂዋ ከላይ ስለሆነ ሰው ሰጣት፡፡ ነገር ግን አሁን የምናው ቁርጠኝነት፤በቂ አይደለም ባይ ነኝ፡፡ ይህ የዶ/ር አብይ ቁርጠኝነት፤ ኢህአዴግና መሪዎቹንም በመፈተሸ ጭምር መረጋገጥ አለበት፡፡ አገር እንዲህ እንዲጠፋ ሁኔታዎችን ሲያመቻች የከረመው ኢህአዴግንና መሪው የነበረውን አቶ ኃ/ማሪያምን አለመንካትና በለሆሳስ ማለፉ እጅግ ስህተት ይሆናል፡፡
—-
የአገራችን ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ቢፈቅድ ኖሮ እኮ፤ በዛሬው ሪፖርት ላይ ብቻ ተመስርቶ፤ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ስልጣን መልቀቅ ነበረበት፤ እንዲሁም ዋና ዋና ባለስልጣናቱ፤ በተለይ እንደ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ያሉት ወፍራራም ባለስልጣናት ደግሞ፤ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት ወንጀል ተከሰው ፍ/ቤት መቅረብ ነበረባቸው እላለሁ፡፡ ግን-ግን ኢህአዴግ ሆን ብሎ ተኪ ሀይል እንዳይኖረው እየሰራ ስለመጣ፤ ለጊዜው ከስልጣን የመልቀቅ መከራው አልፎታል፡፡ አቶ ኃ/ማሪያምና መሰሎቹ ግን ተኪ ስላገኙ፤ ለዚህ ሁሉ ወንጀል የድርሻቸውን ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው፤ያለ በለዝያ ትግሉን ሙሉ አያደርገውም፡፡
Filed in: Amharic