>
5:18 pm - Thursday June 16, 7836

"ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሕዝበኛ ወይንም ፖፕሊስት አይደሉም !!!"  ፎሪን ፖሊሲ መጽሔት

“ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሕዝበኛ ወይንም ፖፕሊስት አይደሉም !!!”
 ፎሪን ፖሊሲ መጽሔት
(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 28/2011)  የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለፖለቲካ አላማቸው ሲሉ ሕዝብን ወደ ራሳቸው ፍላጎት ለማምጣት ሌሎችን በጠላትነት የሚፈርጁ ሕዝበኛ ወይንም ፖፕሊስት አይደሉም ሲል ታዋቂው የትንተና መጽሔት ፎሪን ፖሊሲ ዘገበ።
አንዳንድ በስም የጠቀሳቸው ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ሕዝበኛ ሲሉ ቢያነሷቸውም ዶክተር አብይ አሕመድ እንደ አሜሪካው ትራምፕም ሆነ እንደ ቱርኩ ኤርዶጋን ብራሳቸው ዙሪያ ሰዎችን ለማሰልፍ ተቀናቃኛቸውን በጠላትነት የሚፈርጁ አይደሉም ሲል ምስክርነቱን ሰቷቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከመንግስቱ ሃይለማርያምም ሆነ ከመለስ ዜናዊ በተለየ ከፍረጃ ፖለቲካ ወተው ሁሉንም ሃይሎች በሃገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ እያደረጉ ናቸው ሲልም በሰፊው ዘርዝሯል።
ከ48 አመታት በፊት የተመሰረተውና መቀመጫውን በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ፎሪን ፖሊሲ መጽሔት “አብይ አሕመድ ፖፕሊስት/ወይም ሕዝበኛ አይደለም”በሚል ርዕስ በቶም ጋርድነር በቀረበው ጽሁፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በወሰዳቸው ርምጃዎች በሃገራቸው ያገኙትን ሕዝባዊ ድጋፍና በውጭ አለም ያላቸውን ተቀባይነት ዘርዝሯል።
ዶክተር አብይ አሕመድ ያገኙትን ድጋፍና ተቀባይነት በበጎ የማይመለከቱና ይልቁንም ይህንን “አብይ ማንያ” ወይንም “የአብይ ልክፍት” በማለት የሚጠሩት ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን፣ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚያመሳስሏቸው ገልጿል።
ሆኖም ዶክተር አብይ አሕመድ እንደተጠቃሶቹ የሃገር መሪዎች ፖፕሊስት ወይንም ሕዝብን በዙሪያቸው ለማሰለፍ ተቀናቃኞቻቸውን በጠላትነት የሚፈርጁ አይደሉም ሲል መጽሔቱ ምስክርነት ሰቷል።
ዶክተር አብይ አሕመድ ሕዝብን በዙሪያቸው ለማሰለፍ ከመድረኩ የተገለሉትን የሕወሃት መሪዎችን እንኳን በጠላትነት ሲፈርጁ ያልታዩ፣አሸባሪ ተብለው ከሃገራቸው የተገለሉ ሃይሎችን በሃገራቸው ጉዳይ በባለቤትነት እንዲሳተፉ ያደረጉ፣በጥቅል ከፍረጃ ይልቅ መደመር በሚል መርሃቸው ሁሉንም ባለድርሻ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ሲል በጽሁፉ አስፍሯል።
ፎሪን ፖሊሲ ላቀረበው መሞገቻ ጽሁፍ በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሕግ ባለሙያ የሆኑትን አቶ መኮንን ፍሬውን በአስረጅነት ጠቅሷል።
አቶ መኮንን ፍሬው እንደገለጹት ዶክተር አብይ አሕመድ እንደ ኮለኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ተቀናቃኞቻቸውን ኢምፔሪያሊስቶች፣እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ጠባብና ትምክተኛ እያሉ ፍረጃ ውስጥ አይገቡም።
Filed in: Amharic