>

ኦዴፓ ጭልጥ ብሎ   የኦነግን መስመር መከተሉን ጀምሮታል!!! (የሽሀሳብ አበራ)

ኦዴፓ ጭልጥ ብሎ   የኦነግን መስመር መከተሉን ጀምሮታል!!!
የሽሀሳብ አበራ
ኢትዮጵያ ከብሄር የተሰራች ሀገር ናትና፣ ከብሄርተኝነት የሚሸሽ ፖለቲካ ለቀጣይ ክፍለ ዘመን አይኖራትም፡፡ በቀጣዮ ክፍለ ዘመንም ቢሆን  ብሄርተኝነት የሚላላው  አንድ  እንደ  ፈረንሳይ ብሄሮችን ውጦ አንድ ሀገር በመመስረት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ህንድ ዲሞክራሲያዊ   የሆነ የትብብር  የብሄር ሀገር ሲመሰረት ብቻ ነው፡፡ የመልካዓምድራዊ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ  ምኞት ነው፡፡ ከምኞት ሊያልፍ አይችልም፡፡ እንዳይችል ሆኗል፡፡
  …
 ኦዴፓ
  ኦነግ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ኦዴፓ  የበለጠ ብሄርተኛ እንደሚሆን ከትቤ ነበር፡፡፡ ዶክተር አብይም ቢሆኑ ብሄርተኛ ከመሆን   አያመልጡም፡፡ ብሄርተኛ የሚሆኑት ወደው ላይሆን ይችላል፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ወክለው ኦዴፓን እስከ መሩ ድረስ ዳውድ ኢብሳን ባይሆኑ እንኳን የተወሰነ  ዳውድን መምሰል አለባቸው፡፡ ኦዴፓም ኦነግን መምሰል አለበት፡፡ያለበዚያ ማህበራዊ መሰረት የለውም፡፡ ፍቅር እና ብሄርተኝነት አንድ ነው፡፡ ስለዚህ ዶክተር አብይ  የኦሮሞ ብሄርተኛ እንጂ የኢትዮጵያ  አይሆኑም፡፡ ብሄርተኝነት ከአንድ በላይ አይዘልም፡፡ የኢትዮጵያ  ከሆኑ የኦሮሞ ብሄርተኝነታቸው ይተዋሉ፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ኦዴፓ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ ኦዴፓ ጭልጥ ብሎ   የኦነግን መስመር መከተሉን ጀምሮታል፡፡  የኦዴፓን ፍኖተ ፖለቲካ በመረዳት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን  ያህል የአንድነት አቀንቃኝ አላየሁም፡፡ ኢንጂነሩ የኦሮማራ  ታክቲካል ወዳጅነት  መሰረቱ የሚኖርበትን  ቦታ አፈላልግ ላይ ሁነኛ አረዳድ አላቸው፡፡ ሌላው የአንድነት አቀንቃኝ ጥገኛ በመሆኑ የኦዴፓን ታክቲካል የኢትዮጵያዊነት እየሰማ አንቀላፍቶ ሲያጨበጭብ  ከርሟል፡፡
 ….
ህዋኃት እና ኦዴፓ ሁለቱም በብሄር ፌዴራሊዝሙ እንደማይደራደሩ  በተመሳሳይ  ሰዓት ገልፀዋል፡፡ በተለይ ኦዴፓ በአዲስ አበባ ጉዳይ እና የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን ጉዳይ እንደሚሰራ በፖለቲካ ቋንቋ አሳውቋል፡፡ በአንድምታ ሲተረጎም አዲስ አበባን የኦሮሞ አድርጌ፣አፋን ኦሮሞን ደግሞ የሀገሪቱ የስራ ቋንቋ አድርጌ እሾማለሁ ማለቱ ነው፡፡
 ኦዴፓ እንደ ኦነግ ካልሆነ ማህበረ መሰረቱን አይተክልም፡፡ ስለዚህ ቀጣይም more Oromo, less Ethiopia   እየሆነ ይመጣል፡፡ በኢትዮጵያ  ፖለቲካ ዶክተር አብይም አቶ መለስን፣ኦዴፓም ትህነግን የመሆን ዕድላቸው   በሩ ተከፍቷል፡፡
 አዴፓ
….
