>

ሶርያዊያኑ እኛን ለማስተማር ይሆን የተላኩት ? (ብር ክስ ሀበሻዊ)

ሶርያዊያኑ እኛን ለማስተማር ይሆን የተላኩት ?
ብርክስ ሀበሻዊ
በማህበራዊ ድረ ገጾች  ሰሞኑን ከሚሰራጩት ምስሎች መካከል በስደት መጥተው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ምጽዋት የሚጠይቁት ሶርያዊያን የብዙዎች መነጋገሪያ ሆነዋል፡፡  ለዓመታት በእርስ በርስ ግጭት የቆየችው አገር ዜጎች ለስደት ተዳርገው ይህን አስከፊ ጽዋ መጎንጨታቸውን የሚያሳዩትን ምስሎች ተከትሎም ኢትዮጵውያን  በ ‹‹ነግ በእኔ›› መንፈስ በርካታ አስተያየት አስፍረዋል፡፡
አንድ ሶርያዊ አባት ልጁን ይዞ በአዲስ አበባ ጎዳና ምጽዋት ሲጠይቅ የሚያሳይ ምስልን ተከትሎ ዮሐንስ በሚል ስም ፌስ ቡክ የሚጠቀም ዜጋ ‹‹ሃገር ስትሞት እንዲህ ነው። ዛሬ ዘር ለይተህ ከብሄርህ ሌላ ያለን ሰው ባጠቃህ ቁጥር ሃገርህን እየገደልካት እንደሆነ እወቅ። በእቅድ የፈረሰ ሃገር የለም›› የሚል አስተያየት አስፍሯል።
«እግዚአብሔር እነዚህን ሶርያዊያን ወደ እኛ የላካቸው ምናልባት እነርሱን ዓይተን እንድንማር ሊሆን ይችላል፡፡ … ዘረኝነት በቃ ብለን በኢትዮጵያ ዊነታችንና በአባቶቻችን ፍቅር አንድ ሆነን ተስማምተን እንኑር፡፡ የእነዚህ ሶሪያዎች ወደሃገራችን መምጣት ለእኛ ትልቅ መልዕክት ነው፤ ሶርያዊያኑ የእርስ በርስ ጦርነትን አስከፊነት እኛ እንድንማር የተላኩ ናቸው›› ያለው ደግሞ አድማሱ የተባለ የማህበራዊ ድረ ገጹ ተጠቃሚ ሲሆን፤ አጸደ የተባለች ሌላ ግለሰብ ‹‹አዎ የሰላም ዋጋው ብዙ ነው፤ እኛ ግን አልተረዳነውም›› ብላለች፡፡
ባህር ተሻግረው በረሃ አቋርጠው፤ የቀን ንዳድ የሌት ቁር ሳይበግራቸው አስከፊውን ጦርነት ሸሽተው በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው በአዲስ አበባ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ህይወታቸውን ለማሰንበት ምጽዋት ከሚጠይቁት ሶርያውያን መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ጃዕፋር አንዷ ናቸው፡፡ ወደ ስፍራው ባቀናንበት ወቅት  በአማርኛ ችግራቸውን የሚያስረዳ ጽሑፍ  ይዘው በመንገዱ አካፋይ ላይ ወዲያ ወዲህ እያሉ ተላላፊ አሽከርካሪዎችን ዕርዳታ እየጠየቁ ነበር፡፡ ብዙዎችም እጃቸውን ከመኪናቸው መስኮት እየዘረጉ ለእናት ፋጡማ እገዛቸውን ይቸራሉ፡፡
ከሀገሪቱ መዲና ደማስቆ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዱማ ከተማ ውስጥ ተወልደው እንዳደጉ እና እዚያው አግብተው ወልደውና ከብደው ይኖሩ  እንደነበር ወይዘሮ ፋጡማ ይናገራሉ፡፡ ተወልደው፣ አድገውና ወልደው በከበዱባት ስፍራ ግን በሰላም መኖር አልቻሉም፡፡ ከተማዋ ለተከታታይ አምስት ዓመታት የጦርነት አውድማ በመሆኗ  ለአስከፊው የስደት ህይወት መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡
የፕሬዚዳንት አሳድ መንግሥት እና የተቃዋሚ ደጋፊዎች  ለዓመታት ባካሄዱት ፍልሚያ ወደ ፍርስራሽ ወደተቀየረችው የትውልድ ቀዬአቸው በትዝታ ጭልጥ ብለው በመሄድ ሁኔታውን የሚያስታውሱት ወይዘሮ ፋጡማ ‹‹ባለቤቴ፣ ወንድሞቼ፣ እህቴ፣ አባትና እናቴን በጦርነቱ ምክንያት ተነጥቀዋል፡፡ የአብራኬ ክፋይ የሆኑት ልጆቼም በጦርነቱ የሞቱ ሲሆን፤ በህይወት የተረፈው  አንድ ልጄም  ከጦር ጀት በተወረወረ ቦንብ እግሩን ተጎድቶ በዊልቸር ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ያፈራነው ንብረት በሙሉ በጦርነቱ ወድሟል›› በማለት  ከቀዬአቸው ያሰደዳቸውንና በሰው አገር የሰው ፊት እንዲገርፋቸው ያደረገውን የእርስ በርስ ጦርነት አስከፊ አሻራ ያነሳሉ፡፡
