>

በጠራራ ፀሐይ አገር  ሲዘረፍ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

በጠራራ ፀሐይ አገር  ሲዘረፍ!!!
አቻምየለህ ታምሩ
 
* ለትውስታ የተደገመ
 
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በወርሀ ጥር የወያኔ ካድሬዎችና  የአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ  ተቋማት የሆኑት እነ ኤ.ቢ.ሲ.፣ ዋልታ፣ ፋና፣ ኤ.ዜ.አ. ወዘተ ትግራይ በታሪኳ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበችው  ስላሉት የወርቅ ምርት መጠን በስፋት ዘግበው ነበር። የአገዛዙ ልሳን ኢ.ቢ.ሲ. እ.አ.አ. ጥር 07 ቀን 2016 ዓ.ም. ባቀረበው ርዕሰ አንቀጽ፤ ዋልታ እ.አ.አ. ጥር 09 ቀን 2016 ዓ.ም. ባስደመጠም የዜና እወጃ ፤ ኤ.ዚ.አ. ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ባስነበበን ሪፖርት ትግራይ  እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ 597.7 ቶን ወርቅ  [በባህላዊ መንገድ] እንዳመረተችና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳቀረበች ነግረውናል።
ይህንን  «ልማታዊ ዜና»  የሰሙ ብዙ ሰዎች «ትግራይ ከየት አምጥታ ነው ይህንን ያህል ወርቅ አምርታ ለብሔራዊ ባንክ የምታቀርበው?» በማለት ከቁጥሩ ጀርባ ያለውን የምጣኔ ሀብት ትርጉም ሳያጤኑ አጣጥለውት አልፈዋል።  ሆኖም ግን ከቁጥሩ ጀርባ ወያኔ  ትልቅ አገራዊ ዘረፋና ወንጀል  ፈጽሟል። ወያኔ በቁጥሩ ቁማር  ተጫውቶ የኢትዮጵያን የሁለት አመት ባጀት ያህል ብሔራዊ  ሃብት በአንድ ግብይት ብቻ  ወደ ትግራይ አሸሽቷል ወይንም አሻግሯል። ነገሩ እንዲህ ነው።
ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ 597.7 ቶን ወርቅ ከትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀረበ ማለት በ42 ወር ውስጥ 597.7 ቶን  ወርቅ ከትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ቀረበ ማለት ነው። ይህ ማለት ትግራይ በአመት በአማካኝ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባ ነበር ማለት ነው። በኢትዮጵያ የንግድ ህግ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብቸኛው ወርቅ ገዢና አስቀማጭ ተቋም ነው። ክልሎች በየክልሉ የተመረተውን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ሲያቀርቡ ብሔራዊ ባንክ ክልሎች ላቀረቡት የወርቅ መጠን ክፍያ ይፈጽማል። ለምሳሌ ትግራይ 597.7 ቶን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስታቀርብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለትግራይ ክልል የ597.7 ቶን  ወርቅ ክፍያ በገንዘብ ይፈጽማል። ያልቀረበ ወርቅ ሪፖርት ተደርጎ  ብሔራዊ ባንክ ላልቀረበ ወርቅ እንደቀረበ ተደርጎ  ክፍያ ቢፈጽም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሀብት transfter ይኖራል ማለት ነው።
ወያኔ የነገረን ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበችው  597.7 ቶን  ወርቅ ማለት 597,700 ኪሎ ግራም ወርቅ ማለት ነው።ይህ ማለት ደግሞ  19,216,473 ወቄት ወርቅ ማለት ነው።  ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት አመታት ውስጥ  አማካኝ የአንድ ወቄት ወርቅ ዋጋ 1,100 የአሜሪካን ዶላር ነበር። ይህ ማለት ትግራይ አቀረበችው የተባለው 597.7 ቶን ወርቅ ዋጋ 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል ማለት ነው።
