>

ሐዲስ አለማየሁ- የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አባት !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ሐዲስ አለማየሁ- የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አባት !!!
አቻምየለህ ታምሩ
ዛሬ  ታሪካችንን የማያውቁት የአገዛዙ ሰዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተቋቋመበትን 60ኛ አመት አክብረው ዋሉ አሉ። ሰዎቹ  ከኢትዮጵያውያን  ዘመን ተሻጋሪ ተቋም ፈጣሪዎች ጋር የተጣሉ ስለሆኑ  የተቋሙን ስድሳኛ አመት  ምስረታ ሲያከብሩ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አባት የሆነውን ሐዲስ አለማየሁን ስሙን እንኳ ሳያነሱት አለፉ አሉ።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ወይንም ECA የተቋቋመው በታላቁ አርበኛ፣ ዲፕሎማት፣ አስተማሪ፣ ሚኒስትርና ደራሲ  ሐዲስ አለማየሁ ጥረት ነው። ታላቁ ሐዲስ አለማየሁ በ1950 ዓ.ም.  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበር። ይህ  ወቅት  አብዛኛው የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ሲማቅቅ  የነበረበት ወቅት  በመሆኑ ቅኝ ገዢዎች ቅኝ የሚገዙትን  አብዛኛውን  የአፍሪካ ሕዝብ እንዲለቁት  ሲጠየቁ  ያቀርቡት የነበረው ምክንያት «አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች  ነጻ ቢወጡ በኢኮኖሚ  ራሳቸውን አይችሉም» የሚል ሰንካላ ምክንያት ያቀረቡ ነበር። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ   ከነበሩት  ሁለት ጥቁር   አምባሰደሮች መካከል አንዱ የሆነው ሐዲስ ቅኝ ገዢዎች  የቅኝ ግዛት ቀንበራቸውን ለማራዘም የሚያቀርቡትን ሰበብ  በተመለከተው ጊዜ   አፍሪካን በዘላቂነት  ከቅኝ ግዛት ማላቀቅ የሚቻለው የአፍሪካውያን ትብብር ማጠናከርና የአሕጉሪቷን የኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት  ሲቻል መሆንኑ በማጤን ለዚህም  አንድ አፍሪካዊ ተቋም እንደሚያስፈልግ አምኖበት  ሀሳቡን ለንጉሠ ነገሥቱ አቅርቦ   የአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአዲስ አበባ  ሊቋቋም ቻለ። ይህ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአመሰራረት ታሪክ ነው።
በዛሬው እለት የአገዛዙ ሰዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተቋቋመበትን 60ኛ አመት አክብረው  ሲውሉ  አንዳቸውም  የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አባት የሆነውን አርበኛውን ሐዲስ አለማየሁን አንስተው ሳያስታውሱት  ማለፋቸው እጅጉን ያሳዝናል። አድዋን ያለ ዳግማዊ ምኒልክ፤ የአፍሪካ ሕብረትን ያለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማሰብ እንደማይቻል ሁሉ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንንም ያለ ሐዲስ አለማየሁ ማክበር  ክርስትናን ያለ  እየስሱ ክርስቶስ፤  እስልምናን ያለ ነብዩ መሐመድ እንደማሰብ ያለ ቅዥት ነው። ሐዲስ አለማየሁ ራሱ ከማረፉ በፊት ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር  እርጅና ተጭኖት ባደረገው  ቃለ መጠይቅ ይህንን ታሪክ  የተናገረበት ተንቀሳቃኝ ምስል  በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ላይብራሪ ውስጥ ይገኛል።
Filed in: Amharic