 አዴፓ ከስንፍናው በተጨማሪ ወዳጅ አልባ ድርጅት ነው፡፡ የትህነግ መሻገሪያ እና የስልጣን ኮርቻ አዴፓ ነበር፡፡ አዴፓ ከኢህአዴግ የሚለየው የራሱ ህልውና የለውም፡፡ ከሌለው ደግሞ የሄደውን ጠልቶ የመጣውን ይወዳል፡፡ ኦዴፓ አዴፓን እየሸሸው ይመስላል፡፡  አዴፓ የአማራ ህዝብ ዕድል አለው፡፡ የኢትዮጵያ  ፖለቲካ ከአማራ ህዝብ ባህል እና ታሪክ  በተቃርኖ  የቆመ ነው፡፡ አዴፓንም  የኢህአዴግ  ግንባሮች ሁሉ  በተቃራኒው ሊቆሙበት ይችላሉ፡፡  ስለዚህ አዴፓ ህልውና(self ) ሊኖረው ይገባ ነበር፡፡ አዴፓ more Amhara,less Ethiopia እስካልሆነ ድረስ ታክቲካል እንጂ ስትራቴጂክ አጋር አያገኝም፡፡ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች  አዴፓ ውስብስብ ችግሮች ስላሉበት፣ ከሁሉም በበለጠ መንቃት ፣ነገን መገመት ያስፈልገው ነበር፡፡ አዴፓ መንግሥት  ነው፡፡ መቅረብ እና መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ አዴፓን አልየው በማለት ብቻ መፍትሄ አይመጣም፡፡
 ….
የአማራ አንቂዎች
 ….
 የአማራ አንቂዎች ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው የአማራን ንጥላዊ (individualist) ባህሪ ወደ ቡድናዊ  (collective) እሳቤ ቀይረዋል፡፡ የባህል አብዮት ፈጥረዋል፡፡ የአማራ ብሄርተኝነትን በምክንያት ሰርተዋል፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት የአማራ ፖለቲካ መርሆ ነው፡፡  አንቂዎች  ኢ ፍትሃዊነትን በማሳየት ተሟጋች ትውልድ ፈጥረዋል፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት በብዛት የወጣቱ ነው፡፡  በወጣቱ የተወደደ ነገር አሸናፊ ነው፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት የድል መንገድ ነው፡፡
 የአማራ አንቂዎች በቅንጅት  አማራነትን ቢሰሩም ፣ በችግሮች የታጠረ ነው፡፡
 1) አግድሞሻዊ ንትርክ
የእርስ በእርስ ፍትጊያ የአማራን ትግል በእጅጉ ይጎትታል፡፡ ጉዞውም ቀጥ ያለ ሳይሆን አግድሞሻዊ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ነገሮችን በውስጥ እየጨረሱ በላይ  ስለ አማራነት ብቻ ቢሆን መንገዱን የሰላ ያደርገዋል፡፡
2)   የመረጃ ስስነት
 ….
የመንግስቱን መዋቅር የሚመራው አዴፓ እና አና አንቂዎች ተመጋጋቢ አይደሉም፡፡ አዴፓ በራሱ ቅንፍ ውስጥ ታጥሯል፡፡ አንቂው ማዶ ቁሟል፡፡በዚህ መሃል መናበብ ይሉት ነገር ባዶ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት ጀግኖች ሰነፍ፣ሰነፎች ጀግና ሆነው ተስለዋል፡፡ አጉል ጥርጣሬ በዝቷል፡፡  ለአብነት ከሰሞኑ አቶ ንጉሱ  ታገዱ፡፡አማራ አይደሉም የሚል ወጀብ ነበር፡፡  ግን አቶ ንጉሱን ቀርቦ ማናቸው የሚለውን በውል የተረዳ አልነበረም፡፡ አንዳንዴ ለፖለቲካ ልክነት በአደባባይ  የሚነገረው እና መሬት ላይ የሚሰራው ይለያያል እንጂ አቶ ንጉሱን ያህል የአማራ ፖለቲካ ስትራቴጂስት  ብዙ ሰዎች ቢኖሩን ብዙ መሻገር ይቻል ነበር፡፡  አቶ ንጉሱን ከአማራው ይልቅ ሌላው ስለሚረዳቸው ይፈራቸዋል፡፡  አቶ ንጉሱን በአብነት አነሳው እንጂ ሌሎችም ያለስራቸው የተወገዙ፣ምንም ሳይሰሩ እንደ ባልቴት ሰፈር ለሰፈር እየተልከሰከሱ የገነኑ ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው አለመናበብ ነው፡፡ አዴፓም አንቂውም መቀራረብ አለበት፡፡ አዴፓ  ለአቅመ ሄዋን እንዳልደረሰች የገጠር ኮረዳ  ክንብንብ(መሸፋፈን) መውደዱ፣አንቂውም በአዴፓ ተስፋ አልባ መሆኑ ለመረጃ ግርዶሹ ምክንያት ይሆናል፡፡
3) የአማራ ብሄርተኝነት ላይ  በውል መረዳት አለመቻል
