>

ፖለቲከኞቻችን፤ ሆድ ለባሰው ሕዝብ ማጭድ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ፖለቲከኞቻችን፤ ሆድ ለባሰው ሕዝብ ማጭድ…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍ፣ መፈናቀል፣ ወከባ፣ ዝርፊያ እና የኑሮ ውድነት አዝለውታል። ዛሬ  ሆድ ያልባሰው ኢትዮጵያዊ የለም ማለት ይቻላል። ትላንት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሆድ ያስብሱ የነበሩት ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ መቀሌ ከትመው ብሶተኞች ሆነዋል። ወደ ሚዲያ ብቅ ባሉ ቁጥር የብሶት እሮሮ ነው የሚያሰሙት። ከሁሉም የአገሪቱ አቅጣጮዎች እስከ ሸገር ድረስ ብሶት በሽ ሆኗል። በአዲስ አበባ ጉዳይ ብሶት አለ፤ በወልቃይት፣ በራያ እና በቅማንት ጉዳይ ብሶት አል፣ የክልል ይገባኛል ጥያቄ ባነሱ ማህበረሰቦች ዘንድ ብሶት አለ፤ ከቀያቸው በተፈናቀሉ ብዙ መቶ ሺዎች ዘንድ ብሶት አለ፣ ሕገ ወጥ እየተባለ ለዘመናት የኖሩበት ቤት እየፈረሰባቸው ባሉ ዜጎች ዘንድ ብሶት አለ፤ በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ብሶት ብሸ በሽ ነው።
የትላንት ብሶቶቻችን ምላሽ እና እልባት ሳያገኙ አዳዲስ ብሶቶች በላይ በላያቸው ላይ መታከሉ ደግሞ ብዙዎችን እቋፍ አድርሷቸዋል። እነዚህን ብሶቶች ደግሞ ባለማወቅም ሆነ ብለው የሚያራግቡ ሰዎች በመበራከታቸው ፖለቲካችንንም ሆነ የአሳብ መለዋወጫ መድረኮቻችንን የቀለጠው መንደር አስመስሏቸዋል። በቀን ውስጥ በርካታ አገራዊ አጀንዳዎች በየውይይቱ መድረክ ይነሳሉ፣ ይወቀጣሉ ነገር ግን ተጨምቆ ለግንዛቤ የሚውል ነገር ማግኘት መከራ ሆኗል። እጅግ ከፍተኛ ጥናት፣ ምርምር እና ጥልቅ እውቀት በሚጠይቁ ጉዳዮች ሁሉ ከታዋቂ ፖለቲከኞች አንስቶ ብዙ ተንታኞች ያለ ምንም በቂ ዝግጅት እና እውቀት ተነስተው ያሻቸውን ሲቦተልኩ መዋል የተለመደ ሆኗል። በሕዝብ እና በአገር ጉዳይ አደባባይ ወጥቶ ለመናገር እውቀት ሳይሆን ድፍረት ብቸኛ መስፈርት የሆነም ይመስላል። ይህ አይነቱ የእዘጭ እቦጭ ጉዞ ሊያገግም እየዳኸ የነበረውን ፖለቲካችንን ከወዲሁ ጤና እንዲያጣ እያደረገው ይመስላል።
በሌላ በኩል በመንግሥት በኩል ለአንዳንድ ወሳኝ እና ወቅታዊ ለሆኑ አገራዊ ጉዳዮች የሚሰጠው ትኩረት እና በጉዳዮቹ ላይ ለሕዝብ ግልጽነት የተሞላው ማብራሪያና ገለጻ አለመደረጉ ውዥንብሩን አባብሶታል። አልፎ አልፎም ገዢው ፓርቲ እና ሌሎች የተቃዋሚ ኃይሎች የሚወስዷቸው እርምጃዎች እና የሚሰጧቸው መግለጫዎች ውዥንብር ውስጥ ላለው እና ሆድ ለባሰው ሕዝብ ማጭድ እንደማዋስ ያህል የሚቆጠሩ ናቸው።
መንግስት ቢያንስ ከዚህ በሚከተሉት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ግልጽ ማብራሪያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሊሰራ ይገባዋል፤
፩. የፌደራል መንግስቱ መቀለ ከመሸገው የህውሃት አመራር እና ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር ያለው የሻከረ ግንኙነት ዛሬ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የተፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ ወይም ለመድፈን ምን ምን እርምጃዎች ተወሰዱስ፤ እየተወሰዱስ ይገኛሉ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሎች ክልሎች እንደሚያደርጉት ሁሉ መቀሌን እና የትግራይ ክልልን መጎብኘት ይችላሉ ወይ? ካልቻሉ ለምን? ከቻሉስ ለምን ወደ ክልሉ ሔደው ሁኔታውን ለማብረድ ጥረት አያደርጉም? ከክልሉ ፕሬዚደንት ከደብረጺዮን ጋር እየከረሙ ፎቶ ተነስተው የሚልኩልን ከልብ ወይስ ሕዝብን ለመደለል? የሰሞኑ የደብረጺኦን ፉከራ እና የክተት የሚመስል ጥሪስ በአገር ላይ የተሰነዘረ እና የተቃጣ ዛቻም አይደለ ወይ? በመሃል እየተጎዳ ላለው ደሃ የትግራይ ሕዝብስ ተጠያቂው ማነው?