   ወይዘሮ ፋጡማ ማብቂያ ያጣውን ጦርነት ሸሽተው ከዓመት በፊት ነበር ወደ ዮርዳኖስ የተሰደዱት፡፡ ከዮርዳኖስ ወደ ግብፅ፤ ከግብፅ ወደ ሱዳን ከዚያም  እግሩ ላይ በደረሰበት አደጋ ምክንያት በዊልቸር የሚንቀሳቀሰውን ልጃቸውን ይዘው በመኪና እስከ ኢትዮጵያ እልህ አስጨራሽ ጉዞ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ  ዘልቀዋል፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ኢትዮጵያዊ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ አንድ ክፍል ቤት ሰጥቷቸው እየኖሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ፋጡማ፤ ተመጽውተው ባገኙት ገንዘብ የሚበላ ምግብ ይዘው እስኪሄዱ ልጃቸው እዚያች ትንሽዬ ቤት ውስጥ ሆኖ እንደሚጠብቃቸው ይናገራሉ፡፡ ቀን ቀን ምጽዋት እየጠየቁ በሚያገኙት ገንዘብ የራሳቸውን ህይወት ለማሰንበት የሚማስኑ ሲሆን፤ አካል ጉዳተኛ ልጃቸውንም በመንከባከብም በእርሱ ዘራቸው ህያው እንዲሆን ፈጣሪን እንደሚማጸኑ ይተርካሉ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከገቡበት ዕለት ጀምሮ ፍጹም ዕረፍት እንደሚሰማቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ፋጡማ፤ ኢትዮጵያዊያን እጅግ ገር እና ባላቸው አቅም ሰው ለመርዳት ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውን መገንዘባቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን ክፉ እንዳይነካቸው ፈጣሪዬን እማጸናለሁ›› በማለት ሰላም አንዴ ከእጅ ካመለጠ ለመመለስ የሚያዳግት መሆኑን ተረድተው በጥንቃቄ ሊይዙት ይገባል የሚል መልዕክት ይለግሳሉ፡፡
ሌላኛዋ ወይዘሮ ኑሪያ ዩኑስ በቦሌ አካባቢ ሕፃን ልጅ ታቅፈው እና በአማርኛ የኢትዮጵያዊያንን ዕርዳታ የሚጠይቁበትን ወረቀት በእጃቸው ይዘው ነው ያገኘናቸው፡፡ ከሶሪያ መዲና ደማስቆ በስተምሥራቅ አቅጣጫ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኝ ግሁውታ ከምትባል ከተማ ወደ ኢትዮጵያ እንደተሰደዱ ይናገራሉ፡፡ ዕድሜያቸው በሠላሳዎቹ መጀመሪያ የሚገመተው ወይዘሮ ኑሪያ ምንም እንኳን የቀን ፀሐይ እና የሌሊት ቁር መልካቸውን ቢያጠቁረውም በአንድ ወቅት መልካም ኑሮ ያሳለፉ መልከ መልካም ሴት እንደሆኑ ለመገመት አያዳግትም፡፡
‹‹በጦርነቱ የቅርብ ቤተሰቦቼን በሙሉ አጥቻለሁ፡፡ ቤትና ንብረቴ  በሙሉ ወደ አመድነት ተቀይሯል›› የሚሉት ወይዘሮ ኑሪያ፤  ተስፋ የሚያደርጉበትን በሙሉ ሲመጡ ግብፅ እና ሱዳንን አቋርጠው በወርሐ ሀምሌ 2010 ዓ.ም ወደ  ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ አዲስ አበባ  ከገቡበት ወቅት አንስቶ አነስተኛ ቤት ተከራይተው እየኖሩ ሲሆን፤ የቤት ኪራይ እና የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈንም ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ከአሽከርካሪዎች ምጽዋት ይጠይቃሉ፡፡
