>
5:13 pm - Saturday April 18, 0572

የአብይ ጥርስ!!! (ደረጄ ደስታ)

የአብይ ጥርስ!!!
ደረጄ ደስታ
ከጽሁፌ በፊት 18 ዓመት ወደኋላ ልወሰዳችሁና ሩህ ጋዜጣ ላይ የጻፉክትን ላካፍላችሁ።
አቤት የሰነፍ ብዛቱ! ምላስህን ሰብስበህ ቁጭትህን አርግበህ የተሰናከለውን ዘመን በርጋታ ለማለፍ ሁልህም በየጥግህ ትሆናለህ። የደፈረ ሲገኝ ያሳፍርሃል። ላመዛዝን ያለ ሲገኝ ከነሱ አንዱ ይሆንብሃል። ካንተ የተለየ ሁሉ የነሱ ነው። ከነሱ የተለየ ሁሉ ግን ያንተ አይደለም። እውነቴን ነው፣ የምልህ ፓርቲ ያጡ፣ ተከታይ ደጋፊ የሌላቸው፣ ሁሌም የእናንተ ጥርጣሬ የሚቆላቸው ሰዎች አሉ። ለመንግሥት ያላደሩ ካንተ ገልቱ ሃሳብ ያላበሩ ስንት ብቸኞች አሉ መሰለህ። ሕፃን እንደተወለደ ያለቅሳል። ከልደታቸው ጀምረው ሳያቋርጡ እሚያለቅሱ ሰዎች አሉ። አሁን ያንተን ጓደኛ አውቀዋለሁ። አንተም ታውቀዋለህ። የአገርህ የወንዝህ የዘርህ የብሔር ብሔረሰብህ ሰው ስለሆነ አቅፈኸዋል። ጠባብ አልጋ በግድ ያስተቃቅፋል እንዲሉ ጠባብነታችሁ አስተቃቅፏችኋል። ኢትዮጵያን የምታይዋት በናንተ ዓይነ ብቻ ነው። እንደ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ከአካባቢያችሁ ርቃችሁ መሄድ አትችሉም። ኢትዮጵያዊ የሚመታው ዘርህ ሲመታ ብቻ ነው። ሰብዓዊነት እሚጣሰው የደምህ ላስቲክ ሲነደል ብቻ ነው።
…እና ምን እያልኩህ ነበር አዎ ስለጎሰኝነት ይመስለኛል…እና ጎሰኝነት እንደወዳጅ ሆኖ መዝጊያችንን መታ። ከንቱ ባንሆን ባንከፍትለት ወዲያ በተመለሰ። ስታሊን ምንትሴ ተባለና ሰው በእጅ በእውቀቱ ሳይሆን ሊያሳየው በማይችለው ማንነቱ እንዲኮራ ተደረገ። ማንነት? ማንነት ራሱ የማንነት ቀውስ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ማንነት ሲያፍሩበትም ሲኮሩበትም በሽታ ነው። በሽታ ባይሆን ድንቁርና ነው። ሰው ከሰው እንዴት ይበልጣል? ሰው ከሰውስ እንዴት ያንሳል? ለምሳሌ አሁን ይህን ይዘህ ለአገር ብታወራ ሰዎች እንደ ጅብ ይወሩሃል። እህል አገኙም አላገኙም ሊበሉህ ይደርሳሉ።  (ሩፋኤል ውበቱ – ሩሕ ጋዜጣ፣ “ይልቅ ወሬ ልንገርህ” አምድ ሰኔ 2/1992)
እና ዘንድሮም –
 የኛና የነሱ ወገን ጨዋታና መበላላቱ ቀጥሏል። ነፍሰ ገዳዩ የኔ ወገን ነው፣ ዘራፊው የኔው ወገን ነውና አትንኩት እሱን መንካት እኔንና ህዝቤን እንደመንካት ነው  እያሉ…. ጎሰኞች ሲያለቃቅሱ ተመለከትኩ። አብይ ጥርስ የላቸውም ወላቃ ናቸው ብለው አዘናግተው ቀና ሊሉ ፖለቲካ አንስተው ፖለቲካ ሲጥሉ ሰውየው ጥርስ አወጡባቸው። በዚህ ተበሳጩ፡፡ ደግሞ ሌሎች አብይ ጥርስ አወጡ፣ ሰርቆ የሰባውን ሁሉ እየነከሱ ባላዳባና ባለካባውን ሊበጣጥሱ ተነሱ እያሉ ደስ ተሰኙ። ኡኡታውና እልልታው ቀልጧል። እኔም አለቅጥ ደስ አለኝ። ደስታዬ ግን የኔ ወገን አሰረ ያኛው ወገን ታሰረ ከሚል አይደለም። በቃ እርቅ ይሁን የተራበም የጠገበም ያለፈው አልፏል ብሎ ለአገር አንድነት ይነሳ ሲባል እምቢ ብለው ፍቅር ረግጠው ተሰባስበውና ተቧድነው ሊመጡ ሲሉ… ወረደ መግደል እንደለመደ ብለው ሲፎክሩ…እንግዲያውስ ገመናችሁ ያውላችሁ የተባሉት በመደፈራቸው ነው። እንጂ ደስታዬ አብይ ጥርስ ስላወጡ አይደለም። አብይ መቸም መቸም ጥርስ እንዲያወጡ አልፈልግም። ለዚህ ያበቃን የመሪዎች ጥርስ ማጣት ሳይሆን ጥርስ  ማብዛት ነው። ጥርስ ማውጣት ያለበት ህዝብ ነው። መሪ ጥርስ ምን ያደርግለታል? የህዝብ ጥርስ ህግ ነው፣ የህዝብ ጥርስ ፍትህ ነው፣ የህዝብ ጥርስ ነጻ ፕሬስ ነው። የህዝብ ጥርስ ነጻና ገልለተኛ ምርጫ ቦርድ ነው። እንጂ አምባገነን መሪዎች ወይም የኛ ወገን ይግደል የነዚያ ወገን ሰዎች ይሙቱ እሚሉት የእፍኝት ልጆች እሚያበቅሉት ጥርስ አይደለም። ደግነቱ አብይ እስካሁን እንደዚያ ያሉ ሰው መሆናቸውን አላሳዩም። የኢትዮጵያ ልጅ መሆናቸውን የመርህ ልጅ መሆናቸውን ለማሳየት እሚያደርጉትን ጥረት አለማድነቅ አይቻልም። አንቺ ታመጪው አንቺው ታሮጪው እሚባለው ድርጅታቸው “ኢህአዴግን” አለመርሳት እንደተጠበቀ ሆኖ ህወሃት የወለቀበት ቦታ ላይ ሌላ አርቲፊሻል ጥርስ እንዳይተክል መጠንቀቅ ነው። ቢቻል ቢቻልማ እንዲያውም ኢህአዴግ ራሱ እንዳለ ጥርሱ አልቆ በድዱ ቀርቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥርስ ሲያወጣ ማየት ጥሩ ነገር ነው። አብይ ለዚያ እሚያበቁን ከሆነ የወርቅ ጥርስም ቢሆን ይገባቸዋል። ሲስቁ ለማየት። እሚወዱት ሰው ሲስቅ ከማየት ሌላ ምን ደስ እሚል ነገር ይኖራል!-
ዋናው ነገር ግን እነዚህ የተያዙት ሰዎች ሰርቀዋል አልሰረቁም? ገድለዋል አልገደሉም እሚለው በትክክል መረጋገጡ ነው። ያ ከተረጋገጠ በኋላ ግን ገዳዮቹም የኔ ፣ ሌቦቹም የኔ ወገኖች ናቸውና ለምን ተነኩ ማለት ግን ….በሌብነትና በግድያ ተፈትኖ ከወደቀ ወንበዴና ነፍሰ ገዳይ ወገን በመወለድ እንደመኩራት ነው። ወይም የወስላቶች አብዮት ወስላቶቹን ልጆቿን በላች እንደማለት ይሆናል። የህዝብ ወንበዴ የታጋይ ነጋዴ ግን የለውም። ስለዚህ እንደዚያ ዓይነቶቹን እንኳን የአብይ ጥርስ የሌላውም ጥርስ ቢሆን አይምራቸውም። ሌኒን ቢኖር – ሌባ ሁላ! ይል ነበር…..
Filed in: Amharic