>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6141

የሕወሓት ባለሥልጣናትን ትብብርና ውለታ ስለመጠየቅ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

የሕወሓት ባለሥልጣናትን ትብብርና ውለታ ስለመጠየቅ!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
ወንጀል የፈጸሙ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት እስራትን በተመለከተ እናንተ እስራቱን “ሕወሓት ላይ ነው ያተኮረው በመሆኑም ፖለቲካዊ ነው፡፡ ወንጀል የፈጸሙት የሕወሓት አመራሮች ብቻ አይደሉም፡፡ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ካለበት የብአዴን፣ የኦሕዴድ፣ የደኢሕዴን አመራሮችንም ሕጉ በዕኩል ደረጃ  ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባል! ካልሆነ ግን ሕወሓት ላይ ብቻ የሚያነጣጥርን ተጠያቂነት አንቀበልም!” የሚል ምክንያት በማቅረብ ሕግ የሚፈልጋቸውን ወንጀለኞች (ተጠርጣሪዎች) አሳልፎ ላለመስጠት መወሰናቹህን አስታውቃቹሃል፡፡
ለነገሩ እናንተ እንደዚህ አላቹህ እንጅ በቁጥጥር ስር የዋሉት የሕወሓት ባለሥልጣናት ብቻ እንዳልሆኑና እንዲያውም በቁጥር ላቅ የሚሉት ምክትሎቻቸው የሆኑ ከሕወሓት ውጭ ያሉ የኢሕአዴግ አባላት መሆናቸውን አሳምራቹህ ታውቃላቹህ፡፡
ከዚህ አንጻር እኔ በግሌ ይሄንን ያቀረባቹህትን የማይመስል ምክንያት ከተጠያቂነት ለማምለጫነት ወይም ቀድሞም ቢሆን የማስመሰል ወይም ሕዝብን ለመደለል ሲባል የተወሰደውን የእስር እርምጃ እራሳቹህን በማስመሰሉ እርምጃ ሊመጣ ከሚችል ያልታሰበ ሪስክ (አደጋ) ለመጠበቅ ስትሉ የእስር እርምጃ ድራማው (ትውንተ ሁነቱ) እንዳይቀጥል ለማድረግ የተፈጠረ ሐሰተኛ ምክንያት እንደሆነ አስባለሁ፡፡
“አይ አይደለም እስራቱ የምር ነው ድራማ አይደለም!” የምትሉ ከሆነ ግን እነ ዐቢይ የእናንተን ሰዎች በብዙኃን መገናኛዎች የፈጸሙትን ወይም የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለሕዝብ እንደገለጹ ሁሉ እናንተም በእናንተ ደረጃ “ወንጀል ሠርተዋል መታሰር አለባቸው!” የምትሏቸውን የኦሕዴድ፣ የብአዴን፣ የደኢሕዴን አመራሮችን ወንጀሎች በብዙኃን መገናኛዎች ለሕዝብ በመግለጥ ሕዝብ እንዲያውቅና ለተጠያቂነታቸው እንዲንቀሳቀስ በማድረግ “ለሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት መጠበቅ ቁርጠኞች ነን!” ያላቹህትን ቃል እንድታረጋግጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