የፕሬዚዳንት አሳድ ደጋፊ እና ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል በተካሄደው ዓመታትን ባስቆጠረው ጦርነት ምክንያት ሶሪያ በአጠቃላይ እንደፈራረሰች የሚናገሩት ወይዘሮ ኑሪያ፤ በተለይም የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት እንደምክንያት ተጠቅመው ጦራቸውን ወደ አገሪቱ ያዘመቱት ኃያላን መንግሥታት ለንጹሐን ዜጎች ከማሰብ ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ከግምት በማስገባት እያካሄዱ ያለው ጦርነት የብዙዎችን ህይወት እንዳመሰቃቀለው በቁጭት ይናገራሉ፡፡
ፒያሳ ቤኒን መስጊድ አካባቢም ከሶርያ የመጡ ስደተኞች የሚያዘወትሩት አካባቢ ነው፡፡ ከዕለተ ዓርብ የጁምዓ ስግደት ከመስጊድ የሚመለሰውን ህዝበ ሙስሊም ዕርዳታ ሲጠይቅ ያገኘነው ወጣት ሞሃመድ ሙገነት በሶሪያዋ መዲና ደማስቆ ውስጥ ተወልዶ እንዳደገ ይናገራል፡፡ መላ ቤተሰቦቹን የነጠቀው የሀገሩ ጦርነት በሀገሩ ሠርቶ ለመለወጥ የያዘው ውጥን ህልም ሆኖ እንዲቀር ማድረጉን ይናገራል፡፡ በሀገሩ ተስፋ በመቁረጡ ከወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ያስታውሳል፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶርያዊያን ሕፃናት እና ወጣቶች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸው ወደ ተለያዩ ሀገራት ለመሰደድ መገደዳቸውን ኀዘን በተሞላበት ድምጸት የገለጸው ወጣት ሞሃመድ የሶርያ የነገ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ይናገራል፡፡ ‹‹በጦርነቱ ምክንያት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከተዘጉ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ህይወት በእዚያ እጅግ አስከፊ በመሆኑ ስደትን የሚመርጡ ብዙዎች ናቸው›› ይላል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ሰባት ዓመታትን ባስቆጠረው የሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ከ500 ሺ በላይ ዜጎች  ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከሀገሪቱ   ከ18 ሚሊዮን ህዝብ ግማሹ ከመኖሪያ ቀዬው ተፈናቅሏል፡፡ ቱርክ፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢራቅና ግብፅ የሶርያ ስደተኞችን በማስጠለል ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት መሰረተ ልማቶች በመፈራረሳቸው 95 በመቶ የሚሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ የጤና አገልግሎት ማግኘት አይችልም፡፡ 70 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አያገኝም፡፡ ከሀገሪቱ ህዝብ 80 በመቶ ለከፋ ርሃብ ተዳርጓል፡፡
Filed in: Amharic