ይህ ማለት  [በወያኔ ዜና መሰረት] ትግራይ  ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላቀረበችው  597.7 ቶን ወርቅ  ብሔራዊ ባንክ 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍሏታል ማለት ነው። የኢትዮጵያ  ያለፈው አመት ባጀት አስር ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ማለት  ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቀረበችው  ለተባለው  597.7 ቶን ወርቅ የተከፈላት 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ የሁለት አመት በጀት በላይ ነው ማለት ነው።
ዋናውና ቁልፉ ጥያቄ እውነት ትግራይ   ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 597.7 ቶን  ወርቅ ወይንም ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም.  በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ አቅርባለች ወይ?  የሚለው ነው።
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የአለም አገሮችን የወርቅና የሌሎች ማዕድናትን አመታዊ ምርት ማስረጃ  የሚሰበስበውንና  የሚያደራጀውን የUnited States Geological Survey (USGS) Minerals Resources Program አመታዊ  የአለም ማዕድናት ምርት  ሰንጠረዥን ማየት በቂ ነው። ይህ የአሜሪካ ተቋም በአለም ላይ ያሉ ማዕድን አምራች አገሮችን የማእድን አመታዊ ምርት አሃዝ ሰብስቦ ደረጃ ያወጣና የአለም አገሮችን በማዕድን ምርት ያወዳድራል። በዚህ መስሪያ ቤት ማስረጃ መሰረት ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ  በአለም ላይ በወርቅ ምርት አንደኛ ቻይና ስትሆን አመታዊ የወርቅ ምርት መጠኗ  403 ቶን ነው። ሁለተኛዋ የአለም ወርቅ አምራች አገር ደግሞ  አውስትራሊያ  ስትሆን አመታዊ የምርት መጠኗ  ደግሞ 250 ቶን ወርቅ  ነው።  ሶስተኛ አሜሪካ [235 ቶን ወርቅ በአመት] ፤አራተኛ ሩስያ ፌድሬሽን [217.8 ቶን ወርቅ  በአመት] ፤ አምስተኛ ፔሩ  [161 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ስድስተኛ ደቡብ አፍሪካ [160  ቶን  ወርቅ በአመት]፤ ሰባተኛ ካናዳ  [103 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ ስምንተኛ ሜክሲኮ  [96.7 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ ዘጠነኛ ኡዝቤኪስታን [ 93 ቶን ወርቅ በአመት] እና ጋና  [86.5 ቶን ወርቅ በአመት] በአለም ላይ አስሩ ከፍተኛ ወርቅ አምራች አገሮች ናቸው። የዚህ ምንጭ የሚከተለውን ትር መክፈትና መመልከት ይቻላል… http://www.indexmundi.com/minerals/?product=gold&graph=production
ወያኔ ኢትዮጵያ ትግራይ ብቻ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ  በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ  አቅርባለች ያለው እውነት ቢሆን ኖሮ  ኢትዮጵያ በወርቅ ምርት በአለም ደረጃ ፔሩን ቀድማ  ሩስያን ተከትላ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትሆን ነበር። ልብ በሉ ከአንድ እስከ አስር የወጡ  አገሮች ሁሉ ወርቅ የሚቆፍሩት በጣም ዘመናዊ በሆነ መሰርሰሪያ ማሽን ነው። ወያኔ  ግን ትግራይ በየ አመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባለች  የሚለን በባህላዊ መንገድ አምርታ ነው።
ከፍ ብዬ በለጠፍሁት የUnited States Geological Survey (USGS) Minerals Resources Program  አመታዊ የወርቅ ምርት  እውነተኛ ደረጃ መሰረት የኢትዮጵያ አመታዊ የወርቅ አምራችነት ደረጃ 29ኛ ሲሆን አመታዊ  የወርቅ ምርቷ ደግሞ 12 ቶን ብቻ ነው። ልብ በሉ ይሄ አመታዊ የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ዶዶላ፣ መተከል፣ ለገደንቢና ወለጋ ሜድሮክ በዘመናዊ ቴክኖሎች ታግዞ የሚያመርተውን ይጨምራል።  ወያኔ ግን የትግራይን አመታዊ ምርት ብቻ 171 ቶን  ነው ይለናል።
