>

የህወሀት ሹማምንቶችን ከየተደበቁበት ማንቁርታቸውን ለመያዝ የጀመሩት ዘመቻ ልብ ያሞቃል!!! (መሳይ መኮንን)

የህወሀት ሹማምንቶችን ከየተደበቁበት ማንቁርታቸውን ለመያዝ የጀመሩት ዘመቻ ልብ ያሞቃል!!!
መሳይ መኮንን
 
* አዎን! ኢትዮጵያ በቁሟ ተዘርፋለች፣ ተግጣለች ሜቴክ ደምና ስጋዋን ጨርሶ በአጥንቷ አስቀርቷታል!!!
 
* አዎን! ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የሲዖል ምድር ሆና ቆይታለች። ተደፍረዋል። ተቀጥቅጠዋል። ተኮላሽተዋል። ተገድለዋል!!!
ነገሮች ፍጥነታቸው አስደማሚ ሆኗል። አይናችንን በተከፈተ ቁጥር የምንሰማው የምናየው ተአምር እየሆነብን ነው። በዚህ ፍጥነት ህወሀት ፍርስርሱ ወጥቶ ለጥፋት ያሰማራቸውን ተኩላዎቹን ወደበረታቸው መሰብሰብ እስኪያቅተው ይደርሳል ብዬ አልጠበኩም። ዋናዎቹ አሳዎች የተደበቁበት ምሽግ መናዱ አይቀርም። አሁን እንደሰማነው የስኳሩ ንጉስ አባይ ጸሀዬ፡ የሜቴኩ ባላባት ብ/ጄ ክንፈ ዳኘው እና የሳይበሩ ጠላፊ ሜ/ጄ ተክለብርሃን ወልደአረጋይ የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል። ቀደም ሲል ማዘዣ ተቆርጦበት ከመቀሌ መውጣት ሳይችል ከአክሱም ሆቴል የተደበቀው ጌታቸው አሰፋ ቁጥር አንድ ተፈላጊ ሆኗል።
የኢሳትን የ8ዓመታት ጩሀት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጋዜጣዊ መግለጪያ አጠቃለው ነገሩን። በመጨረሻም የእኛን ጩሀት ያስተጋባውን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት መልካም ጅምር ብዬ አወድሼዋለሁ። አቶ ብርሃኑ እሳቸውም በአንድ ወቅት የፍትህ ቢሮ ባለስልጣን በነበሩ ጊዜ ሲያስተባብሉት የነበረውን ግፍ ዛሬ በራሳቸው አንደበት መመስከራቸው ሃጢያታቸውን በአደባባይ ያጠቡበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል።
አዎን! ኢትዮጵያ በቁሟ ተዘርፋለች። ተግጣለች። ሜቴክ ደምና ስጋዋን ጨርሶ በአጥንቷ አስቀርቷታል።
አዎን! ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የሲዖል ምድር ሆና ቆይታለች። ተደፍረዋል። ተቀጥቅጠዋል። ተኮላሽተዋል። ተገድለዋል።
የአቶ ብርሃኑ መግለጫያ በአጭሩ ከተገለጸ ከዚህ አያልፍም።
መቼም አጃኢብ ነው። ባለፉት ሶስት ቀናት የሆነው ያልተጠበቀ ነበር። በመከላከያና ደህንነት ውስጥ እየተወሰደ ያለው የመጥረግና የማጽዳት ስራ ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመውሰድ ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ዶ/ር አብይ ቃላቸውን የሚጠብቁ እንደሆኑ እያስመሰከሩ ነው። የማይደፈር፡ የማይነካ የሚመስለውን የህወሀትን ቅጥር ሰባብረው እነዚያን ለሰማይ ገዝፈው የተቆለሉ የህወሀት ሹማምንቶችን ከየተደበቁበት ማንቁርታቸውን ለመያዝ የጀመሩት ዘመቻ ልብ ያሞቃል፡ ተስፋ ይሰጣል።
ይህ እርምጃ ከማንም በላይ ለትግራይ ህዝብ እፎይታን የሚሰጥ ነው። አንዳንድ የትግራይ አክቲቪስቶችና ልሂቃን እያደነቆሩን እንዳለው የጠ/ሚር አብይ እርምጃ የትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። አንድ ያነጋገርኳቸው የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ይህ የሰሞኑ እርምጃ ለትግራይ ህዝብ ትንሳዔን ይዞ የሚመጣ ነው ብለውኛል። እነዚህ ወደ ከርቸሌ የገቡና እንዲገቡ ማዘዢያ የተቆረጠባቸው የህወሀት ሹማምንት ከማንም በላይ መከራና ፍዳ ያመጡት ለትግራይ ህዝብ ነው። በእነሱ ዳፋ የትግራይ ህዝብ ዋጋ ሊከፍል አይገባም። እንደአልቅት ጀርባው ላይ ተሰክተውና ተጣብቀው ደሙን ሲመጡ የከረሙት ህወሀቶች ለፍርድ ሲቀርቡ መቀሌ መደነስ፡ አክሱም መጨፈር፡ አዲግራት አጆሀ ማለት እንጂ ስጋት ሊገባቸው አይገባም።
የኢንሳው ምክትል ቢኒያም ተወልደ ከርቸሌ ገብቷል። አለቃው በቅርቡ ይቀላቀለዋል። የሜቴክ ግሪሳዎች ተለቅመው እስር ቤት ናቸው። አዛዣቸው ክንፈን እንኳን ደህና መጥህ ብለው የሻማ ተቀብለው ያስተናግዱታል። አቶ አባይ ጸሀዬ 77 ቢሊየን ብር የት እንዳቀለጡት እጆቻቸው በሰንሰለት ታስሮ ከልደታ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ ቃላቸውን የሚሰጡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። በረከት ስምዖን እንደቢንቢ ጆሮ ላይ የሚጮሁ ቃላቱን የምናይበት ሶስተኛው መጽሀፉ ”የከርቸሌው በረከት” በሚል እንደሚያስነብበን አልጠራጠርም። ሁሉም በሰፈረው ቁና ይሰፈር ዘንድ ጊዜው እነሆ ቀርቧል!!
Filed in: Amharic