>

እርሳቸውን ያየህ ተቀጣ!!! (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

እርሳቸውን ያየህ ተቀጣ!!!
በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
በረከት ስምዖን በስርዓቱ ውስጥ “አይደፈሬ” ነበሩ። “ከእርሳቸው መጋጨት፣ ግድግዳ መግፋት ነው” ይባልላቸው ነበር። በተለይ ከ1993ቱ የሕወሓት መሰንጠቅ በኋላ የመለስ ዜናዊ ቀኝ እጅ ነበሩ። በአማራ ክልል የካድሬውን መረብ ከመቆጣጠራቸው የተነሳ በአንድ ቀን ክልሉን የሚያንቀጠቅጥ ሰልፍ መጥራት ይችላሉ ይባልላቸው ነበር። ኃይለኛ ፕሮፓጋንዲስት እና የሚዲያ ጠላት ናቸው። ለኢትዮጵያ ነጻ ሚድያ እንዲህ መሽመድመድ ከርሳቸው በላይ አስተዋፅዖ ያደረገ የለም።
ሥልጣን ሳይኖራቸው እንኳን ባለ ሥልጣን ሆነው ከርመዋል። እነሆ እርሳቸውም ዛሬ ታሰሩ። በረከት የታሰሩት  የጥረትን ንብረት አባክነዋል በሚል ተጠርጥረው እንደሆነ ተነግሯል። ባለፈው ደብረማርቆስ ላይ የደቦ ፍርድ ሊያደርጉባቸው በንዴት እሳት የጎረሱ ወጣቶች ተሰብስበው መኪና ሲያቃጥሉ አይተናል። የነዚያ ወጣቶች የንዴትና የበቀል ስሜት መንሥኤ ከጥረት ብዝበዛ ይልቅ ያንን ጨቋኝና ነፍሰ በላ ስርዓት “ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ” ሆነውበት በማቆማቸው የተፈጠረ ነው የሚመስለኝ። የሆነ ሆኖ ትልቁ በረከት ስምዖንም ታስረዋል።
በዓለም ላይ የም:ሳቸውን ሳይቀምሱ፣ ፍትሕን ያመለጡ አምባገነኖች ጥቂት ናቸው። በርግጥ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ዓይነቶቹ ሀራሪ ቁጭ ብለው ቀጣዩን ድራማ በቴሌቪዘዥን ይከታተላሉ። የጌታቸው  አሰፋ  ዓይነቶቹም አፍንጫችን ሥር ተሸሽገው ጉዳዩን ይከታተላሉ። ሆኖም የገዛ ሕሊናቸው ያሳድዳቸዋል።
Filed in: Amharic