የአማራ ብሄርተኝነት  ቅማንቱን ፣አርጎባውን ፣አማራውን እኩል አስተቃቅፎ ለኢኮኖሚ  ተጠቃማነት የሚገነባ የፖለቲካ  ኢኮኖሚ ቅኝት ነው፡፡ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ደግሞ ከቋንቋ፣ከዘር ያለፈ ስለሆነ ባዮሎጂ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ነው፡፡  የአማራ ፍላጎትን ካሳካ ከኬኒያ መጥቶም አማራን ቢመራ ችግር የለውም፡፡ በዚህ በኩል ትህነግ ጎበዝ ናት፡፡ ከአቶ መለስ እስከ  ገብሩ አስራት፣ከጌታቸው አሰፋ እስከ አዜብ መስፍን ሙሉ ትግሬዎች አይደሉም፡፡ባይሆኑም ትግሬ እንዲሆኑ ሆነዋል፡፡ስለዚህ ለትግራይ ይሰራሉ፡፡ ስለዚህ አማራም የዘር ጥራት ላይ ከማተኮር አማራ ማድረግ(Amarazation)  ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ኦባማ ኬኒያዊ ነው፡፡ ግን አሜሪካዊ ሆኗል፡፡  ብሄርተኝነት ስነ ልቦናዊ ስሪት (psychological  make up)  ነው፡፡
4) ከሳይበር ወደ መሬት መውረድ
 በኢትዮጵያ  16 ሚሊየኑ ህዝብ ኢንተርኔት ይጠቀማል፡፡ 5 ሚሊየኑ ፊስቡክ ይጠቀማል፡፡ የዓለም ህዝብ ደግሞ 60% መረጃውን የሚያገኘው ከማህበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ሆኖም ግን   በኢትዮጵያ  የማህበራዊ  ሚዲያው ተጠቃሚ ቁጥር ዝቅተኛ ነው፡፡ ከሳይበሩ ወርዶ መሬት ላይ ማደራጀት፣የርዕዮተዓለም ስርፀት መስራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የመፃፍ ነፃነት አለ፡፡፡ ነፃነት ባለበት ወቅት ነፃነትን የሚያዘልቅ ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ አንቂነት ብቸኛ ድምፅ የሚሆነው መንግስት አፋኝ ሲሆን ነው፡፡ አሁን የተሻለ ነገር ስላለ የተግባር ስራ ያስፈልጋል፡፡ ነገ ይሄ ነፃነት አይኖርም፡፡ ብዙ ነገር ይከለከላል፡፡ ጊዜን መቅደም ያስፈልጋል፡፡
 
5) ስትራቴጂን ማጥበቅ
ፖለቲካ ጠላትን እየቀነሱ ወዳጅን አበርክቶ ወደ አሸናፊነት መስክ መራመድ ነው፡፡  በአንዴ ከሁሉ ጋር መናከስ አያራምድም፡፡ የባሰውን መርጦ መታገል፣ሌላውን እያባበሉም ቢሆን ማቆየት ያስፈልጋል፡፡  we have to choose  the less evil for tactical friendship. ተለዋዋጭ መሆን ያስፈልጋል፡፡  የፖለቲካ  አልፋ እና  ኦሜጋው ጥቅም  ብቻ ነው፡፡  no else.
  አማራ
……
ሰነፍ መሪ የሚፈጠረው ከማይጠይቅ ማህበረሰብ ነው፡፡ አማራ መንግስታዊ ማህበረሰብ በመሆኑ መንግስትን ያምናል፡፡ ነገስታት ይታመኑ ነበርና፡፡ ጃንሆይ ይባላሉ፡፡ ጥላ ከለላየ ማለት ነው፡፡ በአማራ ዘንድ መንግስት ጥላ ነው፡፡  ስለዚህ የአቶ መለስ አስተዳድርንም ሆነ የዶክተር አብይን አስተዳድር አማራ ከሁሉም በተሻለ ተቀብሏል፡፡ የአማራ ህዝብ መንግስትን አማኝ ነው፡፡ ይህ ግን አሁን ባለው ፖለቲካዊ ስሬት አያዋጣም፡፡ እየጠረጠሩ መጠየቅ፣ብልሹ አሰራርን እምቢ ማለት፣ የሚመጣውን ነገር  ሁሉ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እንደ ህዝብ አብንን በገንዘብ ማጠናከር፣የአማራ ድርጅቶችን በሙሉ መንከባከብ፣ማንነትን ማክበር፣ ፖለቲካን መከታተል፣ተከታትሎም የራስ ሚሆነውን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ ራስነት(self identity ) ያስፈልጋል፡፡ ማንም ደርሶ ሂያጅ  ሁሉ  የሚዘግነው የሰፌድ ቆሎ መሆን  ድልን ይቀብራል፡፡ The real power emantes from self identity-AMHARA. ከኢትዮጵያዊነት መንፈሳዊ አምልኮ ወጥቶ ኢትዮጵያን በፖለቲካ  ዓይን ማየት ያስፈልጋል፡፡
እንዲህ ከሆነ ችግር ሸሽቶ መፍትሄ ይቀርባል፡፡
Filed in: Amharic