>
5:13 pm - Monday April 18, 2163

ወዲህ በዳዊት ወዲህ በጋሻ!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ወዲህ በዳዊት ወዲህ በጋሻ!!!
(በእውቀቱ ስዩም)
ትላንትና  ከባልንጀራየ  ምኡዝ ጋር  ተገናኝተን ቢራ ወይንና  የመሳሰሉትን አልኮሎች ስንጠጣ:-አገርን በፍቅር ስለማስተዳደር አሰፈላጊነት  ”  በሰፊው ሰበክሁለት:: እሱ  እያዛጋና እየተቅበጠበጠ ሲሰማኝ ቆይቶ ሳያስጨርሰኝ የሚከተለውን ቀደዳ ቀደደ::
“ማኪያቬሊ  ስለተባለ ዝነኛ ደራሲ ሰምተህ ይሆን?  ስለስልጣን ባህርይ  እንደ ሌሎች ሳያለባብስ  እቅጯን ፅፏል!!  ይህ ሀቀኛ ጥልያን በፃፈው ድርሳን ውስጥ እንዲህ እምትል ጥቅስ ትዝ ትለኛለች:-የታጠቁ ነቢያት ሁሉ ሲያሸንፉ ያልታጠቁ ነቢያት ግን ተሸንፈዋል”
” ሰውየው  ምን ለማለት ፈልጎ መሰለህ  ? አሪፍ መሪ ነህ እንበል!!  አገርን የሚያበለፅግ የህዝብን ኑሮ የሚያሻሽል ሀሳብ  የምታፈልቅ መሪ ነህ እንበል:: ፍቅርና እውቀት የሚገባቸውን   ዜጎች  በስብከት ልትለውጥ ትችላለህ:: ግን ይሄ በቂ አይደለም!!   ገገማው እብሪተኛው  ጦር-ጠማሹ ስለፍቅር ብትሰብከው መስሚያው ኮብልስቶን ነው!!   አገር ወደ ሁዋላ   ስትሄድ  የሚያተርፉ  ሰዎች ይነሱብሃል:: ከተሳካላቸው ከምትሰብከበት መድረክ ላይ ባፍጢምህ ይደፉሃል:: እና ራስህን እና ሀሳብህን የሚታደግ ጉልበት ከሌለህ ወዮልህ!!  አየህ!!! ቅዱስ ሀሳብ በራሱ ጊዜ እንደ ተስቦ ካንዱ ወዳንዱ አይጋባም:: በሌሎች ጭንቅላት ላይ እንደዘውድ ልትጭነው ይገባል:: ይህን ደሞ ያለ ሀይል አይታሰብም:: አብርሃም ሊንከን የሚባል ያሜሪካ መሪ -ባሮችን ነፃ የሚያወጣ ፖሊሲ  ነደፈ:: ይህ ለባሮችና ብዝበዛን ለሚጠሉ  ነጮች የምስራች  ነበር::  ባርያ ፈንጋይ ዜጎች ግን አምርረው ተቃውመታል::  እና አብርሽ ቅዱስ ሀሳቡን ለማፅደቅ ሰይፍ ማንሳት ነበረበት::
የጥጃ ሳሩ መምሬ ማምሻ
ወዲህ በዳዊት ወዲህ በጋሻ
የምትል ጥንታዊ    ዘፈን  አለች ::  መምሬ ማምሻ “ጥጃ ሳር ” በተባለ ጎጥ ውስጥ የሚኖሩ ነቄ ካህን ናቸው:: ገጣሚው እንደነገረን  መምሩ ዳዊት ብቻ ሳይሆን ጋሻም ነበራቸው:: ገጣሚው ለግጥም ምጣኔ ስላልተመቼው ዘልሎት ነው እንጂ ጦርም ሳይኖራቸው አይቀርም:: በማኪያቬሊ አገላለፅ   መምሬ ማምሻ ታጣቂ ነቢይ ናቸው::  በሽፍቶች ሰፈር ውስጥ ስትኖር ትጥቅ እንጅ  እንጂ ፅድቅ  እድሜ አያረዝምም!! ” በሞት ጥላ መካከል እንኳን  ብሄድ አንተ ከኔጋ ነህና ክፉ አልፈራም”   የሚለውን የዳዊት ጥቅስ መድገም  ያባት ነው::
ግን በቂ አይደለም:: ለምንም ለምንም-በሞት ጥላ መከከል ሲያልፉ ጋሻና ጦር ማንገብ   አይከፋም::  እና ምን ልልህ ነው?! ፍቅር ለማይዘልቀው ፍቅር መስበክ የሰነፍ ነው:: መገደል መሸነፍ ነው!! “
Filed in: Amharic