>

እነዚህ ዘራፊዎችና ጨካኞች የትግራይ ህዝብን ይጠቀሙበታል እንጂ አይጠቅሙትም!!  (ስዩም ተሾመ)

እነዚህ ዘራፊዎችና ጨካኞች የትግራይ ህዝብን ይጠቀሙበታል እንጂ አይጠቅሙትም!! 
ስዩም ተሾመ
በተደጋጋሚ “ህወሓት የሀገርና ህዝብ ነቀርሳ የሆነ የዘራፊዎችና ጨካኞች ድርጅት ነው” እያልኩ ስናገርና ስፅፍ አንዳንድ የህወሓት ቡችሎች “የትግራይን ህዝብ ትጠላለህ!” እያሉ በዘረኝነት ይከስሱኛል። በእርግጥ ቅጥ-ያጣ ዘረፋ የሚፈፅሙ እና በጭፍን ጥላቻና ዘረኝነት የታወሩ ሰዎች ሌሎችን በራሳቸው፥ በሆኑት ልክ ቢመለከቱ አይፈረድባቸውም። እውነታው ግን እነዚህ ሰዎች የትግራይን ህዝብ የሚፈልጉት ለራሳቸው ለመዝረፍና ሌሎችን ለመጨቆን ብቻ ነው።
ሌባ ልጅ በዘረፈው ገንዘብ እናትና አባቱን አይጦርም፣ ወንድምና እህቱን አይደግፍም። በተመሳሳይ እነ ጄ/ል ክንፈ ዳኘው ከኢትዮጵያ ህዝብ በዘረፉት ገንዘብ ለትግራይ ህዝብ የሚጠቅም አንዳች ነገር አይሰሩም። በመሰረቱ ያለ አግባብ የመጣ ገንዘብ የሚወጣው በመጣበት መንገድ ነው። በመሆኑም እነዚህ ሌቦች የዘረፉትን ገንዘብ የሚያጠፉት በአጉል ቅንጦትና ቅብጠት ነው። ከእነሱ የቁስና የስሜት ሴሰኝነት ተርፎ ለትግራይ ህዝብ ጠቃሚ ነገር ለመስራት የሚውል ገንዘብ አይኖርም።
እንደ አቶ ጌታቸው አሰፋ ያሉ ጨካኝ ሰወች በመስቀል አደባባይ ህዝብን በቦንብ ለመፍጀት ሴራ የሚጠነስሱት ለትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ብለው አይደለም። ከዚያ ይልቅ የሀገሪቱን ህዝብ በፍርሃት ቆፈን በማስያዝ በተለመደ ዘረፋቸውን ለማስቀጠል ነው። እነዚህ ዘራፊዎችና ጨካኞች አዲስ አበባ ላይ ሲሸነፉ መቐለ ላይ ሄደው የመሸጉበት ምክንያት ላለፉት 27 አመታት በሀገሪቱ ላይ የሰሩትን ግፍና በደል ስለሚያውቁ እና ከዚያ ውጪ ሌላ መሸሺያና መሸሸጊያ ስለሌላቸው ነው።
የፌዴራል ዋና አቃቤ ህግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ መሰረት፣ እነዚህ እንደ ጠላት ሀገርን የዘረፉ ሌባዎችን ማስጠጋት በተጋሩዎች ቤት የሙት መንፈስ እንዲገባ መፍቀድ ነው። ሰይጣን እንኳን የማያስበውን በጭካኔ የተሞላ አሰቃቂ ተግባር በፈፀሙ ሰዎች መፈለግ በራሱ በአስክሬን እንደ መሳም ይቀፍፋል።
አሁን ደርሶ “ዘራፍ” የሚሉት አንዳንድ የትግራይ ልሂቃን የዘራፊዎቹና ጨካኞቹን ፍርፋሪ ሲቃርሙ የነበሩና ወደ ሌላ ሀገር ሸሽተው ጥጋቸውን የያዙ ድኩማኖች ናቸው። ከዚያ በተረፈ ሀገርን ሲዘርፉና በሰዎች ላይ በጭካኔ የተሞላ ተግባር ሲፈፅሙ የነበሩ ጄኔራሎችና የደህንነት ሰዎች የትግራይ ህዝብን እንደ ልማዳቸው ሊዘርፉትና ከሌሎች ኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ግጭት ውስጥ በማስገባት እልቂት ሊደግሱለት እንጂ ለሌላ አይደለም። በአጠቃላይ እነዚህ ዘራፊዎችና ጨካኞች የትግራይ ህዝብን ይጠቀሙበታል እንጂ አይጠቅሙትም!!
Filed in: Amharic