ይሄንን ማድረግ ካልቻላቹህ ግን ከላይ የገለጽኩትን የነገርየውን ትወናነት ጥርጣሬ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ እንዲያው ነገሩን አልኩ እንጅ እነሱ እንደምትሉት ዓይነት በእናንተ ደረጃ ከባባድ ወንጀል እያለባቸው እናንተ ይሄንን ያህል ታግሳቹህ ዝም ትላላቹህ ተብሎ አይታሰብም፡፡ እነሱም ደግሞ በእናንተ ደረጃ ወንጀል እያለባቸው በእናንተ ላይ ጣት ለመቀሰር ፈጽሞ አይደፍሩም ነበር፡፡ በመሆኑም በእነሱ ላይ እያወራቹህት ያላቹህት ነገር ወይ ሐሰተኛ ስም ማጥፋት ነው ወይ ደግሞ ነገርየው በአጠቃላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ እየተመካከራቹህ የለውጥ ኃይልና ለውጥ አደናቃፊ የሚል ገጸባሕርያትን ይዛቹህ የምትተውኑት ትወና ነው ማለት ነው፡፡
እርግጥ ነው እናንተን ሲያገለግሉ እንደመኖራቸው መጠን የብአዴን፣ የኦሕዴድ፣ የደኢሕዴን አመራሮች ከወንጀል የጸዱ ሊሆኑ እንደማይችሉ ማንም ሊገምተው የሚችለው ሐቅ ነው፡፡ ነገር ግን በምንም ተአምር ቢሆን ወንጀሎቻቸው በእናንተ በአለቆቻቸው ወንጀሎች ደረጃ ሊሆን አይችልም፡፡ ይሄም ማለት ተጠያቂነታቸው በእናንተ ደረጃ አይሆንም ማለት ነው፡፡ መለስተኛ ወንጀሎች ነው ሊኖርባቸው የሚችለው፡፡ እሱም ቢሆን ግን ይሄንን የፈጸሙትን መለስተኛ ወንጀል “እንዴትና ለምን ፈጸሙት???” የሚለውን ዐቢይ ነጥብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያይ ሳይመለከት በእነሱ ላይ መፍረድ እንደማይፈልግ መገንዘብ ይኖርባቹሃል፡፡ ምክንያቱም ወንጀል ከሰሩ ወንጀሉን የሚሠሩት በእናንተው በአለቆቻቸው አስገዳጅነት ነውና፡፡
ይሄም ማለት የብአዴን፣ የኦሕዴድ፣ የደኢሕዴን አመራሮች የእናንተ አሻንጉሊቶች፣ ትዕዛዝ ፈጻሚዎችና ጭራሽ እንዲያውም እነሱም እራሳቸው የእናንተ የግፍ አገዛዝ የቅጣት ሰለባዎች እንደመሆናቸው መጠን “ምንም ዓይነት ዋጋ ቢያስከፍለንም እንክፈል!” ብለው ቆርጠው፣ ጨክነው፣ በራሳቸው ላይ ፈርደው “ከሕወሓት ባርነትና ዘበኝነት ነጻ ወጥተን፣ ተለውጠን ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዚህች ሀገር ቆመናል!” ማለታቸውን ከሕዝብ በተዘረፈ ሀብት በሕገወጥ መንገድ ተመሥርቶ ግብርና ቀረጥ ሳይከፍል በሕገወጥ መንገድ እየሠራ ያለውን ኤፈርትን (ትእምትን) እና እኅት ድርጅቶቹን ማለትም ጥረትን፣ ዲንሾን፣ ወንዶን ውርስ ለመንግሥት በማድረግ የመለወጣቸውን እውነትነት ማረጋገጥ የሚችሉ ከሆነና የወያኔ ባለሥልጣናትን በሙሉ ለፈጸሙት ወንጀል በሙሉ ሕግ ፊት ለማቅረብ ቁርጠኝነቱ ካላቸው ዋጋ ለመክፈል ቆርጠው ከእናንተ ጨካኝ እጅ መጥተው እንዲህ ዓይነት ድፍረት የተሞላበት ወሳኝ አቋማቸውንና ንስሐቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ትልቅ ውለታ ቆጥሮ እናንተ ባሳደራቹህባቸው ጫና ለፈጸሙት ወንጀል ሁሉ ለጊዜው እነሱን ተጠያቂ ማድረግ አይፈልግም!!! ሕግም ቢሆን አባሪ ተባባሪን ከዋና ወንጀል ፈጻሚ ጋር ዕኩል አይቀጣም፡፡
ይሄ ግን አሁንም ድረስ ለእናንተ ታማኝ ሆነው የሚንቀሳቀሱትን እርጉም የብአዴን፣ የኦሕዴድና የደኢሕዴን እንዲሁም የአጋር ድርጅቶች አባላትን አይጨምርም!!! እነኝህ እርጉሞች ለእናንተ የብረት ምርኩዝ በመሆን በሀገርና በሕዝብ ላይ ይሄንን ሁሉ ጥፋት እንድታደርሱ ያስቻሉ ናቸውና ከእናንተ ባልተናነሰ ደረጃ ተጠያቂ የሚሆኑ ናቸው!!!
