>
5:13 pm - Wednesday April 19, 4056

ሰበታና የካራ ቆሬ ተፈናቃዮች ፒያሳ አራዳ ህንፃ ሜዳላይ ፈሰዋል!!! (ዘመድኩን በቀለ)

ሰበታና የካራ ቆሬ ተፈናቃዮች
ፒያሳ አራዳ ህንፃ ሜዳላይ ፈሰዋል!!!

ዘመድኩን በቀለ

•••
እስከ ትናንትናዋ ምሽት ድረስ ከሰበታ አጃምባ ተፈናቅለው አዲስ አበባ ጫፍ በሚገኘው ዓለም ባንክ ቅዱስ ፋኑኤል ቤተ ክርስቲያን ጊቢ ውስጥ በድንኳን ተጠልለው የነበሩት ዜጎች ከቤተ ክርስቲያኑ ለቅቀው እንዲወጡ በመደረጉ ትናንት ሌሊቱን በእግራቸው ሲጓዙ አድረው ዛሬ ረፋዱ ላይ ፒያሳ አራዳ ህንፃ ፊት ለፊት ሼክ ሁሴን አሊ አላሙዲን አጥሮት በነበረው ስፍራ ላይ ማረፋቸው ተነግሯል።

•••
የለውጡን ምስል ላለማበላሸት ሲባል ፖሊስ ስደተኞቹን ከብቦ ከህዝብና ከሚዲያ አካላት ጋር እንዳይገናኙ አድርጎ እንደዋለም ተነግሯል። ብዙ ሰዎች ተፈናቃዮቹን ለማግኘትና የምግብና የውኃ አገልግሎት ለመስጠት ቢፈልጉም ፎሊስ ነፍሴ ለተጎጂዎቹ ማንኛውም ዓይነት ዕርዳታ እንዳይደረግ በመከልከሉ እንዳልተሳካ ተነግሯል።

•••
ተፈናቃዮቹ ዛሬም አዳራቸውን በአውላላው ሜዳ ላይ ይሁን ወይም ደግሞ ሌሊት ከብቦዋቸው የዋለው ፖሊስ ጭኖ ሌላ ስፍራ ይውሰዳቸው እስከአሁን የታወቀ ነገር እንደሌለም ተነግሯል። ተፈናቃዮቹ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ እስከአሁን ግን በቂ ምግብና መጠጥም መንግሥት እንዳላቀረበላቸው ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ሰው እንዳይረዳቸውም መከልከሉ ተነግሯል።

•••
ከተፈናቃዮቹ መካከል የወለዱ አራስ ሴቶች፣ የቲቢ ህመምተኞች፣ አቅመ ደካማ አዛውንቶችም በስፍራው እንደሚገኙ የደረሰኝ መረጃ ያመለክታል። የምትችሉና የለውጡ ደጋፊዎች መሆናችሁ በመንግሥቱ የተረጋገጠ፣ መደመራችሁ ታምኖበት በአገዛዙ ፊት የተሰጣቹህ ቤተሰብ የሆናችሁ አካላት ምን አልባት አንጀታችሁ ከራራ ወደ ስፍራው ሄዳችሁ ድጋፍ እንድታደርጉላቸውም ጥሪ ቀርቧል።

•••
በሚቀጥለው ሰኞ አካባቢ ደግሞ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የለገጣፎና አካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቅቀው ደብዳቤ እንደደረሳቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። እናም በሩቅ ስንሰማው የነበረው የስደቱ ዜና አሁን አዲስ አበባ ሰተት ብሎ ገብቷል ማለት ነው። ይሄ ነገር ለአገዛዙ ዕድሜ ጥሩ ነው ወይ? ለውጡንስ ማደናቀፍ አይሆንም ወይ?

•••
የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሌያና የኤርትራን ስደተኞች ተቀብላ ፋብሪካ ገንብታ ልታስተዳድራቸው፣ አንቀባርራም ልታኖራቸው ለፈረንጆቹ ቃል የገባችዋ ኢትዮጵያችን እንዴት ነው ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ መሆን ያማራት ግን? እኔ ግን ተናግሬያለሁ። ስብከቱ ይብቃ። ድለላው ይብቃ። የተረገዘው ይወለድ። የተደበቀው ይገለፅ። ያበጠውም ይፈንዳ። ጓሮጓሮውን ባንልስ? ዙሪያ ዙሪያውን ባንሽከረከርስ? ካም ቱ ዘ ፖይንት አለ ኦባማ። ትርጉሙ ባይገባኝም አባባሏ ግን ደስ ትለኛለች። ሌኒንም የማይነጋ መስሏት በቋት…… ሲል የሰማሁት መሰለኝ።

•••
ለአብቹ መንግሥት፣ ለለማ መንግሥት፣ ለታከለ ዑማ መንግሥት። ለጀነራል ፣ ለውጭ ጉዳይ መንግሥት ብቻ ለኦፒዲኦ/ ኦነግ መንግሥት ልቦና ይስጥልን አሜን።

•••
ለአዲስ አበቤ መልካም እንቅልፍ። መልካም መኝታ። መልካም የሽሽሽሽ ጊዜ ይሁንላችሁ። ኢትዮጵያውያኑ ተፈናቃዮችም እግዚአብሔር ጥላ ከለላ ይሁናችሁ።

ሻሎም ! ሰላም !

Filed in: Amharic