ሜድሮክ በዶዶላ፣ በመተከል፣ በለገደንቢና በወለጋ  የሚያመርታቸውን ዜሮ አድርገን ኢትዮጵያ ያመረተችውን 12ቱን ቶን ወርቅ ከትግራይ ብቻ  ለብሔራዊ ባንክ  የቀረበ የወርቅ መጠን አድርገን ብንወስድ፤ ብሔራዊ ባንክ ከትግራይ  በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ እንደቀረበለት ተደርጎ ለትግራይ በጠቅላላ  ከከፈለው 21.3 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ውስጥ በያመቱ ላልቀረበ  158 ቶን ወርቅ ክፍያ ፈጽሟል። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትግራይ ቀረበ ተብሎ  ከፍያ ከፈጸመበት 597.7  ቶን ወርቅ ውስጥ ባንኩ የተረከበው ወርቅ 42 ቶብ ብቻ ነው። የተቀረው 555.7 ቶን ወርቅ ወርቁ ከትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሳይቀርብ  ብሄራዊ ባንክ ግን ከትግራይ  ወርቅ ሳይቀርብ ክፍያ  እንዲፈጽም የተደረገበትና  የአገር ሀብት ዘረፋ የተካሄደበት የውሸት ቁጥር  ነው።
ይህ ማለት ብሔራዊ ባንክ ለትግራይ ከከፈለው 21.3 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ከ20  ቢሊዮን ዶላር በላይ ለትግራይ የተከፈለው የአገር ሀብት  ላልቀረበ የወርቅ መጠን እንደቀረበ ተደርጎ  ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ወያኔ ያልቀረበ ወርቅን አስታኮ 20  ቢሊዮን ዶላር በላይ ያገር ሀብት ወደ ትግራይ  wealth transfter  አድርጓል ማለት ነው። ይህ ማለት የሁለት አመት የኢትዮጵያ  አመታዊ በጀትን የሚያህል  የአገር ሀብት ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ  ወርቅ እንዳቀረበች ተሳቦ  እንድትወስድ ተደርጓል ማለት ነው። ይህ ማለት የሁለት አመታት የኢትዮጵያ አመታዊ ሀብት  ወደ ትግራይ እንዲሄድ ሲባል ዘረፋ ተፈጽሟል ማለት ነው። ወገኖች this is a huge wealth transfter.  ወያኔ ከጥር ወዲህም  ማራኪ ቁጥር እያቀረበ  የአገር ሀብት ወደ ተስፋዋ ምድሩ እያሸጋገረ ይገኛል። በሌላ ጊዜ ከሌሎች ቁጥሮች ጀርባ ስለሚፈጸም  አገራዊ ዘረፋ  የምለው ይኖረኛል።
የሚገርመው ትግራይ በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበች በተባለ   በወሩ የቀረበው ሌላ ዜና የስርዓቱ ዜና  ነው። ፋና  በየካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም [እ.ኢ.አ.] ያቀረበው ዜና  ርዕስ እንዲህ ይላል…«ለብሄራዊ ባንክ እየቀረበ ያለው ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው።» ዜናው በዚህ ብቻ አያበቃም። ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም.[እ.ኢ.አ.] በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበች እንዳልተባለ  «ብሄራዊ ባንክ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መልኩ ተመርቶ የሚቀርበለት ወርቅ በእጅጉ ቀንሷል። በ2005 ለባንኩ የቀረበለት 8.1 ቶን ወርቅ ነበር። በ2006 ዓ.ም ደግሞ 7.4 ቶን ሆነ፤ በ2007ም በጣም አሽቆልቁሎ 5.4 ቶንድረስ ወርዷል።» አሉን። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከትግራይ ብቻ ለብሔራዊ ባንክ በአመት 171 ቶን ወርቅ ቀረበ ተብሎ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደቀላል   ወደ ትግራይ transfter  እንዲሆን ባደረጉ በአንድ ወር ውስጥ ነው።
አይ አንቺ አገር! ማፍያዎች የውሸት ቁጥር እየቀቀሉ ሌላውን ጾም ደፍተፍና አራቁተው  የድሆችን ሀብት  ወደ መንደራቸው ያግዛሉ። በአንድ ማጭበርበር ብቻ ሀያ ቢሊዮን ዶላር የአገር ሀብት ወደ መንደራቸው አሸሹ!  በቁጥር ሊሸውዱን ሲሞክሩ በትንተና  እንዲህ ባጋለጥናቸው ጉዳይ ብቻ ሀያ ቢሊዮን ዶላር   በድብቅ ባልተወለደ አንጀታቸው ከገፈፉ ሰው ሳያውቀው የዘረፉት የአገር ሀብት ቢታወቅ ለሌላው ኢትዮጵያ ምን ያህል ያተርፉለት ይሆን?
Filed in: Amharic