እርግጥ ነው የለውጥ ኃይሉ እንቅስቃሴ እውነት ከሆነ የኤፈርት ፋብሪካዎች (ማበጆች) እና ኢንዱስትሪዎች (ምግንባቦች) ያሉት ትግራይ ውስጥ እንደመሆናቸው በአሁኑ ሰዓት ኤፈርትንና ንብረቶቹን በሙሉ ውርስ ለመንግሥት ለማድረግ አይችሉ ይሆናል፡፡ ይሁንና አንድ ነገር ግን ማድረግ ይችላሉ፡፡ እሱም የጥረትን፣ የዲንሾንና የወንዶን ንብረቶች ውርስ ለመንግሥት በማድረግ ኤፈርት ሕገወጥ ድርጅት መሆኑን በማወጅ ከትግራይ ውጭ የትም ቦታ በሀገሪቱ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ግን ይችላሉ፡፡
ይሄንን ወሳኝ እርምጃ የመውሰድ ያለመውሰዱ ጉዳይ ለውጥ የሚባለው ነገር እውነት መሆን አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እርምጃውን ከወሰዱ ለውጡ እውነት መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ እርምጃውን ካልወሰዱ ግን ለውጥ የሚባለው ነገር ውሸት ወይም ደንበኛ ድራማ (ትውንተ ሁነት) መሆኑን በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ይመስለኛል የለውጥ ኃይል የሚባለው እስከአሁንም ይሄንን እርምጃ ያልወሰዱበት ወይም ኤፈርትና እኅት ድርጅቶቹ ሕገወጥ መሆናቸውን የሚገልጥ አቋም እንዳላቸው እንኳ ያላሳወቁበት ምክንያት ለውጥ የሚባለው ነገር ውሸት ወይም ትወና ስለሆነ ነው፡፡
የሕዝብን ሀብት ከባንክና ከመንግሥት ድርጅቶች በመዝረፍ ተመሥርቶ፣ በሕገወጥ መንገድ ተቋቁሞ፣ ቀረጥና ግብር ሳይከፍል እየሠራ የሀገሪቱን ጋዝና ያራቆተው ይሕ ሕገወጥ የወንበዴዎች ድርጅት እያለ ሜቴክ ምንንትስ እያሉ በትንሹ ጉዳይ ለማላዘን የመረጡትም በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡
“አይ የለውጥ ኃይሉ ጊዜ እየጠበቀ ስለሆነ ነው እንጅ ይሄንን ማድረጋቸውማ አይቀርም!” ከተባለም ሊያስኬድ ይችላል ነገር ግን እርምጃው ወደፊት የሚወሰድ ሆኖ ለአሁኑ ግን ቢያንስ በአቋም ደረጃ ግርጅቶቹ ሕገወጦች መሆናቸውን  በመግለጥ አቋማቸውን ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሲጠቃለል ሔዶ ሔዶ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለ27 ዓመታት ለወረደው እጅግ አሳዛኝ አረመኔያዊ ግፍና ለተፈጸመው እጅግ አሳፋሪ ዝርፊያ ዋነኛ ተጠቃቂዎቹ እናንተው ሕወሓቶች መሆናቹህ እርግጥ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄንን አሳምራቹህ ታውቁታላቹህ፡፡
ስለሆነም ሕግ ፊት ላለመቅረብ ወይም ተጠያቂነትን ለመሸሽ እያቀረባቹህት ያለው ምክንያት ሁሉ ውኃ የማይቋጥ፣ ተልካሻ፣ የማያሳምንና የማይመስል በመሆኑ “የእስር እርምጃውም ሆነ የለውጥ እንቅስቃሴው የማታለል፣ የማስመሰልና ሕዝብን ለመደለል እየተደረገ ያለ ድራማ (ትውንተ ሁነት) ሳይሆን እውነተኛ ነው!” የምትሉ ከሆነና እውነቱም እንደዚያ ከሆነ ተጠያቂ መሆናቹህ መቸም ቢሆን አይቀርምና የሕግ የበላይነትን በማክበር እራሳቹህን ለሕግ አሳልፋቹህ በመስጠት ውለታ ትውሉልን ዘንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠይቃል??? ይሄንን ማድረጋቹህ ፍርድ ሊያቀልላቹህ ይችላልና “እንደዋዛ ባታዩት!” ብየ ምክር ቢጤ ልለግሳቹህ እወዳለሁ፡፡ ለትብብራቹህ አስቀድመን በእጅጉ እናመሰግናለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic