>
5:12 pm - Wednesday November 30, 2022

በተነቃነቀ ጥርስ አጥንት የመጋጥ ሙከራ ...!!! (ደስታ እንበል)

በተነቃነቀ ጥርስ አጥንት የመጋጥ ሙከራ …!!!
ደስታ እንበል
የሕወሓት 1ለ5 አደረጃጀት በግዳጅ የጠራቸው  የመቀሌ ነዋሪዎች በዘራፊው የኤፈርት ኩባንያ…. በአልመዳ ጨርቃ-ጨርቅ ከናቴራዎች  ተዥጎርጉረው ለሰልፍ ወጥተዋል ። ዶክተር ደብረፅዮን ” …. ከአማራ ሱዳን ይሻለናል ! ” አለ የተባለውን ሐሳብ የተሟላ ስሜት እንዲያስተላልፍ ተፈልጎ ሳይሆን አይቀርም ከተማዋን  ካሸበረቁት ሰንደቆች አንዱ የሱዳን ነው ። በተጨማሪም የኦነግ ባንዲራ የመቀሌን ሰልፍ እንዲያደምቅ ከተመረጡት የወዳጅ ባንዲራዎች  አንዱ ሆኗል ።
.
የሰልፉ ዋነኛ አላማ ” ሕገ-መንግስቱ ይከበር ፤ ……. ! ” የሚል ነው ። የቸገረው እርጉዝ ያገባል ሆኖ ነው እንጂ ይህ መርህ ለሕወሓት ሰልፍ የሚያሶጣ አልነበረም ። ሕወሓት 27 አመት ሙሉ በወረቀት ብቻ የሚያውቀውና ሲረግጠው የኖረውን  ሕገ መንግስት ዛሬ ” አክብሩልኝ ! ” ብሎ ሕዝብን በሰልፍ ማዋከቡ ፌዝ ነው ።  …. ግራ ከመጋባትም የመነጨ እንደሆነ አያጠራጥርም ።
.
ለመሆኑ ባለፉት የሕወሓታውያን የግፍ  ዘመናት ፦ ሰው ሲገደል ፣በጅምላ ሲታሰር ፣ ሲገረፍ ፣ሲኮላሽ ፣ጥፍሩ ሲነቀል ፣ ሴቶች በመርማሪዎች በደቦ ሲደፈሩ ፣ ወንዶች ላይ ግብረ-ሰዶም ሲፈፀም ፣ በአጠቃለይ ገሃነምን የሚያስመርቅ ምርመራ በዜጎች ላይ ሲከናወን ፣ ማታ ገራፊና  መርማሪ የሆነ ሰው  ጠዋት ዳኛ ሆኖ በፍትህ ወንበር ላይ ሲሰየም ፣ሕዝብ ሲፈናቀል ፣ የመናገር ፣ የመፃፍ የመደራጀት መብት ሲገደብ ፣ ለከት የለሽ የመሬት ቅርምት በካድሬዎች ሲፈፀም ፣ ሐገር በተደራጁና መንግስታዊ ከለላ በተሰጣቸው ተቋማትና ቡድኖች ሲዘረፍ ፣
” ሕገመንግስቱ ያፀደቀልኝ ማንነቴ ይከበርልኝ ! ”  በማለቱ ዜጋ ሲሳደድ ፣ ሕዝብ ” ፍትሃዊ የሐብትና የልማት ክፍፍል ይስፈን ! ” በማለቱ ሲታፈን ፣ የሐገሪቱ ቁልፍ ተቋማት በአንድ ቡድን የአመራር ተፅእኖ ስር  ሲወድቅ ፤
የሐይማኖት ተቋማት ጠመንጃ በታጠቁ ፣ ጫማ ባጠለቁ አጋዚ ገዳዮች ሲረክስ ፣ ሰው ከርስቱ ፣ ከዘመናት ሕጋዊ ይዞታውና  በቱ ከነንብረቱ በዶዘር ሲፈርስ ፣ ከቁልፍ የንግድ አካባቢዎች ስልታዊ በሆነ ዘዴ ነባር ነጋዴዎችን አሶግዶ የስርአቱ ሰው ሲተከል ፣ ስርአቱን የሚገዳደሩ ልሂቃን ከአገር ለቀው እንዲወጡ ሲገደዱ ፣
የሐገር ታሪካዊ ድንበር ተሻግሮ መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ፤…………በነዚህና ከዚህም በበዙ ገሃድ ምክንያቶች  ሕገመንግስቱ  ጥሰት ሲፈፀምበት ፤….  በሰልፍ ቀርቶ በትንንሽ የስብሰባ መድረክም ” ሕገመንግስት ተጣሰ ! ” ያላለ ቡድን ዛሬ ደርሶ የሕገመንግስት ጠበቃ ሆኖ ለመቅረብ መሞክር ይህም ፌዝ ነው ።
.
ሕወሓት አሁን የሚያደርገው እንቅስቃሴ  መቃብሩ አፋፍ ላይ ቆሞ ነው ፤ ይህ ሁሉ የሰልፍ ጋጋታም የመቃብሩ አፋፍ ሽታ  የፈጠረበት የፍራቻ  ስሜት የወለደው  ነው ።
.
በሌላ መልኩ ሕወሓት የማእከላዊ መንግስት ስልጣኑ ሳያስበውና ቅዠት በሚመስል ሁኔታ እንደ ጠዋት ጤዛ ረግፎበታል ፤ ከጁ አምልጧል ። ይህን ስልጣን መልሶ ከጁ የሚያስገባበት እድልም ሞቶ ተቀብሯል ። ይህ ቡድን አሁን ያለው አማራጭ የክልሉን ስልጣን ከእጁ እንዳይወጣ ለ27 አመታት የከዳውን ሕዝብ ምሽግ አድርጎ መውተርተር ነው ። ሌላኛው ደግሞ በንፁሐን ደምና መረን በወጣ ዝርፊያ የጨቀየው ሕወሓት ተጠያቂ የሚያደርገው የተረጋጋና ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት እንዳይኖር በዝርፊያ ያከማቸውን ገንዘብ በመጠቀም እዚህም አዚያ እሳት መለኮስ ነው ። ሰልፉም የዚህ እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው ። ይህም በተነቃነቀ ጥርስ አጥንት ለመቆርጠም ከመሞከር አይተናነስም ።  ይህ ሰልፍ ወደ እብደት የተቀየረ ብስጭትም የተንፀባረቀበት አይነት  ነው ፤ ብስለት የጎደለው የሕፃናት የብሽሽቅ አይነት ጨዋታም ያለቀት የሚመስል ነው ። ለዚህ ማረጋገጫ 27 አመት የኦነግ አባልና ድርጅቱን ሲያሳድድ የነበረው ሕወሓት የኦነግን ባንዲራ በፍቅር ማውለብለቡና የሱዳንንም ባንዲራ ለሰልፍ ድምቀት መመረጡ ነው ።  ይህ ደግሞ  አሳፋሪ የፖለቲካ ቁማርም ነው ፤ በቁማር ደግሞ ኪሳራ እንጂ ትርፍ ተገኝቶ አይታወቅም ።
አይህ ኣብርሃ ደስታ ስለ መቐለው ሰልፍ በገጻቸው ላይ ይህን አስፍረዋል!!!
ለ20 ዓመታት ያህል “ሕግ ይከበር” ስንል ነበር። ህወሓትም ለ27 ዓመት ስትረግጠው የነበረችውን “ሕግ” አሁን ከተመታች በኋላ የ”ሕግ ይከበር” ተቃውሞ ከህዝብ ጋር ተቀላቅላለች። ከዓመታት በፊት ሕግ የጣሱ ዶኩመንታሪዎች (አኬልዳማ፣ ጂሃዳዊ ሐራካት ወዘተ) ስትሰራ ሕግ መጣሱ ያልገባት የ”ሜቴክ” ዶኩመንተሪ ሲሰራ ግን ገብቷታል።
ሁሉም ነገር የሚገባህ ራስህ ላይ ሲደርስ ነው። ህወሓት ስታፍንበት በነበረችው ሕግ ራሷ ስትዳኝ ምን ያህል መጥፎ እንደነበረች ይገባታል። ትንሽ ቆይታ “የፀረ ሽብር ሕግ ዓፋኝ ነው፤ ይሰረዝ” ብላ ሰልፍ ትጠራለች። ለማንኛውም “ሕግ ይከበር” የህዝብ ጥያቄ ነው፤ የሁላችን አጀንዳ ነው። መንግስት ሕግ ያክብር፣ የንፁሃን ዜጎች ህይወት ይጠብቅ። በሕግ የሚጠየቅ ደግሞ ይጠየቅ! It is so!!!
Filed in: Amharic