>

የኢትዮጵያን መርከቦች በርካሽ  አከራይተው የውጪ መርከቦችን በውድ የሚከራዩት ሌቦች! (ስዩም ተሾመ)

የኢትዮጵያን መርከቦች በርካሽ  አከራይተው የውጪ መርከቦችን በውድ የሚከራዩት ሌቦች!
ስዩም ተሾመ
 ቀኑን ሙሉ የጠፋሁት “የጠፉትን መርከቦች ስፈልግ” ነው። ትላንት የጠፉት መርከቦች ቁጥር አራት መድረሱን ገልጩ ነበር። ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያን መርከቦች በርካሽ አከራይቶ የሌላ ሀገር መርከቦችን በውድ ስለሚከራዩ ጉዶች ልንገራችሁ? ነገሩ እንደዚህ ነው፤ እ.አ.አ. በ2012 ባህር ዳር እና በ2013 ዓ.ም ደግሞ ሃዋሳ የተባሉ ሁለት መርከቦችን እያንዳንዳቸው በ37 ሚሊዮን ዶላር ከአንድ የቻይና መርከብ አምራች ድርጅት ይገዛሉ። በድምሩ 74 ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው ሁለት መርከቦች የተገዙበት መሰረታዊ ዓላማ ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባውን ነዳጅ ለማመላለስ የሚያገለግሉ ናቸው። እነዚህ መርከቦች ተገዝተው መጥተው ልክ ጅቡቲ ወደብ ሲደርሱ የኢዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከአንድ የውጪ ድርጅት ጋር ስምምነት ይፈራረማል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የነዳጅ ምርት እንዲያመላልሱ የተገዙት ባህር ዳር እና ሃዋሳ የተሰኙት ሁለት መርከቦች ለስድስት ወር ያህል ጅቡቲ ወደብ ላይ ሥራ አጥተው ቆሞ። እነዚህ ሁለት መርከቦች ከተገዙ አምስት አመት ሞላቸው። በእነዚህ አመታት ውስጥ አንድ ቀን እንኳን ወደ ኢትዮጵያ ለሚገባው ነዳጅ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጥተው አያውቁም። ከቻይና በተገኘ 74 ሚሊዮን ዶላር ብድር የተገዙት የኢትዮጵያ ነዳጅ ጫኚ መርከቦች አንድም ቀን የኢትዮጵያን ነዳጅ ጭነው አያውቁም። ሀገሪቱ ለነዳጅ ጫኚ መርከቦች ኪራይ መክፈል የለባትም ተብለው የተገዙት ነዳጅ ጫኚ መርከቦች ተከራይተው ለሌላ ሀገር ነዳጅ በማመላለስ ላይ ይገኛሉ።
“ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ነዳጅ በኢትዮጵያ መርከቦች ቢጓጓዝ ችግሩ ምንድነው?” ላላችሁ መልሱ በአጭሩ “የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ኃላፊዎች በየአመቱ የመርከብ ኪራይ ውል ሲፈራረሙ ከአከራዮች የሚያገኙት ኮሚሽን (ጉቦ) ስለሚቀርባቸው” የሚል ነው። ይህ የኪራይ ውል ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ኃላፊዎች ለዕረፍት ወደ አሜሪካ ይሄዳሉ። ከምሬ ነው! ውሸቴን ከመሰላችሁ በቅርቡ የዕረፍት ግዜያቸውን ጨርሰው የተመለሱትን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ምክትል ኃላፊ መጠየቅ ትችላላችሁ።
Filed in: Amharic