፪. በአማራ ክልል እና በትግራይ ክልል መካከል የሚታየውስ ውጥረት እና አንዱ በአንዱ ላይ የሚያደርገው ዛቻ እየተባባሰ መምጣቱ የአገሪቱን ጠቅላላ ፖለቲካ እና ሰላም አያደፈርስም ወይ? ይህን ችግር ለድንበር እና ማንነት ጥያቄን እንዲያጠና ለተሰየመው ኮሚሽን መተው ይቻላል ወይ? በተለይም አንደኛው ወገን ማለትም የትግራይ ክልል ይህን ኮሚሽን እንደማይቀበል በይፋዊ መግለጫ አሳውቋል። ስለዚህ የፌደራል መንግስቱ የሁለቱን ክልሎች ባለሥልጣናት የአገር ሽማግሌዎችን ሰብስቦ በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጦ ችግሩን በጋራ ለመፍታት ወይም ቢያንስ ወደፊት ጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ ሁለቱ ወገኞች ከጸብ አጫሪ ተግባራት እንዲታቀቡ የመግባቢያ ሰነድ በማስፈረምም ሆነ ሌሎች ፖለቲካዎ መፍትሔዎችን መውሰድ የለበትም ወይ? እየወሰደ ያለው እርምጃስ ካለ ለሕዝብ ማሳወቅ የለበትም ወይ? ሁለቱ ክልሎች በተጋጩባቸው ሥፍራዎች ያለው ውጥረት ተባብሶ ለሰዎች መፈናቀል እና ለህይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። ስለዚህ ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? በቅርቡ በጎንደር አካባቢ የተከሰተው በመሳሪያ የተደገፈ ግጭት ብዙዎችን አፈናቅሏል፤ የሰው ህይወትም አልፏል። በዚህ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ ሰለሁኔታው በቂ ማብራሪያ አለመስጠቱ ለምን ይሆን?
፫. በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ባለው የልዩ ጥቅም ጉዳይ ብዙ አደናጋሪ መረጃዎች እየተሰራጩ እና የተወሰኑ ፖለቲከኞችም ጉዳዩን የመፋለሚያ አጅንዳ አድርገው ከጦር መለስ የቃላት ሰይፍ እየተማዘዙ ሕዝቡን ግራ አጋብተውታል። አንዳንዶችም ዛቻና ማስፈራሪያ በሕዝብ ላይ በአደባባይ ሰንዝረዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ሕዝብን ከእንዲህ ያሉ ውዥንብሮች የማረጋጋት እና የሰላም ኑሮውን እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት የፌደራል መንግስቱ ጉዳዩን ችላ ማለቱ ወይም ክብደት ሳይሰጠው መቅረቱ እንደገና ሌላ የመወናበጃ ርዕስ እንዲሆን አድርጓል። መንግስት በዚህስ ጉዳይ የከተማዋ ነዋሪም ሆነ ሌላው ሕዝብ እንዲረጋጋ በቂ ማብራሪያና መግለጫ መስጠት፤ ህብረተሰቡን ማስተማር እና በሕገ መንግስቱ የተቀመጡንት መሰረታዊ የሆኑ ድንጋጌዎች ሕዝቡ እንዲያውቃቸው እና በደንብ እንዲረዳቸው ማድረግ የለበትም ወይ?
እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። ለማንኛውም የአንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች እና የመብት አቀንቃኝቾ በሚያሰራጩት ኃላፊነት የጎደላቸው እና ወቅቱን ያላገናዘቡ መረጃዎች ሕዝብ ግራ ሲጋባ እውነቱን በማሳወቅም ሆነ በቂ ማብራሪያ በመስጠት ሕዝብን ማረጋጋት የማን ኃላፊነት ነው?
እንደ እኔ እምነት የብዙዎቹ የሃሰት ወይም የተዛቡ መረጃዎች ምንጭ  ሊሆን የሚችለው የመንግስት ግልጽነት የጎደለው አሰራር እና በወቅቱ ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ ያለመስጠት ችግር ነው። ሁሉ ነገር አደባባ እንደ ስጥ ባይሰጣም አደባባይ ላይ መነጋገሪያ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መንግስት የሚያሳየው የሽፍንፍን ባህሪ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። ሆድ ለባሰው ሕዝብ ደግሞ በማደናገሪያ የሽብር ወሬዎች ላይ የመንግስት ዝምታ ወይም የመሸፋፈን ባህሪ ሲታከልበት ወደ ሌላ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና በማህበረሰቡም ውስጥ እርስ በርስ መተማመንን እንዲጠፋ ያደርጋል።
መንግስት የሽፍንፍን ፖለቲካውን ያቁም። ለአገር ደህንነት እና ለሕዝብ ሰላም ሲባል ሊደበቁ ከሚገባቸውና ከፍተኛ ምስጥር ተደርገው ከሚወሰዱ ጉዳዎች ባለፈ ከላይ በተጠቀሱት እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ጋር በግልጽ የመወያየት ባህልን ከወዲሁ ማዳበር አለበት። የመንግስት አሰራር ከወዲሁ ሽፍንፍን በሚበዛው ባህላችን ከተጠለፈ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው ጉዙ እጅግ እሩቅ እና የማይደረስበት ህልም ይሆናል። የዲሞክራሲ ባህል በወrኤ ሳይሆን በእውቀት እና በግልጽነት በሚደረጉ ውይይቶች ነው የሚዳብረው። ድምሩ ሳይናድ በፊት መንግስት ከላይ በተጠቀሱት እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ወቅቱን የጠበቀ ማብራሪያ ሊሰጥ እና ሕዝቡን ሊያረጋጋ ይገባል።
 በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic